HM

የአዘጋጁ ማስታወሻ፡ ቀደም ሲል ባቀረብነው መረጃ ላይ አንዳንድ ስህተቶችን ስላገኘንበት አርትዖት አድርገን እንደገና አቅርበነዋል።

ዋዜማ ራዲዮ- በሐዋሳ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ከፍቶ ስራ የጀመረውና ለስዊድኑ ኤች ኤንድ ኤም (H&M) ልብሶችን የሚያቀርበው የባንግላዴሽ ኩባንያ (ዲቢኤል) ለኢትዮጵያውያን ሠራተኞቹ የሚፈጽመው 1050 ብር ወርሃዊ ክፍያ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ስዊድን ውስጥ ውዝግብ አስነሳ።

የስዊድን የሕዝብ ቴሌቪዥን ኤስቴቬ ካካሔደው ምርመራ በመነሳት ባቀረበው ዘገባ ዲቢኤል በሐዋሳ ማምረቻ ፋብሪካው ለቀጠራቸው ሠራተኞች በወር የሚከፍላቸው 1050 ብር ወይም 300 የስዊድን ክሮነር ብቻ ነው። ይህ ክፍያ በስዊድን ለሚገኙት የኤች ኤንድ ኤም ደንበኞችና ለማኅበረሰቡ ለማመን የሚያስቸግር እጅግ ዝቅተኛ ክፍያ ከመሆነም በላይ የጉልበት ብዝበዛ ተደርጎ ሊታይ የሚችል ነው። ይህም ኤች ኤንድ ኤም ”ያለቁ ምርቶችን በሚያቀርብለት ዲቢኤል የምርት ሒደት ላይ በቂ ክትትል አላደረገም፣ በዚህም የብዝበዛው ተባባሪ ሆኗል” የሚል ከፍተኛ ትችት እያስተናገደ ነው። ይህን ተከትሎም የኤች ኤንድ ኤም የአክስዮን ባላድርሻ የሆነው ኖርዲያ (Nordea) የተባለው ባንክ ተጭማሪ ማብራሪያ እስከሚሰጠው ድረስ ለኤች ኤንድ ኤም ተጨማሪ መዋእለ ንዋይ እንደማይሰጥ አስታውቋል።

በዚህ ውዝግብ ለትችት የተዳረገው ኤች ኤንድ ኤም ብቻ አይደለም። ዲቢኤል ፋብሪካዎቹን በመቀሌና በሐዋሳ ሲገነባ ከተለያዩ ምንጮች ብድር አግኝቷል። ከእነዚህ አብዳሪዎቹ አንዱ ስዌድፈንድ (Swedfund) የተባለው ከመንግስት ጋራ የተያያዘና ድህነትን በኢንቨስት ለመቀነስ ይስራል የሚባል ድርጅት ነው። ስዌድ ፈንድ ከሁለት ዓመት በፊት ለዲቢኤል 15 ሚልዮን ዶላር ሲያበድር ስምምነቱ ኤች ኤንድ ኤምን ያካተተ ነበር። (የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለተመሳሳይ ፕሮጀክት ለዲቢኤል በድምሩ ከ70 ሚልዮን ዶላር በላይ ማበደሩን ፎርቹን ጋዜጣ በግንቦት 2008 ዘገቦ ነበር።) ስዌድፈንድ ብድሩን ሲሰጥ ኤች ኤንድ ኤም ረዘም ላሉ ዓመታት የዲቢኤልን ምርቶች ሊወስድ፣ እንዲሁም ዲቢኤል በምርት ሒደቱ የዘላቂ ልማት መርሆችን እንዲተገብር ለመርዳትና ለመከታተል ተስማምቶ ነብር። ከዘላቂ ልማት መርሆች አንዱ ደግሞ ሠራተኞች ተገቢ ክፍያ እንዲያገኙ፣ ምቹና መብት የሚከበርበት የስራ ከባቢ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ኤች ኤንድ ኤም በሰሞኑ ውዝግቡ ላይ እስካሁን አስተያየት ባይሰጥም፣ ስዌድ ፈንድ ግን ጣቱን ወደ ቀጣሪው ወደ ዲቢኤል ጠቁሟል።

ኤች ኤንድ ኤም፣ ዲቢኤል፥ ስዌድፈንድ እና ልማት ባንክ የተጣመሩበት ኢንፈስትመንት ከ4000 በላይ የስራ እድል ፍጥሯል ተብሎ ሲወደስ ነበር። ኤች ኤንድ ኤም እና ስዌድፈንድ ለኢትዮጵያውያኑ የሚከፈለው ደሞዝ በቂ ነው ባይሉም ቀጣሪው ዲቢኤል በአገሪቱ ከሚከፈለው ያነሰ አልከፈለም፣ ሲጀመር የአገሪቱ የደሞዝ ክፍያ መጠን በጣም ዝቅተኛ ነው የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ። የኤች ኤንድ ኤም ተወካይ የሰራተኞች ከሞዝ ከፍ እንዲል ከዲቢኤልና ከመንግስት ጋራ እየሰራን ነው ብለዋል።

አሁን በሐዋሳ ኢንዱሰትሪ ፋብሪካ ተቀጥራ በመሰራት ላይ ያለችው የባህርሰው ጥበቡ “እየተጠቀሙብኝ ነው። ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሰው ሃገር እንደሚሰሩ አይነት ሰዎች እንደሆንኩ ይስማኛል፡፡ ግን ይህ ሃገሬ ነው።” ስትል ለኤስቬቴ (SVT) ቴሌቭዥን ጣቢያ አሰተያየቷን ሰጥታለች ። ሰራተኞች ከዝቅተኛ ክፍያ በተጨማሪ ድንገት ህመም ቢያጋጥማቸው አንድ ቀን ለቀሩበት ከወር ደሞዛቸው 20 በመቶ ይቆርጥባቸዋል ሲል ይኸው ቴሌቭዥን ዘግቧል።
እንደ ኤች ኤንድ ኤም (H&M) እና ዛራ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ስም እና ዝና ያላቸው የልብስ ሻጮችንና አቅራቢዎቻቸውን ወደ ሃገርቤት ለመሳብ የኢትዮጲያ መንግስት በርካታ ማበረታቻዎችን ለማድረግ ሲሞክር ስንብቷል። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹና ሌሎቹም ማበረታቻዎች ሻጮቹናን አቅራቢዎቻቸውን መሳብ ለመቻሉ እነ ኤች ኤንድ ኤም እና ዲቢኤል ማሳያዎች ናቸው። እንዚህ ኩባንያዎች ወደአገሮች ከሚሳቡባቸው ቁልፍ ምክንያቶች አንዱ የጉልበት ዋጋ ዝቅተኝነትና ጥብቅ ቁጥጥር የማይደረግበት የጉልበት ገብያ ተጠቃሾች ናቸው። ኤች ኤንድ ኤምም ሆነ ዲቢኤል ቻይናና እና ባንግላዴሽን በመሳሰሉ አገሮችን ያላቸን ስራ በመቀነስ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት አንዱ ምክንያትም ይኸው እንደሆነ በስፋት ይነገራል።
“ችግሩ መንግስት ምን ያህል ስራ እንደምንፈልግ ያውቃል። ከቀጣሪያችን ጋር በመሆን ምን ያህል ለእኛ መከፈል እንዳለበት ስምምነት አደርጓል” ትላለች የባህርሰው።
“ሶስት ሺህ ብር እንድሚከፈለን በደላሎቻቸው አማካኝነት ሲነግሩን አሰተማሪዎች ሳይቀሩ ስራቸውን ጥለው በፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው ነበር፣ ነገር ግን እውነተኛ ክፍያው በወር 1050 ብር ብቻ ነው።”
አንድ የኤች ኤንድ ኤም አቅራቢ ባንግላዴሽ በነበረው ፋብሪካው ውስጥ በደረሰ የመደርመስ አደጋ አንድ ሺህ 1 መቶ ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ፣ የሥራ ላይ የደኅንነት ማረጋገጫዎችን ሰለማይተገብር ወቀሳ ደርሶበት ነበር። በተመሳሳይ በኢትዮጲያ ባለው የዲቢኤል ፋብሪካ መሰረታዊ የደኅንነት ማረጋገጫዎች አልተሟሉም ተብሏል። ኤች ኤንድ ኤምን የመሳሰሉ ድርጅቶች በምርት ሂደት ሰብአዊ መብቶች እንዳይጣሱ ክትትል የማድረግና ለማረም የመሞከር ሃላፊነት ቢኖርባቸውም፣ ትርፍ ለማጋበስ ቅድሚያ ይሰጣሉ እየተባሉ በስፋት ይወቀሳሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኩባንያዎቹን አግባብቶ ወደኢትዮጵያ እንዲመጡ ለማድረግ የሚሞክረውን ያህል ዜጎቹ ተመጣጣኝ ክፍያ እንዲያገኙ ለመከራከር ከሚደፍርበት ደረጃ አልደረሰም። እንዲያውም ኩባንያዎቹን የማባበልና መሰል ጉድለቶችን እንዳላዩ ማለፍ ለጊዜው የተመረጠ ስልት ይመስላል።

በፋርማሲ እና በኤሌክትሪክ ኢንጂነሪንግ ላይ በቅርቡ ኢንቨስት አድርጎ ስራ የጀመረው የባንግላዴሹ ዲ ቢ ኤል ግሪፕ በኢትዮጲያ ባሉት ፋብሪካዎቹ ለጨርቃጨርቅ የሚሆኑ ጥጦችን በመፍተል፣ በማቅለም፣ በማተም፣ በማሸግ ስራ ላይ ተሰማርቷል። እ.ኤ.አ በ1991 ጀምሮ ስራ የጀመረው ይኸው ቡድን ያለቁላቸው ልብሶችን የማምረት ስራ በመቀሌ ፋብሪካዉ በየካቲት 2010 ይጀምራል ተብሏል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገሮችን የኢንቨስትመንት ምቹነት የሚያጠናው ሲልክ ኢንቨስት የተባለ ድርጀት እንደሚለው በኢትዮጲያ በአሁኑ ሰዓት ከህንድ፣ ከሱዳን፣ ከጀርመን፣ ከጣሊያን፣ ከቱርክ፣ ከሳውዲዓረቡያ፣ ከየመን፣ ከእንግሊዝ፣ ከእስራኤል፣ ከካናዳ የመጡ አዳዲስ ፋበሪካዎችን በሃገሪቷ አቋቁመዋል። [ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ተያይዟል]

 

https://youtu.be/LqN-lo8NzkM