Tedy Afro  photo credit -Mario Di Bari
Tedy Afro
photo credit -Mario Di Bari

(ዋዜማ) በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ እንደ አዲስ ዓመት፣ ገና እና ፋሲካ በዓላት ተጠባቂ ጊዜ የለም፡፡ አንጋፋ የሚባሉ አቀንቃኞች ሳይቀሩ የሙዚቃ አልበሞቻቸውን ለአድማጭ ጆሮ የሚያደርሱት እነዚህን በዓላት ታክከው ነው፡፡ የዘንድሮ ፋሲካም እንደከዚህ ቀደሞቹ በጥበባዊ ስራዎች ሊያሸበርቅ ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡

በሙዚቃው ሰፈር ያሉ ሰዎች እስከ ሰባት የሚደርሱ አልበሞች ለፋሲካ ይደርሳሉ የሚል ግምት ቢኖራቸውም ጣጣቸው አልቆ በእርግጠኝነት ለመለቀቅ ጊዜ እየጠበቁ ያሉት ከአምስት አይበልጡም፡፡ ስራቸውን ለሙዚቃ አፍቃሪያን ከሚያደርሱ ዘፋኞች መካከል በመጀመሪያው ረድፍ ያሉት ጸደኒያ ገብረማርቆስ እና ሄኖክ መሀሪ ናቸው፡፡ ከወጣቶቹ የዘውድ አኩስቲክ ባንድ መስራች ሳሚ ዳን እና ተቀማጭነቱን በስዊድን ያደረገው ዳንኤል ለማ ይጠበቃሉ፡፡

ለፋሲካ ይጠበቁ የነበሩት ጃኖዎች እስካሁን በይፋ ምንም አላሉም፡፡ ቴዲ አፍሮ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ እና ሄለን በርሄ አልበማቸው ለበዓሉ ይደርሳል ተብሎ ቢጠበቅም የሶስቱም አልበሞች ለበዓለ ትንሳኤ እንደማይወጡ ምንጮች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡

ቴዲ አፍሮ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በኦፌሴሊያዊ የፌስ ቡክ ገጹ አማካኝነት አዲሱን አልበሙን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ቢገልጽም እንደ ቅርብ ምንጮች ገለጻ ከሆነ አሁን ባለበት ደረጃ ስራው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ለመውጣት አንድ ወር ገደማ ያስፈልገዋል፡፡ ለፋሲካ ከስራዎቹ መካከል አንዱን በነጠላ ዜማ መልክ እንደሚያስደምጥ ይጠበቃል፡፡

አዳዲስ ዘፈኖች እየሰሩ የሚገኙት ጎሳዬ እና ሄለን ከአዲስ ዓመት በፊት ባሉት ወራት አሊያም ለዘመን መለወጫ ስራቸውን ይዘው እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በድንገት በሞት የተለየን የኢዮብ መኮንን የመጨረሻ ስራዎችም ከበዓሉ በኋላ ወዳሉት ወራት መገፋታቸውን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡

የበርካታ አልበሞች በአንድ ጊዜ መለቀቅ የገበያ ፉክክሩን የሚያጦዘው ሲሆን ለአድማጩም ዓይን አዋጅ መሆኑ ግልፅ ነው። የፀደኒያ አልበምን ይዘት የተመለከትንበት ዝርዝር ዘገባ እዚህ በማስፈንጠሪያው ይመልከቱት -ጠቅhttp://wazemaradio.com/?p=2046