Photo -Deputy Mayor office (FILE)
  • የአለም ባንክና የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ድርጊቱን ተቃውመዋል

ዋዜማ ራዲዮ- የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ወደ ሀላፊነት ከመምጣታቸው በፊት በከተማው ያሉ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች እንደየስራ ጸባያቸው ለከተማው አስተዳደር የተለያዩ ቢሮዎችና ማዘጋጃ ቤቱ ተጠሪ ሆነው ነው የቆዩት። ይህ የተለያዩ ዘርፎችን በስራ ክፍፍል ለመምራትና ለተጠያቂነት ምቹነትን ይፈጥል ተብሎ የተደረገ የቆየ አሰራር ነው ።

ምክትል ከንቲባ ታከለ ወደ ሀላፊነት ከመጡ በሁዋላ በተለይም በቅርቡ ለተለያዩ ቢሮዎችና ለመዘጋጃ ቤቱ ተጠሪ የነበሩ ተቋማትን በቀጥታ ተጠሪነታቸው ለራሳቸው ማለትም ለከንቲባው ጽህፈት ቤት በማድረግ እየጠቀለሏቸው መሆኑን ከመስተዳድሩ የተለያዩ ሀለፊዎች ስምተናል።

ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ ከተማይቱን የመምራት ሀላፊነቱን በበላይነት የሚቆጣጠሩ አፈፃፀሙን የሚከታተሉ ይሁኑ እንጂ ቁልፍ የከተማው ጉዳዮች የሚወሰኑት በከተማው ምክር ቤት ውሳኔ እንዲሁም የካቢኔ አመራሮች ማለትም በዘርፍ በተደራጁ ተቋማት ነው።


የዋዜማ ራድዮ ምንጮች በአስረጂነት ካቀረቧቸውና በምክትል ከንቲባው ከተጠቀለሉ ቢሮዎች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ተጠሪነቱ ለከተማ አስተዳደሩ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ነበር።

ሆኖም በምክትል ከንቲባ ታከለ ፍላጎት የኤጀንሲው ተጠሪነትን ለራሳቸው ጽህፈት ቤት አድርገውታል። ቀድሞ የኢንቨስትመንት ኤጀንሲው ተጠሪነቱ ለንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሲሆን እንደ ንግድና ኢንቨስትመንት ላሉ ስራዎች ፍቃድ ከመስጠትና ሌሎች አገልግሎቶች አንጻር የተቋማቱ ስራ ተመጋጋቢ በመሆኑ ተናበው ለመስራት እንዲረዳቸው ታስቦ የተደራጀ ነው።

በሌላ በኩል ለከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ቢሮ ተጠሪ የነበረውን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣንንም ታከለ ኡማ ተጠሪነቱን ለራሳቸው አድርገውታል። ሁለቱ ተቋማት ልክ በፌዴራል ደረጃ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለትራንስፖርት ሚኒስቴር ተጠሪ እንደሆነው አይነት ነው። ምክትል ከንቲባው እየወሰዷቸው ያሉት እርምጃው ዘርፋቸው በሚቀራረቡ ተቋማት መካከል ያለ የእርስ በርስ ተጠያቂነትን የሚያጠፋና የካቢኔ አባል የሆኑ የቢሮ ሀላፊዎችን አስፈላጊነትንም ጥያቄ ውስጥ የጨመረ ሆኗል።


በመዘጋጃ ቤት ስር የነበረውን የአዲስ አበባ ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣንንም ወደ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ተጠሪነቱ ዞሯል። የባለስልጣኑ አንድ ከፍተኛ የስራ ሀላፊ ለዋዜማ ራዲዮ እንዳሉትም ውሀና ፍሳሽን የተመለከቱ ስራዎች በፍጥነት በመዘጋጃ ቤቱ የማለቅ እድል የነበራቸው ሲሆን አሁን ግን ያለው ከፍተኛ የውሃ ችግር ሳያንስ ጉዳዮች በሙሉ ወደ ምክትል ከንቲባው እየተመሩ ከፍተኛ መጓተቶች እያጋጠሙ ነው ብለዋል። ከተማው ሌሎች በመዘጋጃ ቤት ስር የነበሩ ወሳኝ ኩነት ፣ ውበትና ጽዳት የመሳሰሉትም ወደ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ተዘዋውረዋል። በመሬት አስተዳደር ስር የነበረው ግንባታ ፍቃድና ቅንጅት የመሳሰሉ ተቋማትም ተጠሪነታቸው ተቀይሯል።


ምክትል ከንቲባው በከተማይቱ ተቀባይነትና ይሁንታ ለማግኘት ባላቸው ጉጉት የተሻለና ፈጣን ውጤት ለማምጣት ያደረጉት እንደሆነ ግምታቸውን የሚናገሩ የአስተዳደሩ ሰራተኞች አሉ። ሌሎች ግን እርምጃው የስልጣን ጠቅላይነትና ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤትም ሆነ የካቢኔ አባላት ባላቸው ስልጣንና ሀላፊነት ሁኔታውን ለማስተካከልና ለመጠየቅ ሲጥሩ ብዙም አይታዩም። ምክትል ከንቲባው ያለ ምንም ህግ ተወርዋሪ ፖሊስ ሲያቋቁሙም ሁለቱ አካላት መረጃውም የላቸውም፣ ሰምተውም አልጠየቁም።

ዋዜማ ራዲዮ እንደሰማችው የምክትል ከንቲባውን ድርጊት ተገቢ አይደለም ፣ ከተማ እንዲህ አይመራም ሲል የአለም ባንክ አስጠንቅቋል። ባንኩ በከተማው የመዘጋጃ ቤት ስራ ለመዘጋጃው እንዲሁም የቢሮዎች ስራም ለቢሮዎች መሆን አለበት ያለ ሲሆን የምክትል ከንቲባው ስራ ስትራቴጂያዊ አመራር መስጠት ላይ ማተኮር እንዳለበት ጠቁሟል። የአለም ባንክ ብቻ ሳይሆን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በታከለ ኡማ የአደረጃጀት ለውጥ ላይ ያለውን ተቃውሞ መግለጹን ሰምተናል። ሆኖም ይህን ተከትሎም የተደረጉ ማስተካከያዎች የሉም። [ዋዜማ ራዲዮ]