ዋዜማ ራዲዮ-በሀገሪቱ በፖለቲካ አመለካከታቸው አልያም በጥርጣሬ ብቻ ታስረው ስቃይ የሚፈፀምባቸው በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች አሉ። የስቃዩ መጠን ይለያያል። ይህ ገዥው ፓርቲ አፋፍሞ የቀጠለው ግፍና እስር ዛሬ በሀገሪቱ ለተከሰተው ህዝባዊ አመፅ አንዱ ምክንያት ነው። ግፍ እየተፈፀመባቸው ያሉ የተወሰኑ እስረኞችን እናስተዋውቃችሁ። [በድምፅ የተሰናዳውን ዘገባ ከግርጌ ያድምጡ]
የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈፀመባቸውን ዜጎች ሁሉ ዘርዝሮ በደላቸውን ለማንሳት ቢያሰቸግርም ዋዜማ ራዲዮ ከኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት ጋር በመተባበር መንግስት የሽብር ክስ መስርቶባቸው በማዕከላዊ፣ በቅሊንጦ፣በቃሊቲ እንዲሁም በሽዋ ሮቢት ማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ ሳሉ በሶስት እስረኞች ላይ የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከራሳቸው ከእስረኞቹ ያገኘነውን መረጃ አጠናቀረነዋል።
አግባው ሰጠኝ የ38 አመት ጎልማሳ ነው፡፡ በሽብር ክስ ተመሰርቶበት ከተመሰረተበት ክስ ነፃ ቢባልም አሁንም በቅሊንጦ ይገኛል። የቅሊንጦን ማረሚያቤት በማቃጠል ሰው እንዲሞት አድርገሃል በሚል ዳግም የሽብር ክስ ተመሰርቶበታል።
የዋቄ ፈናን ሃይማኖት መከተሉ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የዳረገው ለማ ባየ በቅሊንጦ ከክርስትና እና እስልምና ውጪ ምንም አይነት የአምልኮ ሰርዓት አትፈፅምም ተብሎ ጫና እንደደረሰበት ተናገሯል፡፡
ከኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት አሰተባባሪ ሶሊያና ሽመልስ ጋር ኤዶም ካሳዬ በማዕከላዊ፣ በቅሊንጦ፣በቃሊቲ እንዲሁም በሽዋ ሮቢት ማረሚያ ቤቶች በተቋማዊ አደረጃጀት ሰለሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን የሶሰቱ ታሳሪዎችን ገጠመኝ አያነሱ ይወያያሉ።