ዋዜማ ራዲዮ- የገንዘብ ሚንስቴር ሚንስትር አህመድ ሽዴ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው በምስራቅ አፍሪካ ፋይናንስ ጉባኤ የመክፈቻ ላይ የኢንሹራንስ ቁጥጥር ተቋም ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አንስተው ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢንሹራንስ ቁጥጥር በብሔራዊ ባንክ የፋይንናስ ተቋማት ስር በዳይሪክቶሬት ደረጃ እየተመራ ይገኛል።
ጉዳዩ ለረጅም አመታት የዘርፉ ጥያቄ ሆኖ የሰነበተ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ጉባኤ ላይም ዋና መናጋገሪያ ሆኖ ውሏል።
ጉዳዩ ለረጀም ጊዜ ውይይት ሲደረግበት ቆየቶ አሁን ለውሳኔ ሰጪዎች እንደቀረበ፣ መቼ ውሳኔ እንደሚያገኝ ግን መናገር እንደማይችሉ አቶ በላይ ቱሉ የብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተናግረዋል።
የኒያላ ኢንሹራንስ ዋና ስራ አስፈጻሚና የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማህበር መሪ የሆኑት አቶ ያሬድ ሞላ ለባንኮች የተሰፋን ልብስ ስንለብስ ኖረናል ሲሉ ኢንዱስትሪው የራሱን የተለየ ትኩረት እንደሚሻ ተናግረዋል::
ሌሎች ተሳታፊዎች በበኩላቸው የተቆጣጣሪው በቃትና ነጻነት/ገለልተኝነት ደካማ መሆኑን በተደጋጋሚ በመጥቀስ ዘርፉ እንዲያድግ ከተፈለግ ራሱን የቻለና ገለልተኛ ተቋም ማቋቋም የግድ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የኢንዱስትሪው ማነቆ ከሆኑት ህጎች መካክል ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ያወጣው የመድን ድርጅቶች 15 በመቶ የሚሆነውን የተጣራ ትርፋቸውን ለልማት ባንክ የተዘጋጀ ቦንድ እንዲገዙ የሚያስገድደው ህግ ይጠቀሳል። ህግ ከወጣበት ከመስከረም ወር ጀምሮ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያስነሳ ቆይቷል።
የዘርፉ ባለሙያዎች የሌሎች ሀገራትን ልምድ በመጥቀስ ራሱን የቻለ ተቋም መቋቋም ዘርፉን እንደሚያሳድግ ይሞግታሉ።
ከዋናው ማዕከላዊ ባንክ የተገነጠሉ ተቋማትን ማቋቋም በሌሎች ሀገራት የሚተገበር አሰራር ነው:: ለምሳሌ በኬንያ የኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን በ2006 እ.ኤ.አ. ተቋቁሞ በስራ ላይ ይገኛል::
በሀገሪቱ የሚገኙ 56 የመድን ድርጅቶችና 5 የጠለፋ መድን ድርጅቶች ይቆጣጠራል። በኢትዮጵያ ግን 18 የመድንና አንድ የጥለፋ መድን ድርጅት ብቻ በስራ ላይ ይገኛሉ
በኢትዮጵያ የመድህን አገልግሎት ሽፋን ደግሞ 3 በመቶ አካባቢ ሲሆን በኬንያ ደግሞ 10 እጥፍ ይሆናል።
የፋይናንስ ባለሙያ የሆኑት አብዱልመናን መሐመድ 20 የማይሞሉትን መድህን ድርጅቶች ለመቆጣጠር ራሱን የቻለ ተቋም እንደማያስፈልግና በብሔራዊ ባንክ ስር ያለውን አደረጃጀት ማጠናከር እንደሚሻል ይናገራሉ።
የኢንሹራንስ ዘርፉ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገት፣ በመድህን አገልግሎት አይነቶች ማነስና በህብረተሰቡ በኩል የሚስተዋለው የግንዛቤ እጥረት ዋነኛ ችግሮቹ እንደሆኑ ባለሙያው ያስረዳሉ።
“ችግሩን የቁጥጥር ጉዳይ ብቻ ባያደርጉት ጥሩ ነው” ይላሉ ባለሙያው።
እንደባንኮች ሁሉ የኢንሹራንስ ዘርፉም ለውጭ ድርጀቶች ክፍት እንደሚደረግ ይጠበቃል።
ዘርፉ በምን መልኩ መከፈት እንዳለበት መንግስት ምክረሃሳብ እንደሚቀበል ሚንስትሩ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]