ዋዜማ- አዲስ ስታንዳርድ የብየነ መረብ ሚዲያ ባለፉት ቀናት ዋና አዘጋጁ ታግቶ ተወሰዶ እንደነበር ፤ ቢሮው በፀጥታ ሀይሎች መበርበሩንና ንብረቶቹ መወሰዳቸውን እንዲሁም ለአስራ ስድስት ዓመታት ከተከራየው ቢሮ እንዲለቅ እየተገደደ መሆኑን አስታወቀ።

በሶስት ቋንቋዎች መረጃ የሚያቀርበው የአዲስ ስታንዳርድ ብየነ መረብ አስታሚ ጃከን አሳታሚ ድርጅት እንዳስታወቀው ሐምሌ 25 ቀን የሚዲያው ዋና አዘጋጅ ዮናስ ከድር በፀጥታ አካላት ታፍኖ ከ24 ስዓታት በኋላ ተለቋል። በተያዘበት ወቅት ረጅም የቃል ምርመራ እንደተደረገበት ጃከን አሳታሚ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ አስረድቷል።


ሐምሌ 26 ቀን ደግሞ የታጠቁ የፀጥታ አካላትና የደህንነት ሰራተኞች የሚዲያ ተቋሙ ቢሮ በመግባት የስቱዲዮ መገልገያዎችን፣ የቀረፃ መሳሪያዎችንና ሌሎች ንብረቶችን በግዳጅ መውሰዳቸውን የተወሰኑ እቃዎችን መስበራቸውን የድርጅቱ መግለጫ ያትታል። ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን አዲስ ስታንዳርድ ለአስራ ስድስት ዓመታት ከቆየበት የኪራይ ህንፃ ለቆ እንዲወጣ እንደተነገረውና ከድርጊቱ ጀርባ የፀጥታ ሀይሎች ግፊት እንዳለበት አብራርቷል።


ድርጅቱ ጉዳዩን በህጋዊ መንገድ በፍርድ ቤት ለመሟገት መዘጋጀቱንና የሚመለከታቸው የመግስት አካላት ለህግ ተገዢ እንዲሆኑ፣ ለመገናኛ ብዙሀን ነፃነት ጥበቃ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

አዲስ ስታንዳርድ በመንግስት የፀጥታ ኅይሎች ጥቃት ሲደርስበት ያሁኑ የመጀመሪያ አይደለም። ከወራት በፊት የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን የሚዲያውን የምዝገባ ፈቃድ መንጠቁ ይታወሳል። አዲስ ስታንዳርድ ያለአግባብ ተነጥቂያለሁ ያለውን ፈቃድ ለማስመለስ ስራውን ሳያቋርጥ በፍርድቤት ክስ አቅርቧል።


ጃከን አሳታሚ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት እንዲረጋገጥ ፣ አጥፊዎች እንዲለዩና ተጠያቂ እንዲደረጉ ለመንግስት ጥሪ አቅርቧል።

ባለፈው ሳምንት የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ህግ አላከበሩም የሰነምግባር ጥሰት ፈፅመዋል ላላቸው ለአሀዱ ራዲዮና ለአርትስ ቴሌቭዥን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ይታወሳል። [ዋዜማ]