ዋዜማ- ቅርሶችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ህጋዊ ስልጣን ቢሰጠውም በአዲስ አበባ ያሉ ታሪካዊ ህንፃዎችን በልማት ሰበብ እንዳይፈርሱ ለመከላከል ከሌሎች መንግስታዊ አካላት በቂ ትብብር እንዳልተደረገለት የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ለዋዜማ ተናግሯል።
የፌደራል ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዳይሬክተር አበባው አያሌው እንደነገሩን በልማት ሰበብ በአዲስ አበባ በሚገኙና የከተማዋን አመሰራረት የሚያሳዩ ፣ ታሪክና እሴትን የሚያንፀባርቁ በቅርስነት የተመዘገቡ ሕንፃዎች ላይ አደጋ ተጋርጧል።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመልሶ ማልማት መርሃግብር ረጃጅምና ዘመናዊ ህንጻዎችን ለመገንባት በሚል የከተማዋን ታሪክና ባህል በውስጣቸው የያዙ፣ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩና በቅርስነት የተመዘገቡ ህንጻዎች መፍረስ በከተማዋ የተለመደ አሰራር እየሆነ መጥቷል፡፡
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣንና የኢትዮጵያ የቅርስ ባለ አደራ ማህበር በከተማዋ ከ316 በላይ የሚደርሱ እድሜ ጠገብ ህንጻዎች በቅርስነት ተመዝግበው 130 ቅርሶች የምስክር ወረቀት ቢሰጣቸውም ምዝገባውም ይሁን የምስክር ወረቀቱ ከመፍረስ እያዳናቸው አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፌደራል ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው ባለስልጣኑ የቅርሶቹን ሁኔታ የመቆጣጠር ግዴታ ቢኖርበትም አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች መፍረስ ከባለቤትነት ጋር የተገናኘ ሲሆን በዚህም ቅርሶቹ እንድም በግለሰብ አልያም በኪራይ ቤቶች አስተዳደር ስር ቁጥጥር ስር መሆናቸው ቅርሶቹን ጠብቆ የማቆየት ሃላፊነቱን አዳጋች አድርጎበታል፡፡
በዚህም የተነሳ አሰራሩ የተምታታ በመሆኑ ቅርሶቹን የሚጠቀሙባቸው አካላት ሊያፈርሷቸው ሲያስቡ በቅርስ ጥበቃ አዋጁ መሰረት ለባለስልጣኑ እንዲያሳውቁ ቢጠበቅባቸውም እነዘህ አካላት የባላቤትነት ይዞታ አንኳ ሲቀይሩ ለባለስልጣኑ እንደማያሳውቁ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ለአልሚው የተሰጠውና “አፍርሰህ ስራ” የሚል ውል እሰካልተሰረዘ ድረስ ባለስልጣኑ ምንም ማድረግ የማይችልበት ደረጃ በመድረሱ ጉዳዩ ሊቋጭ የሚችለው ከተማ አሰተዳደሩን “ውሉን አቋርጥልኝ” ማለት ቢሆንም አስተዳድሩ ግን ይህን ሊያደርግ ባለመቻሉ ጉዳዩ ከባለስልጣኑ አቅም በላይ የሆነ ነው ብለዋል፡፡
ባለስልጣኑ በሚያደርጋቸው ጥረቶች የፋይናንስ ዘርፍ ከባቢ ተብሎ በፕላን ተይዞ ለፋይናንስ ድርጅቶች በተሰጠው ሰንጋ ተራ አካባቢ የነበረውን የሎምባርዲያ ህንጻ የቅርስ ባለአደራ ማህበር ህንጻው እንዳይፈረስ ክስ መስርቶ ባለስልጣኑ ጭምር ገብቶበት በፍርድቤት እስከ ሰበር ችሎት ድርስ ተሄዶ ቅርስነቱ እንዲጠበቅ ውሳኔ በማግኘቱ መጨረሻም ከመፍረስ መዳኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በሌለ በኩል በአራዳ ክፍለ ከተማ ባለስልጣኑ እየታገለባቸው የሚገኙ በርካታ የከተማውን ገጽታ የሚያሳዩ ቅርሶች እንደሚገኙ የገለጹት ዳይሬክተሩ እነዚህ ቅርሶች ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ክትትል እያደረጉ መሆኑንና ይህን ቅርስ አስጠብቆ ማቆየት ‹‹ተሰፋ የማንቆርጥበት ጉዳይ ነው›› ብለዋል፡፡
‹‹ስለ ልማት ሲነሳ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የልማት እንቅፋት መሆን የለበትም ፣ መሆንም አይፈለግም›› የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፤ ይሁን እጂን ባለስልጣኑ በአዋጅ በተሰጠው ሃላፊነትና ግዴታ መሰረት ቅርስን ማሰጠበቅ ስለሚኖርብት እና የማይለማ ቅርስ፣ ቅርስ ሊባል ስለማይችል አሁን ላይ ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበበር የሚለሙና የማይለሙ ቅርሶችን ተለይተው የሚለሙ ቅርሶች ቅርስነታቸው ተጠብቆ መልማት እንዲችሉ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቅርስ ባላአደራ ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ መቆያ ማሞ ለዋዜማ እንደገለጹት ቅርሶች ያለ አግባብ እንዲፈርሱ በሚወሰንበት ሰዓት የመጨረሻ ደረጃ እርምጃ እሰከሚባለው ክስ ድረስ በመሄድ ቅርሶቹ ተጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግ ተላልፈው ለባለሃት በሚሸጡበት ጊዜ ይዞታቸውንና ቅርስነታቸውን እንደጠበቁ እንዲታደሱ እንዲደረግ ለሚመለከተው አካል ደብዳቤ የመጻፍ ስራ ይሰራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ማህበር ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ተጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ በሚል በ1984 ዓ.ም የተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጂት ነው፡፡
ማህበሩ ከዚህ በፊት ጣይቱ ሆቴል ለባለሃብት ሲሸጥ የቅርስ ይዘታውን አንደተጠበቀ እንዲያለማው ለሚመለከተው የመንግስት አካል በደብዳቤ ማሳወቃቸውንና በዚህም ቅርሱ በጥሩ ሁኔታ እንዲቆይ ማድረጋቸውን አክለው ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ አቶ መቆያ “እየተጣረሰ አስቸገረን” የሚሉት ጉዳይ ልማት ይካሄዳል በሚል ምክንያት ብቻ ቅርሱ በራሱ ከለማ የተሻለ ሃብት እንደሚያስገኝ እየታወቀ በሁሉም ደረጃ በሚገኙ አካላት የግንዛቤ እጥረት በመኖሩ እንዲፈርሱ እየተደረገ መሆኑ ነው፡፡
ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ በቅርሶች ላይ ከፍተኛ ውደመትና የማፍረስ አዝማሚያ እየታየ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በተለይ መሃል የሚባሉ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች ችግሩ ተባሷል ብለዋል፡፡
ቅርስ ባስልጣን ቅርሶችን በዋነኝነት የሚመለከተው ተቋም ሆኖ እያለ ቤቶቹን አከራይቶና ለተለያየ አገልግሎት የሚያውላቸው የኪራይ ቤቶች በመሆኑ አሰራሩ ተስተካክሎ በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶችን የማሰተዳደሩ ጉዳይ ከኪራይ ቤቶች ይልቅ ባለስልጣኑ መሆን እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡
ከአጠቃላይ የቅርስ ጥበቃ ስራ ጋር በተገናኘ በፌደራል ባለስልጣኑና በክልሎች መካከል ያለውን አሰራር በተመለከተ የቅርስ ጥበቃ ዋና ዳይሬክሩር አበባው አያሌው እንደገለጹት አሁን በስራ ላይ ባለው አዋጅ ቅርሶችን በተመለከተ መመዝገብ፣ መጠገን ፣ መመርመር፣ መንባከብና የማልማት ተግባርና ሃላፊነት በአጠቃላይ ለባለስልጣን መስሪያቤቱ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይሁን አንጅ ይህ አሰራር ትክክል ባለመሆኑ አሁን ያለውን አሰራር ሊያሰተካክል የሚችል አዲስ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ መቅረቡንና ፤ ረቂቅ አዋጁ በ2015 ዓም ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ባለው አቅም ሁሉንም ቅርሶች መዝግቦም ተንከባቦም መጠበቅ ስለማይችልና አገር ለአንድ ባለስልጣን የሚስጥ ባለመሆኑ በቀጣይ አዋጁ ጸድቆ ወደ ስራ ሲገባ ለክልሎችም ተመጣጣኝ ሃላፊነት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
እየተሻሻለ ባለው አዋጅ መሰረት ቅርሶች በሁለት ተከፍለው ብሄራዊና ክልላዊ ቅርስ ተብለው እንዲከፈሉ የሚደረግ ሲሆን በዚህም ብሄራዊ ቅርሶች ለአስተዳደር እንዲመች ለባለስልጣኑ የሚተላለፉ ሲሆን ክልላዊ ቅርሶች ደግሞ ለክልሎች ተላልፈው እንዲተዳደሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ከዚያም አለፍ ሲል ዓለማቀፍ ቅርሶች ተብለው የሚቀመጡ ሊኖሩ እንደሚችሉ ዋና ዳይሬክተሩ ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡ [ዋዜማ]
Wazema Editors can be reached via email wazemaradio@gmail.com