ዋዜማ- መንግስት ከአንድ ወር በኋላ ሃምሌ 2015ዓ.ም በሚጀምረው አዲሱ የ2016 ዓ.ም በጀት አመት ምንም አይነት የመንግስት ሰራተኛ ቅጥር እንደማይፈጸም የገንዘብ ሚንስቴር አስታወቀ፡፡
የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ከጥቂት ቀናት በፊት በሚንስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የተላከውን የ2016 ዓ.ም የመንግስት በጀት አስመልክተው ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓም በፓርላማው ቀርበው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሚንስትሩ የ2015 ዓም የኢኮኖሚ አፈጻጸምና የበጀት ረቂቁን በተመለከተ ባቀረቡት ማብራሪያ የ2016 የመደበኛ በጀት በየመ/ቤቱ ያለውን አዲሱን አደረጃጀት ታሳቢ በማድረግ፣ የበጀት አጠቃቀም በቁጠባና በውጤታማነት ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ጠቅሰው በቀጣይ በጀት አመት አዳዲስ የመንግስት ሠራተኛ ቅጥር እንደማይኖር ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ በጀት መሆኑን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
መንግስት አዘጋጅቶ ባቀረበው የ2016 በጀት ዓመት ካቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት ውስጥ ለመደበኛ ወጪዎች 370.1 ቢሊዮን ብር ፣ ለካፒታል ወጪዎች 203.4 ቢሊዮን ብር፣ለክልሎች የሚሰጥ የበጀት ድጋፍ 214 ቢሊዮን ብር፣ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ 14 ቢሊዮን ብር ሆኖ ቀርቧል፡፡
የቀረበው በጀት የፊሲካል ሥርዓቱን ለማጠናከር የመንግስት ፋይናንስ አጠቃቀም ውጤታማነትን የሚያሻሽሉ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያሰፍኑ ሥርዓቶችን በመዘርጋትና በውጤታማነት ሥራ ላይ በማዋል የሀብት ብክነትን ለማስወገድና በጀትን በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችሉ ተግባራት በተጠናከረ ሁኔታ ይተገበራል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የምክር ቤት አባላት ሚንስትሩ ባለፈው አመት የ2015 በጀት ለምክርቤቱ ሲያቀርቡ በተመሳሳይ አዲስ ቅጥር እንደማይፈጸም መናገሩን አውስተው መንግስት ለአዳዲስ ምሩቃን የስራ እድል መፍጠር ካልቻለ የመንግስት ቅጥር ለሚፈልጉ ተመራቂዎች እጣ ፋንታ ምንድን ነው የሚል ቅሬታ አንስተዋል፡፡
በየአመቱ አዳዲስ የስራ እድል አይፈጠርም በሚል የሚቀጥል ከሆነ ተመራቂዎችና ዜጎች ተስፋ በመቁረጥ ለአላስፈላጊ ስደት እንዳይዳረጉ ስጋት አለኝ ሲሉ አንድ የምክርት አባል ቅሬታ አሰምተዋል፡፡ የምክርት አባሏ አክለውም ይህ አሰራር የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሚሆን ጠቅሰው‹‹ ምስኪን አርሶ አደሮች ብዙ መስዋት ከፍለው ነው ልጆቻቸውን አስተምረው የሚያወጡት ፣ በመንግስት መስሪያ ቤት በየአመቱ ይቀጠሩ የሚል እምነት ባይኖረኝም በምን መልኩ ነው አሁን የተማሩ ምሁራንን ወደ ስራ ማስገባት እና ማሰማራት የምንችለው ›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህርና የምክርቤት አባሉ ዶ.ር ዘገየ ሙሉየ ሲናገሩ ለዜጎቹ ስራ መፍጠር አንዱ የመንግስት ሃለፊነት መሆኑን ጠቅሰው ስራ ባለመፍጠር የትም ሊደረስ አይችለም ብለዋል፡፡ ይህን በመዝጋት ዘላቂ የሆነ ስራ መስራት አይቻለም ስለዚህ መንግስት የገቢ አሰባሰቡን ስርዓት በማስተካከልና የመንግስትን ወጭ በተገቢው ቦታ በማዋል ጠበቅ ተደርጎ ካልተሄደ በቅርብ ጊዜ ከችግር ሊወጣ አይችለም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በመንግስትና በግል ዩንቨርሰቲዎችና ኮሌጆች በየአመቱ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች እየተመረቁ ይወጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ የስራ እድል የማግኘት ሁኔታው አስከፊ ከመሆን አልፎ መንግስት በአገር ውስጥ የሚመረቁ ተማሪዎችን ከውጭ አገራት መንግስታት ጋር በመነጋገር በተለያዩ የስራ መስኮች ወደ ውጭ አገራት ስራ ስምሪት ለመላክ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በየመድረኩ ሲያነሱ ይደመጣል፡፡
በቅርቡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የስምንት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ሲቀርቡ በስምንት ወራት ውስጥ ለ2.6 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለሁለት ሚሊዮን ዜጎች መፍጠሩን ገልጸው፡ ነገር ግን በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ስራ አጥ ዜጎች መመዝገባቸውን ተናግረው ነበር፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት የትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በፓርላማው ቀርበው ባደረጉት ንግግር በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ተመራቂ ተማሪዎች 42 በመቶ የሚሆኑት ስራ አጥ መሆናቸውን አስታውቀው ነበር፡፡
የገንዘብ ሚንስትሩ ከምክርቤቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ የኢትዮጵያ የመንግስት ሰራተኛ ቁጥር እጂግ በጣም ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው በመላው አገሪቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰራተኛ አንዳለ ጠቅሰዋል፡፡
ውጤታማነትና የቁጥር ጉዳይ አብሮ በንጽጽር መታየት አለበት ያሉት ሚንስትሩ በቅርቡ የተዘጋጀ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ፕሮግራም መኖሩንና፣ ሪፎርሙ እንደየ ክልሎችና እንደየተቋማት ሁኔታ እየተመነዘረ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል፡፡
‹‹እንኳን አዳዲስ ሰራተኛ ለመቅጠር ቀርቶ ያሉትን ሰራተኞች ጭምር የመዋቅር ማስተካከያ አድርገናል›› ያሉት ሚንስትሩ የተለያዩ ተቋማት ያላቸውን ዲፓርትመንት መቀነሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ስራ እድል መፈጠር አለበት የሚለው የሚያስማማ ቢሆንም ‹‹መንግስት የስራ እድል መፍጠሪያ ማሽነሪ አይደለም፣›› በተቻለ መጠን የግሉ ዘርፈን ኢንቨስትመንት በማሳደግ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡ [ዋዜማ]