ዋዜማ- በትግራይ ክልል መቐለ ቅርንጫፍ የፓስፖርት አገልግሎት መቋረጡን ተከትሎ፤ ተገልጋዮች ለከፋ እንግልት መጋለጣቸውን ዋዜማ ሰምታለች፡፡

ከሁለት አመታት በላይ በዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ፤ የአገልግሎቱ የመቐለ ቅርንጫፍ ለሶስት አመታት ገደማ ተቋርጦ የቆየ ሲሆን፤ የፕሪቶሪያው ግጭት የማቆም ስምምነት በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ከተፈረመ 1 አመት ከ 8 ወራት በኋላ፤ ሰኔ 11 ቀን፤ 2016 ዓ.ም በድጋሚ ተጀምሮ ለሁለት አመታት ገደማ ሲሰራ ቆይቷል፡፡  ሆኖም፤ ካለፈው የካቲት ወር አጋማሽ ወዲህ ግን በፌደራሉ መንግስት እና በህወሃት መካከል የተካረረውን ውጥረት ተከትሎ የአገልግሎቱ መቐለ ቅርንጫፍ አገልግሎት መስጠት አቁሟል፡፡ አገልግሎቱ በየጊዜው ፓስፖርታቸው የደረሰላቸውን ተገልጋዮች ስም ዝርዝር እንዲሁም የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ከሚያሳውቅባቸው ቅርንጫፎች ዝርዝር ውስጥ የመቐለ ቅርንጫፉን አለማካተቱንም ለመረዳት ተችሏል፡፡ በቅርቡም በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው የፓስፖርት አገልግሎት መስጫ ከተሞች ዝርዝር ውስጥ መቐለ ከተማን ጨምሮ ሌላ የትግራይ ክልል ከተማ አልተካተተም።

ቅርንጫፉ በመዘጋቱ የፓስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ መገደዳቸውን የገለጹልን ተገልጋዮች፤ ይህም ለከፍተኛ ወጪ እንደዳረጋቸው አስረድተዋል፡፡

ከትራንስፖርት ወጪና ከሰአት ብክነት በተጨማሪ፤ የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት፤ ከትግራይ ክልል የሚቀርቡ የፓስፖርት ማመልከቻዎችን ‹‹የጊዜያዊ አስተዳደር ማኅተም ካላረፈባቸው አልቀበልም›› በማለቱ ያልጠበቁት እንግልት እንደገጠማቸው ገልጸዋል።

በቀጠሯቸው ቀን እንደ ማንነት ማረጋገጫ የሚያቀርቧቸው የልደት ካርድ እና የነዋሪነት መታወቂያ በፈረሰው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ማኅተም የተረጋገጡ መሆን ይጠበቅባቸዋል እንደሚባሉ ተናግረዋል። በአንጻሩ ‹‹የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት›› የሚል ማኅተም ያረፈባቸውን ሰነዶች፤ አገልግሎቱ እየተቀበለ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

የእነ ደብረጽዮን አስተዳደር …..

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የመቐለ ቅርንጫፍ መዘጋቱን ተከትሎ፤ ፓስፖርት ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ የሚመጡት ተገልጋዮች፤ በአብዛኛው አዲስ ፓስፖርት ለማውጣትም ሆነ ለእድሳት ማመልከቻቸውን የሚያቀርቡት አዲስ አበባ ለሚገኘው የአገልግሎቱ ዋና መሥሪያ ቤት ነው።

ማመልከቻቸውን ካቀረቡ በኋላ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው አሻራ ለመስጠት ሲቀርቡ፤  የልደት ካርድ እና የነዋሪነት መታወቂያቸው በኃይል ሥልጣን በተቆጣጠረው የእነ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል አስተዳደር የተሰጠ ከሆነ ተቀባይነት እንደሌለው ተገልጾላቸው እንደሚመለሱ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅትም በፈረሰው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተረጋገጡ የማንነት ማረጋገጫ ሰነዶች ብቻ እያስተናገዱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ለእንግልት መዳረጋቸውን የሚገልጹት ተገልጋዮች ፤ ‹‹ለከፍተኛ ወጪ፣ የጊዜ ብክነትና እንግልት መጋለጣችን ሳያንስ፤ ሥልጣን የተቆጣጠሩ አካላት በፈጠሩት ሽኩቻ እየተቸገርን ነው›› ብለዋል፡፡ መብታቸውን ለፖለቲካ ፍጆታ እንደማዋል እንደሚቆጠር አክለዋል፡፡

የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ማረጋገጫ ከተሰጠው ሰነድ ውጪ እንደማይቀበል ሲገልጽ፤ ሥልጣን በኃይል የተቆጣጠረው በህወሓት የሚመራው የክልል አስተዳደር በበኩሉ ‹‹ጊዜያዊ አስተዳደር የሚባል መዋቅር እንደሌለ ይገልጻል፡፡ በዚህ ውዝግብ መካከል ግን የፓስፖርት አገልግሎትን ማግኘት የሚፈልጉ ተገልጋዮች፤ ለእንግልት መዳረጋቸውን በመጥቀስ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ልዩ የማንነት ማረጋገጫ ጥያቄዎች

አገልግሎቱን በአዲስ አበባ ለማግኘት በዋናው መስሪያ ቤት ማመልከቻቸውን ያቀረቡ ተገልጋዮች፤ ከመደበኛው የሰነድ መስፈርት ውጭ እንደሚጠየቁ ገልጸውልናል፡፡ መደበኛው የፓስፖርት አገልግሎት የሰነድ መስፈርት፣ የልደት ካርድ፣ የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ እና ብሄራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ቢሆንም፤ ከክልሉ የመጡ ተገልጋዮች ግን አሻራ ለመስጠት ሲቀርቡ፣ የእናት ወይም አባት መታወቂያ ቅጂ እንዲያቀርቡ እንደሚጠየቁ አብራርተዋል፡፡በዚህም አንዳንድ ተገልጋዮች መደበኛውን የማንነት ማረጋገጫ ሰነድ ቢያቀርቡም፤ የወላጆቻቸውን የነዋሪነት መታወቂያ ባለማቅረባቸው ማመልከቻቸው ውድቅ የተደረገባቸው ተገልጋዮች መኖራቸውን ሰምተናል፡፡

እንደተጨማሪ የማንነት ማረጋገጫ የወላጅ መታወቂያ ከማቅረብ ባሻገር፣ አሻራ በሚሰጡበት ወቅት ከአገልግሎቱ ሰራተኞች ‹‹ጠንከር›› ያሉ ተከታታይ የቃል ጥያቄዎች እንደሚቀርቡላቸው አስረድተዋል፡፡

ተቋሙ ምን ይላል?

ተጨማሪ የማረጋገጫ ሰነዶች የሚጠየቁበትን ሁኔታ በሚመለከት ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ሰራተኛ፤ የውጪ ሀገር ዜጎች የኢትዮጵያን ፓስፖርት በአቋራጭ ለማግኘት የተለያዩ ስልቶችን እንደሚጠቀሙ ጠቅሰው፤ ከእነዚህም መካከል የአዲስ አበባ ወይም ሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎችን የነዋሪነት መታወቂያ በህገ-ወጥ መንገድ በመያዝ የኢትዮጵያን ፓስፖርት በቀላሉ የሚያገኙበት ሁኔታ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ሆኖም፤ ከ2013 ዓ.ም አጋማሽ ወዲህ ግን የኤርትራ ዜጎች እና የትግራይ ተወላጆች፣ የሶማሊያ ዜጎች እና የሶማሌ ክልል ተወላጆች እንዲሁም የአፋር ተወላጆች እና የጂቡቲ ዜጎች የቆዳ ቀለም፣ የባህልና የቋንቋ መመሳሰል ያላቸው በመሆኑ፤ ይህንን ለመለየት የተለያዩ የአሰራር ስርአቶች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ የአገልግሎቱ የመቐለ ቅርንጫፍ አገልግሎት መስጠት ማቆሙን እንዲሁም ተቋሙ በጊዜያዊ አስተዳደር ያልተረጋገጠ ሰነድ አልቀበልም ስለማለቱ ግን ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ዋዜማ በጉዳዩ ዙሪያ የአገልግሎቱን ከፍተኛ አመራሮች ለማነጋገር ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ ብታደርግም አልተሳካም፡፡ [ዋዜማ]