ዋዜማ- በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ 34ኛ ቀን ውሎ በጋራ ማረጋገጫ ቡድን ደረጃ የተደራጁ ምክረ ሀሳቦች ለየሥራ ቡድኖች ቀርበዋል። ስምንቱን የሥራ ቡድኖች የወከሉ 120 የጋራ ማረጋገጫ ቡድን አባላት ከነሐሴ 07 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሥራ ቡድኖችን ምክረ ሀሳቦች በማናበብ ወጥ ምክረ ሀሳቦችን የማደራጀት ሥራ ሲያከናወኑ መቆየታቸውን የገለጡ ሲሆን፤ ከየሥራ ቡድኑ የተወከሉ 15 የአጠናቃሪ ቡድን አባላት፤ ከሌሎች ቡድኖች ጋር የተናበበና የተስተካከለ ነው ያሉትን የቡድናቸውን ምክረ ሀሳብ ለተመካካሪዎች ማቅረባቸውን ሰምተናል። የሥራ ቡድኖች አባላት በቀረበላቸው የተጠናቀረ ምክረ ሀሳብ ላይ አስተያየት መስጠታቸውን የጠቆሙ ተሳታፊዎች፤ ምክረ ሀሳቡ እንዲቀርብ የተደረገበት ሁኔታ ላይ ጥያቄ መነሳቱን ጠቁመዋል። 

የኮሚሽኑ የጋራ ማረጋገጫ ቡድኑ ያጠናቀረውን ምክረ ሀሳብ ማክሰኞ ነሐሴ 12 ቀን ለየሥራ ቡድኖች እንደሚያቀርብ ማሳወቁን ዋዜማ መዘገቧ የሚታወስ ሲሆን፤ ምክረ ሀሳቡ የቀረበው ነሐሴ 11 ቀን ከ10 ሰዓት ጀምሮ መሆኑን ያነሱ ተመካካሪዎች፤ የሥራ ቡድኖች ምልዓተ ጉባኤ ባለተሟላበትና መረጃ ባለማግኘታቸው ምክንያት በምክክር አዳራሾች ያልተገኙ ተመካካሪዎች በርካታ በሆኑበት ሁኔታ ውስጥ ምክረ ሀሳቦች እንዲቀርቡ መደረግ የለበትም የሚሉ ቅሬታዎች ማቅረባቸውን ሰምተናል። ኮሚሽኑ ምክክሩን እንዲያስተባብሩ የመደባቸው ባለሙያዎች ግን ተመካካሪዎች ያነሱትን የአካሄድ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ “ከተቀመጠልን አቅጣጫ መውጣት አንችልም” በሚል ሂደቱ እንዲቀጥል ማድረጋቸውን ምንጮች ጠቁመዋል። 

የጋራ ማረጋገጫ ቡድኑ ምክረ ሀሳቦች

120 አባላት ያሉት የጋራ ማረጋገጫ ቡድኑ፤ 34 አባላት ያሉት ኮሚቴ በማቋቋም የሥራ ቡድኖች ምክረ ሀሳቦች እንዲናበቡና እንዲጣጣሙ ማድረጉን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የገለጠ ሲሆን፤ ኮሚቴው እንዲናበብና እንዲጠናቀር ያደረገው ምክረ ሀሳብ ለ120ው የቡድኑ አባላት ከቀረበ በኋላ ለየሥራ ቡድኖቹ   እንዲነበብ ተደርጓል። በተለያዩ ቡድኖች የተነሱ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ምክረ ሀሳቦች በቀጥታ ወደሚመለከታቸውና በተሻለ ሁኔታ ተገልጠውበታል ወደተባሉበት የሥራ ቡድን ምክረ ሀሳብ እንዲሰባሰቡ መደረጋቸውንም ሰምተናል። የሥራ ቡድኖች አማራጭ ያቀረቡባቸው ምክረ ሀሳቦች በዚህኛው ሂደትም አማራጭ ሆነው እንዲቀጥሉ መደረጉን የገለጡልን ምንጮች፤ በሥራ ቡድኖች በዝርዝር ቀርበው የነበሩ ጉዳዮች እንዲያጥሩና ዝርዝሩ በአባሪ እንዲያያዝ አቅጣጫ መቀመጡን ነግረውናል።

መነጋገሪያ ሆኖ የቀጠለው የአዲስ አበባ ጉዳይ 

የጋራ ማረጋገጫ ቡድኑ የፌደራል ከተሞች ጉዳይን እየመከረበት ለሚገኘው የሥራ ቡድን፣ ያናበበውን ምክረ ሀሳብ ያቀረበ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ሕጋዊ አቋም ጉዳይ አሁንም ሁለት አማራጭ ምክረ ሀሳቦችን ይዞ መቅረቡን ምንጮች ነግረውናል። አዲስ አበባ ተጠሪነቷ ለፌደራል ሆኖ ራሷን በራሷ እንድታስተዳድር የቀረበው ምክረ ሀሳብ ቀዳሚ ሲሆን፤ ከተማዋ ተጠሪነቷ ለፌደራል ሆኖ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ እንድትሆን የቀረበው ምክረ ሀሳብ ደግሞ በሁለተኝነት መመዝገቡን ሰምተናል። በሁለተኛው አማራጭ ምክረ ሀሳብ ዙሪያ ጉልህ የሀሳብ ልዩነት መስተዋሉ በተጠናቀረው የምክረ ሀሳብ ሰነድ ላይ መገለጡን የነገሩን ምንጮች፤ ሁለቱ ምክረ ሀሳቦች እልባት ሳይሰጣቸው እስከ መጨረሻው የምክክር ሂደት እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

ለታዛቢዎች የተከለከለው የአጠናቃሪዎች ስብሰባ

የጋራ ማረጋገጫ ቡድኑ ያቋቋመውና 34 አባላት ያሉት ኮሚቴ ያካሄደው ምክረ ሀሳቦችን የማደራጀት ሂደት ለታዛቢዎች ዝግ መደረጉን ዋዜማ ሰምታለች። ሌሎች ሂደቶችን እየታዘቡ የሚገኙት የተለያዩ ሀገር በቀል ድርጅቶች ያሰማሯቸው ታዛቢዎች ሂደቱን ለመታዘብ ጠይቀው እንደነበር የነገሩን ምንጮች፤ ኮሚሽኑ ሂደቱን እንዲታዘቡ ማድረግ የሚያስችል ፍቃድ አለመስጠቱን ገልጠዋል። ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም የምክክር ሂደቱን በመታዘብ ላይ የሚገኙ ታዛቢዎች “ምስጢር አውጥተዋል” የሚል ወቀሳ ማቅረቡን የገለጡልን ምንጮች፤ በ34 አባላት የተካሄደው አጀንዳ የማደራጀት ሂደት በዝግ እንዲካሄድ የወሰነበትን ምክንያት አለማሳወቁን ነግረውናል። በ34ቱ የቡድኑ አባላት የተደራጀው ምክረ ሀሳብ ለ120ው የጋራ ማረጋገጫ ቡድን አባላት ሲቀርብ ግን ታዛቢዎች ሂደቱን እንዲከታተሉ መፈቀዱን ሰምተናል።

የምክክር ሂደቱን እየታዘቡ የሚገኙ ተቋማት ሪፖርታቸውን ለኮሚሽኑ ቢያቀርቡም ለመገናኛ ብዙኃን ግን መግለጫ እንዳይሰጡ በኮሚሽኑ አቅጣጫ መሰጠቱን የነገሩን ምንጮች፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችም ታዛቢዎችን አነጋግረው ዘገባ እንዳይሰሩ ትዕዛዝ መተላለፉን ጠቁመዋል። ከታዛቢዎች በተጨማሪም፤ ኮሚሽኑ በአመካካሪነት ያሰማራቸው ባለሙያዎችን እንዲሁም እስካሁን ሥራ ያልጀመረው የስምምነት ግብረ ኃይል አባል የሆኑ “አስታራቂ ሽማግሌዎችን” በማነጋገር ዘገባዎች እንዳይሠሩ ገደብ ማስቀመጡን ሰምተናል።

ሥራ አልባ የሆነው የክልል ተወካዮች ጉባኤ

ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ ውስጥ ቁልፍ ሚና ይኖራቸዋል ሲል ይፋ ካደረጋቸው አደረጃጀቶች መካከል አንዱ የሆነው የክልል ተወካዮች ጉባኤ እስካሁን ድረስ ስብሰባ አላካሄደም። ኮሚሽኑ በሥራ ቡድን ደረጃ የሚፈለገውን 70 በመቶ የድጋፍ መጠን ማግኘት ያልቻሉ ጉዳዮች፣ የማንነት ወይም የህልውና አደጋን የሚመለከቱ ጉዳዮች እንዲሁም ቢያንስ ሦስት ክልሎች በጉባኤው እንዲታዩ ጥያቄ የሚያቀርቡባቸው ጉዳዮች በዚህ ጉባኤ እንደሚታዩ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፤ 336 አባላት የተመረጡለት ጉባኤ እስካሁን ሥራ አልጀመረም። ኮሚሽኑ በሥራ ቡድን ደረጃ የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦች በቡድኑ 75 በመቶ አባላት የድጋፍ ድምጽ ካገኙ፣ አልያም አስማሚ ግብረ ኃይል ጣልቃ ገብቶ በሚካሄድ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት 70 በመቶ ድምጽ የሚያገኙ ከሆነ ወደ ቀጣዩ ሂደት እንደሚሸጋገሩ፤ ይህ መሆን ካልቻለ ደግሞ ወደ ክልል ተወካዮች ጉባኤ እንደሚመሩ የሚያመላክት አሠራር አስተዋውቆ የነበረ ቢሆንም፤ ይህ አሠራር ተግባራዊ ባለመደረጉ ምክንያት ወደ ጉባኤው የሚመራ ጉዳይ እንዳይኖር ማድረጉን ምንጮች ነግረውናል። 

የጋራ ማረጋገጫ ቡድን ያደራጀው ምክረ ሀሳብ ለጠቅላላ ጉባኤ ከመቅረቡ በፊት በክልል ተወካዮች ጉባኤ እንደሚታይ ኮሚሽኑ ገልጦ የነበረ ሲሆን፤ የጉባኤው አባላት ግን እስካሁን ከሂደቱ ጋር በተያያዘ ከኮሚሽኑ የስብሰባ ጥሪ እንዳልደረሳቸው ዋዜማ አረጋግጣለች። ኮሚሽኑ ጉባኤውን ሊሰበስብ የሚችለው ይህንን ሂደት ለማሟላት ብቻ ሊሆን እንደሚችል የገለጡት የዋዜማ ምንጮች፤ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤውን በቶሎ ለመቋጨት በተላለፈው አቅጣጫ ምክንያት ጉባኤው ያለ ሥራ የሚበተንበት ዕድል ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጉባኤው እንዲጠናቀቅ የተላለፈው ውሳኔ

የምክክሩ ሂደት በተቀመጠለት የጊዜ ዕቅድ መሠረት መካሄድ ካለመቻሉ ጋር ተያይዞ ኮሚሽኑ አስቀድሞ ካሳወቀው የ35 ቀናት ዕቅድ አንጻር ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሞ የነበረ ቢሆንም፤ ጉባኤው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ መቀመጡን ምንጮች ነግረውናል። በጥቃቅን፣ በንዑስ፣ በስልታዊ እና በሥራ ቡድኖች ደረጃ የተካሄዱ የምክክር ሂደቶች ሰፊ ጊዜ የወሰዱ ሲሆን፤ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እንዳይካሄድ መወሰኑ በምክክር ሂደቱ ሚና እንደሚኖራቸው ተነግሮላቸው የነበሩት የስምምነት ግብረ ኃይል እና የክልል ተወካዮች ጉባኤ ወደ ሥራ እንዳይገቡ ማድረጉን ሰምተናል። 8 ቀናት እንደሚፈጅ ተነግሮለት የነበረው የጋራ ማረጋገጫ ሥርዓትም በአምስት ቀናት ብቻ እንዲጠናቀቅ ተደርጓል። 

የኮሚሽኑ ምክር ቤት የምክክር ጉባኤውን ቶሎ ለማጠናቀቅ መወሰኑን የጠቆሙት ምንጮች፤ በምክክር ስልቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነውን የ12 ቀናት ጊዜ እንደሚወስድ ታቅዶለት የነበረው የክልል ተወካዮች ጉባኤ እንዲታጠፍ መደረጉን ገልጠዋል። የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ ነሐሴ 11 ቀን በሰጡት መግለጫ፤ የምክክሩ ምክረ ሀሳቦች ነሐሴ 13 ቀን ይካሄዳል ባሉት ጠቅላላ ጉባኤ ይጸድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጠዋል። ኮሚሽነሯ ይህንን ቢሉም ጠቅላላ ጉባኤው ሁለት ቀናት ይፈጃል የሚል ዕቅድ መያዙን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል። 

በአብን መግለጫ የተጠቀሱት ኮሚሽነሮች

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በምክክሩ ሂደት ዙሪያ ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ፤ ኮሚሽኑ ምላሽ መስጠቱን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ ፓርቲው ለኮሚሽኑ ማስተባበያ በሰጠው ምላሽ፤ “ሁለት ኮሚሽነሮች በፌደራል ከተሞች አጀንዳ ውስጥ እጃቸውን በማስገባት የተሳታፊዎችን ፍላጎት ለማስቀየር እና ተጽዕኖ ለማሳደር ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል።”  ብሏል። የሁለቱን ኮሚሽነሮች ተግባር በሚመለከት ከአብን በተጨማሪ ሌሎች ፓርቲዎችም ለኮሚሽኑ ቅሬታ ማቅረባቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ ኮሚሽኑ በጉዳዩ ዙሪያ የሰጠው ግልጽ ምላሽም ሆነ የወሰደው እርምጃ የለም።

ከዕይታ የራቁት ዋና ኮሚሽነር

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ከሰሞኑ በተካሄዱ የምክክር ሂደቶች ውስጥ አለመታየታቸውን ምንጮች ነግረውናል። ዋና ኮሚሽነሩ ለመገናኛ ብዙኃን ለመጨረሻ ጊዜ መግለጫ የሰጡት ነሐሴ 04 ቀን ሲሆን፤ ኮሚሽኑ ነሐሴ 06 ቀን ባካሄደው የሥራ ግምገማ ላይ ተገኝተው ነበር። በዚሁ ዕለት ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ለ13 ደቂቃዎች የዘለቀ የቀጥታ ሥርጭት ቆይታ አድርገዋል። ሀሙስ ነሐሴ 07 ቀን በተካሄደው የጋራ ማረጋገጫ ቡድን አባላት ምርጫ ላይ በመሪ ኮሚሽነርነት እየተከታተሉት በሚገኘው በሀገር ግንባታ አጀንዳ ዙሪያ በሚመክረው የሥራ ቡድን ተገኝተው ሂደቱን መመልከታቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ ከዛ ጊዜ በኋላ ባሉ የምክክር ሂደቶች አለመታየታቸውን ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ ነሐሴ 07 እና ነሐሴ 11 ቀን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጣቸው መግለጫዎች ላይ ዋና ኮሚሽነሩ ያልተገኙ ሲሆን፤ በሁለቱ ቀናት የተሰጡ መግለጫዎች ላይ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ቦታቸውን ተክተዋል። የኮሚሽኑ ምክር ቤት ለመገናኛ ብዙኃን የሚሰጡ መግለጫዎችን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አልያም ኮሚሽነር መሀሙድ ድሪር እንዲሰጡ ውሳኔ ማሳለፉን ያስታወሱት ምንጮች፤ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ መግለጫዎችን እንዲሰጡ የተደረገበት ምክንያት ግን ግልጽ አለመደረጉን ጠቁመዋል። ዋና ኮሚሽነሩ በሰጧቸውና በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በቀጥታ ሥርጭት በተላለፉ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ባነሷቸው “አንዳንድ” ነጥቦች ዙሪያ ተቃውሞ ያላቸው ኮሚሽነሮች እንዳሉ የነገሩን ምንጮች፤ የኮሚሽኑ ምክር ቤት ዋና ኮሚሽነሩ “ለጊዜው” መግለጫ እንዳይሰጡ መወሰኑን ነግረውናል። 

ነሐሴ 11 ቀን በሀገር ግንባታ አጀንዳ ዙሪያ በሚመክረው የሥራ ቡድን፣ በጋራ ማረጋገጫ ቡድን የተደራጀው ምክረ ሀሳብ ሲቀርብም ዋና ኮሚሽነሩ አለመገኘታቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት በሥራ ቡድኑ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። በንግግራቸውም ዋና ኮሚሽነሩ መገኘት አለመቻላቸውን ከመጠቆም ባሻገር፣ ያልተገኙበትን ምክንያት አለመጥቀሳቸውን ሰምተናል። [ዋዜማ]