ዋዜማ- የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ አገልግሎት እስከ 60 ሺህ ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ዋዜማ ባደረገችው ክትትል ተረድታለች።
በመዲናዋ አዲስ አበባ የክፍያ ደረጃው እንደየ ክፍለ-ከተማዎቹ የሚለያይ ሲሆን፤ በአመዛኙ ከ30 ሺህ ብር በላይ እንደሚከፈልበት ታውቋል። አገልግሎቱ “አስቸኳይ” ተብሎ ጊዜው ከአንድ ሳምንት ያጠረ ከሆነ እሰከ 60 ሺህ ብር ይጠየቅበታል።
ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ለዚሁ ሕገ-ወጥ አገልግሎት፣ ከ15 ሺህ ብር ጀምሮ ይከፈል እንደነበር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ነግረውናል። የመታወቂያ አገልግሎት አሠራሩ ወደ ዲጂታል ስርዓት ሲቀየር ግን፤ የሚጠየቀው ገንዘብ መጠን እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።
ይኸው በሕገ-ወጥ መንገድ የነዋሪነት መታወቂያን የመስጠት ተግባር ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መስፋፋቱን ዋዜማ ባደረገችው ክትትል ተረድታለች። ቀደም ሲል የነበረው መሰል አሰራር ወደ ወረዳዎች መዋቅር መውረድ መጀመሩን ተከትሎ ለድርጊቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ምንጮች ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ በቅርቡ የመዲናዋን የነዋሪነት መታወቂያ አገልግሎት በወረዳ ደረጃ መስጠት መጀመሩን ገልጧል። ይኸው በወረዳ ደረጃ “መሰጠት ጀምሯል” የተባለው አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ባይጀመርም፣ በተጀመረባቸው ወረዳዎች ላይ ግን ሕገ-ወጥነቱ መባባሱን ሰምተናል።
በ10 ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ተከፍሎበት የሚሰጠው የነዋሪነት መታወቂያ፤ ህገ-ወጥ ቢሆንም፤ በድርጊቱ የተሰማሩ የኤጀንሲው ሰራተኞች በየደረጃው የፈጠሩትን ሰንሰለት በመጠቀም፤ መረጃው በመዝገብ እንዲሁም በዲጂታል ስርዓት ውስጥ እንዲካተት በማድረግ ህጋዊነትን የማላበስ ተግባር እንደሚፈፀሙም ለማረጋገጥ ተችሏል።
በሕገወጥ መንገድ የሚሰጠው መታወቂያ፤ የጥቅም ተጋሪ በሆኑ ሠራተኞች መደበኛ የዲጂታል ስርዓት ላይ ስለሚሰፍር ሕጋዊ ሆኖ እነደሚያገለግል የገለጡት የዋዜማ ምንጮች፤ የኤጀንሲው ሠራተኞች መታወቂያውን ሕጋዊ ለማድረግ የሚጠቀሙበት ስልት፣ የገንዘብ ከፋዩን ግለሰብ ሥም ህጋዊ መኖሪያ ቤት እና የነዋሪነት መታወቂያ ባላቸው ነዋሪዎች መዝገብ ውስጥ “የቤተሰብ አባል” በሚል እንዲካተቱ ማድረግ ነው።
ይህ ድርጊት የሚፈጸመው ህጋዊ በሆነ መንገድ ተመዝግበው ተጨማሪ ሰው በቤተሰብ መዝገባቸው ውስጥ እንዲካተት በሚፈቅዱ ነዋሪዎች እና በኤጀንሲው ሠራተኞች መካከል በሚደረግ ስምምነት መሆኑን ዋዜማ ባደረገችው ክትትል አረጋግጣለች። በስምምነታቸው መሰረት የክፍያውን ገንዘብ እንደሚጋሩ ምንጮች ነግረውናል። በአንዳንድ ሁኔታዎችም በህጋዊ መንገድ የተመዘገቡ ነዋሪዎችን ያለ ምንም ክፍያ ትብብር እንዲያደርጉ የሚጠየቁበት ሁኔታ እንዳለም ገልፀውልናል።
በዚህ ሰንሰለት ውስጥ በህገወጥ መንገድ የነዋሪነት መታወቂያ ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎችን የሚያገናኙ እና አሠራሩን የሚያሳልጡ ፥ በየክፍለከተማው የሚንቀሳቀሱ ደላሎች መኖራቸውን ዋዜማ ባደረገችው ክትትል ተረድታለች።
አገልግሎቱን በሕገወጥ መንገድ የመስጠት ድርጊት የተስፋፋው፤ ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የጸጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ጭምር መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል። ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሱ ሰዎች፣ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሆኖ በነፃነት ለመንቀሳቀስ እና የተለያዩ አገልግሎቶች በቀላሉ ለማስፈጸም በማሰብ፤ በሕገ-ወጥ መንገድ መታወቂያ ማውጣትን እንደሚመርጡ ገልፀውልናል።
ከዚህ ቀደም ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ እና ነዋሪነታቸውን ወደ አዲስ አበባ የቀየሩ ሰዎች የነዋሪነት መታወቂያ ለማግኘት ወራትን ለመጠበቅ የሚገደዱ ሲሆን፤ ነዋሪነታቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ በኋላም፤ ከዚህ ቀደም ይኖሩበት ከነበረው አካባቢ የመሸኛ ደብዳቤ አቅርበው፤ ከክልል ተጣርቶ እስከሚመጣ ድረስ ረጅም ጊዜ ይጠብቃሉ።
በመዲናዋ የነዋሪነት መታወቂያ አገልግሎት ላይ ሕገወጥ አሰራር መኖሩን፣ ኤጀንሲው በተደጋጋሚ መግለፁ ይታወሳል። አገልግሎቱን ለብልሹ አሰራር ዳርገዋል ያላቸውን ሠራተኞቹን “እጅ ከፍንጅ” ጭምር ይዞ ተጠያቂ ማድረጉን ቢገልፅም፤ አገልግሎቱ አሁንም ከሕገ-ወጥ አሰራር አለመውጣቱን ማረጋገጥ ችለናል። [ዋዜማ]
