ዋዜማ- ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በሥራ ቡድን ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘውን የምክክር ሂደት የሚያጠናቅቅበት ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አራት የሥራ ቡድኖች ተጠናቅረው በቀረቡ የአጀንዳ ምክረ ሀሳቦች ዙሪያ መግባባት ላይ መድረሳቸውን በተዘጋጁ የቃለ ጉባኤ ሰነዶች ላይ በመፈረም አረጋግጠዋል ቢልም፤ በአራቱ የሥራ ቡድኖች ውስጥ የሚገኙ “በርካታ” ተመካካሪዎች በቃለ ጉባኤዎቹ ላይ አለመፈረማቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። በምክክር ሂደቱ ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆነው የፌደራል ከተሞች ጉዳይ አጀንዳ ላይ ከስምምነት ሳይደረስ በቃለ ጉባኤ ላይ አንፈርምም ያሉ ተመካካሪዎች በርካታ መሆናቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ ቃለ ጉባኤ ባልሰፈረበት ባዶ መዝገብ ላይ ፈርሙ የተባሉ ሌሎች ተመካካሪዎችም “በባዶ መዝገብ ላይ አንፈርምም” በሚል ለቃለ ጉባኤ መመዝገቢያ በተዘጋጀው ቅጽ ላይ ሳይፈርሙ መቅረታቸውን ነግረውናል።
ኮሚሽኑ ነሐሴ 05 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የሰላም ግንባታ፣ የሃይማኖት ጉዳይ፣ የመንግስት አደረጃጀት እና የሙስና እና መልካም አስተዳደር ጉዳይን አጀንዳቸው አድርገው ሲመክሩ የቆዩ የሥራ ቡድኖች “መግባባት” ላይ ደርሰዋል ቢልም፤ መግባባት ላይ ተደርሷል በተባለበት ጊዜ ምልዓተ ጉባኤ መሟላቱና 75 በመቶ የድጋፍ ድምጽ መገኘቱ አለመረጋገጡን ሰምተናል። ኮሚሽኑ ለተመካካሪዎች ባቀረበው “የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት” ሰነድ መሰረት፣ በሥራ ቡድን ደረጃ የውሳኔ ስምምነት አለ ለማለት የተመካካሪዎችን 75 በመቶ ድጋፍ ማግኘት ያስፈልጋል። በማንኛውም የምክክር ደረጃ ውሳኔ የሚሻ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለማስተላለፍ ደግሞ ቢያንስ 75 በመቶ ተመካካሪዎች መገኘት እንዳለባቸውም ሰነዱ ያመላክታል። ይሁንና ኮሚሽኑ ስምምነት ላይ ተደርሷል ሲል ይፋ ባደረገባቸው የሥራ ቡድኖች፣ ሁለቱም ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸው በቆጠራ አለመረጋገጡን፣ የምክክር ሂደቱን የሚመሩ የኮሚሽኑ ባለሙያዎችና የምክረ ሀሳብ አጠናቃሪ ቡድን አባላትም ስለ ቅድመ ሁኔታው አለማንሳታቸውን ምንጮች ነግረውናል።
የአዲስ አበባ ጉዳይ
የፌደራል ከተሞች ጉዳይን እየተመካከረበት የሚገኘው የሥራ ቡድን 7፣ የምክክር ሂደቱን አጠናቅቋል በሚል ቃለ ጉባኤ ላይ እንዲፈረም መወሰኑን ሰምተናል። ነሐሴ 06 ቀን፣ 2018 ዓ.ም ከ8፡00 ጀምሮ በተካሄደና ጥቂት የማይባሉ የቡድኑ አባላት ባልተገኙበት ስብስባ፤ የአዲስ አበባ ሕጋዊ አቋም ላይ ሁለት አማራጮችን ባስቀመጠ የምክረ ሀሳብ ሰነድ ላይ እንዲፈረም መጠየቁን የገለጡልን ምንጮች፤ “አዲስ አበባ ተጠሪነቷ ለፌደራል የሆነ ከተማ ትሁን” እና “የከተማዋ የጠሪነት ለፊደራል መንግስት ሆኖ፣ የኦሮሚያ ክልል መቀጫ መሆኗ በሕገ መንግስቱ ይረጋገጥ” የሚሉት አማራጮች በቃለ ጉባኤ ላይ እንዲካተቱ መደረጋቸውን ነግረውናል።
የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ሁለቱ አማራጮች በቀጣይ በሚከናወኑ የምክክር ሂደቶች ውሳኔ ይተላለፍባቸዋል ማለታቸውንም ሰምተናል። ተመካካሪሪዎች እንዲፈርሙበት በተዘጋጀው መዝገብ ላይ የፈረሙ ተመካካሪዎች መኖራቸውን የጠቆሙን ምንጮች፤ በስብሰባው ተገኝተው “አንፈርምም” ብለው የሄዱ እንዲሁም ስብሰባው እንደሚካሄድ ያልተነገራቸውና ያልተገኙ የሥራ ቡድኑ ተመካካሪዎች መኖራቸውን ገልጠዋል። “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ መሆኗ በሕገ መንግስቱ ይረጋገጥ” የሚለው ምክረ ሀሳብ በቃለ ጉባኤው ላይ መካተት የለበትም የሚሉ ተመካካሪዎች፤ ማስተካከያ ካልተደረገ ፊርማቸውን እንደማያኖሩ መግለጣቸውንም ሰምተናል።
የአዲስ አበባ ጉዳይ “እንዲያድር” የቀረበው ጥያቄ
በአዲስ አበባ ጉዳይ እየተመካከሩ የሚገኙ ተመካካሪዎችን እንዲሁም፤ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ የሚገኙ ወገኖችን እያነጋገረ የቀጠለው የአዲስ አበባ ሕጋዊ አቋም ጉዳይ “እንዲያድር” የሚጠይቁ አካላት መበራከታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል። ለኮሚሽኑ ጥያቄ ማቅረባቸውን ይፋ ካደረጉ ፓርቲዎች በተጨማሪ፣ በጉዳዩ ዙሪያ ከኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ጋር ለመነጋገር ለነሐሴ 07 ቀን ቀጠሮ የያዙ ፓርቲዎች መኖራቸውን ዋዜማ ሰምታለች። ከፓርቲዎች በተጨማሪ የምሁራን ፓናል አባላትም ይህንኑ ጥያቄ ለኮሚሽኑ ማቅረባቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ ኮሚሽኑ እስካሁን ውሳኔ አለማሳለፉን ጠቁመዋል።
የኮሚሽኑ የአንድ ወር የሥራ ግምገማ
ኮሚሽኑ ሐምሌ 08 ቀን የጀመረውን የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደት የገመገመበትን ስብሰባ ማድረጉን ዋዜማ ሰምታለች። ኮሚሽነሮች፣ ባለሙያዎችና ሌሎች የኮሚሽኑ ሠራተኞች በተገኙበት ስብሰባ፤ የምክክሩን አጠቃላይ ሂደት የተመለከቱ ጉዳዮች መነሳታቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ ኮሚሽኑ ላይ ጥያቄ ያስነሱና ወደ አንድ ወገን ያደሉ ናቸው የተባሉ “አወያዮች” እንዲቀነሱ መጠየቁን ጠቁመዋል። ኮሚሽኑ 160 አወያዮችን ማሰማራቱን ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን፤ የምክክር ሂደቱ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መገኘቱን ተከትሎ፤ ለቀጣዩ ሂደት ከሚያስፈልጉ አወያዮች ውጭ፣ ጥቂት የማይባሉት ከሂደቱ እንዲቀነሱ በኮሚሽኑ ባለሙያዎች መጠየቁን ዋዜማ ሰምታለች። በሌሎች የሥራ ቡድኖች እየተካሄደ የሚገኘውን የምክክር ሂደት ተጽዕኖ ውስጥ ስለመክተቱ የተነገረለት የፌደራል ከተሞች ጉዳይ አጀንዳን አስመልክቶም የኮሚሽኑ ባልደረቦች ውይይት ማድረጋቸውን ምንጮች ገልጠዋል።
የአማራ ክልል ተወካዮች ጥያቄ
የአማራ ክልል የማህበረሰብ ክፍሎችን ወክለው በምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙ ተመካካሪዎች፤ ለኮሚሽኑ ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ምንጮች ነግረውናል። ተመካካሪዎች ፊርማቸውን ያኖሩበት የቅሬታ ደብዳቤ፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እና ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ በተገኙበት ነሐሴ 05 ቀን ለኮሚሽኑ ቀርቧል። የቅሬታ ደብዳቤውን እንዲሁም ተመካካሪዎች በቃል ያቀረቡትን ቅሬታ የተቀበሉት ኮሚሽነሮቹ፤ “ተወያይተን” መልስ እንሰጣለን ማለታቸውን ሰምተናል።
ተመካካሪዎቹ ካቀረቧቸው ቅሬታዎች መካከል፤ “በምክክር ሂደቱ ሀሳብን ለመናገር የሚሰጡ ዕድሎች ፍትሃዊ አለመሆን”፣ “ማንነትንና ሀሳብን መሰረት ያደረገ ጫና”፣ “ተመካካሪዎች በአካልና በጽሑፍ ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ ለማስገደድ የሚደረጉ ግፊቶች”፣ “የኮሚሽኑ ባለሙያዎችና የምሁራን ፓናል አባላት ገለልተኝነት ጉዳይ”፣ “የምክክር ሂደቱ ተአማኒነት” እና ሌሎች ጉዳዮችም እንደሚገኙበት ምንጮች ጠቁመዋል።
የጋራ ማረጋገጫ ቡድን አባላት ምርጫ
ስምንቱ የሥራ ቡድኖች “ያጸደቋቸውን” የምክረ ሀሳብ ሰነዶችን “የማጣጣም” ኃላፊነት የሚሰጠውና ስምንቱ የሥራ ቡድኖች እያንዳንዳቸው 15 ተመካካሪዎችን የሚወክሉበት የጋራ ማረጋገጫ ቡድን አባላት ምርጫ ነሐሴ 07 ቀን እንደሚካሄድ ምንጮች ነግረውናል። ከእያንዳንዱ የሥራ ቡድን፤ 12ቱን ክልሎች፣ 2ቱን ከተማ አስተዳደሮች እና የፌደራል ባለድርሻ አካላትን የሚወክሉ 15 ተመካካሪዎች ለቡድኑ አባልነት እንዲመረጡ ይደረጋል ያሉን ምንጮች፤ ከስምንቱ ቡድኖች ከሚመረጡ 120 ተመካካሪዎች በተጨማሪ የምሁራን ፓናል አባላት በቡድኑ ውስጥ እንደሚካተቱ ገልጠዋል። ቡድኑ የአመራር ግብረ ኃይል ማቋቋም እንዳለበት ኮሚሽኑ አቅጣጫ ማስቀመጡንም ዋዜማ የተመለከተችውና ጉዳዩን የተመለከተው ሰነድ ይጠቁማል።
ቡድኑ በተለያዩ ቡድኖች መካከል ባሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ኮሚሽኑ ገልጧል። ቡድኑ የሚያዘጋጀው “የተጣጣመ” ረቂቅ ምክረ ሀሳብ ለየሥራ ቡድኖቹ ቀርቦ እንዲጸድቅ የሚጠበቅ ሲሆን፤ የስምንቱንም የሥራ ቡድኖች ምክረ ሀሳብ ያከተተውና “የተጣጣመው” ሰነድ ለጠቅላላ ጉባኤ ከመቅረቡ በፊት ለክልል ተወካዮች ጉባኤ ቀርቦ መጽደቅ ይኖርበታል። [ዋዜማ]
