December 24/2025 signing ceremony in Addis Ababa

የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ኢትዮጵያን ጨምሮ ከጥቂት የአፍሪቃ ሀገራት ጋር የተፈራረመው የቢሊየኖች ዶላር የጤና ትብብር ስምምነት የሀገራትን የመረጃ ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው በሚል ትችት ይቀርብበታል። የስምምነቱ አላማ የአለም ጤና ድርጅትን ስራዎች በመቀማት ድርጅቱን በማዳከም ላይ ያነጣጠረ ነው በሚልም ይተቻል። ዋዜማ ስለስምምነቱ የሚከተለውን ዘገባ አዘጋጅታለች። አንብቡት

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከተመለሰ በኋላ አሜሪካ በግዙፉ የረድኤት ተቋሟ ዩ ኤስ አይ ዲ በኩል ለተለያዩ ሃገራት ስታደርግ የቆየችውን መጠነ-ሰፊ ድጋፍ እና ትብብር የዛሬ አንድ አመት ገደማ አቋርጣለች፡፡ ‹‹አሜሪካ ፈርስት›› (ቅድሚያ ለአሜሪካ) በሚለው መርሃቸው የሚታወቁት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በምትኩም ‹‹አሜሪካ ፈርስት ግሎባል ኸልዝ ስትራቴጂ›› የተሰኘ አዲስ እቅድ ነድፎ፤ ስምምነቱን ወደ ተግባር ለማውረድ የሚያስችሉ ስምምነቶችን ከተለያዩ ሃገራት ጋር መፈራረሙን ቀጥሏል፡፡    

ይኸው እቅድ ከዚህ ቀደም የነበረውን የድጋፍና ትብብር አካሄድ ሙሉ በሙሉ የቀየረ ሲሆን ተግባራዊነቱም ከሃገራት ጋር በሚደረገው ስምምነት እና ጥምረት ላይ የተወሰነ ነው፡፡ ከሃገራቱ ጋር የሚደረገው ስምምነት ‹‹አሜሪካ ፈርስት›› በተሰኘው አለማቀፍ የጤና ስትራቴጂው ውስጥ የተካተቱ ወሳኝ ሃሳቦችን በተመሳሳይ መልኩ የሚተገብር ሲሆን ለአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ፣ የሁለትዮሽ አጋርነትን መሠረት ያደረገ፣ እንዲሁም አጋር ሀገራትም እንደየአቅማቸው የራሳቸው አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው፡፡

እስካሁን ድረስ በአለማቀፍ ደረጃ ከ 27 ሃገራት ፤ በአፍሪካ ደረጃ ደግሞ ከ 5 ሃገራት ጋር ስምምነቱ ተፈርሟል፡፡ ከአፍሪካ ኬንያ፣ ኢትዮጲያ፣ ቦትስዋና፣ ሴራሊዮን እና ማዳጋስካር ፈርመዋል፡፡ ኢትዮጲያ ለ5 አመታት በሚቆየው ይኸው ስምምነት አማካኝነት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ሲመደብላት፤ ቀሪው በኢትዮጲያ መንግስት በኩል ይሸፈናል፡፡ ከሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ 25 በመቶው ለመድሃኒት ግዢ እና የህክምና ቁሳቁሶች የሚውል ሲሆን 15 በመቶ የሚሆነው ወደ 270 ሺህ የሚጠጉ የጤና ባለሞያዎችን ቅጥር ለመፈጸም የሚውል ነው፡፡ 60 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ለቴክኒካል ድጋፍ እና ተያያዥ ስራዎች የሚውል ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ሀገር የሚመደበው የገንዘብ መጠንም ልዩነት እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ስትራቴጂው ከሃገራት ጋር የሚደረገው ስምምነት እንደ ሰብዓዊ እርዳታ የሚመለከት ሳይሆን፤ በተለያዩ የዓለም አገራት የሚከሰቱ በሽታዎችን ባሉበት ቀድሞ በመለየት፣ በመከላከል እና በመቆጣጠር የአሜሪካውያንን ደኅንነት መጠበቅን የሚያስቀድም ነው፡፡

የስምምነቱ ዋነኛ አላማ

ዋዜማ የተመለከተችው የአሜሪካ ፈርስት አለማቀፍ የጤና ስትራቴጂ ሰነድ በዋነኝነት ሶስት ቁልፍ አላማዎች እንዳሉት የሚገልጽ ሲሆን ይህም ቀዳሚው የአሜሪካውያንን የጤና ደህንነት አስተማማኝ ማድረግ ነው፡፡ አሜሪካን ጠንካራ ማድረግ እና ብልጽግናን ማጎናጸፍ የሚሉት አላማዎች በሁለተኛ እና 3ኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡

የአሜሪካውያንን ደህንነት ለማስጠበቅ በሌሎች ሀገራት የሚከሰቱ እንደ ኤች አይ ቪ፣ ወባ፣ ሳንባ ነቀርሳ፣ የእናቶችና የህጻናት ጤና፣ ፖሊዮ ያሉ በሽታዎችን አሊያም ተያያዥ ወረርሽኞችን በፍጥነት መለየት የሚያስችል አለማቀፍ የክትትል ስርአትን መዘርጋት፤ ወረርሽኝ ሲከሰት ከሃገራቱ መንግስታት ጋር በፍጥነት ምላሽ መስጠት፣ ወረርሽኙን በፍጥነት መለየት የሚችል ዓለም አቀፍ የክትትል ስርዓትን መፍጠር እና ወረርሽኙ አሜሪካን እንዳይጎዳ ተጓዦች እንዲመረመሩ ማድረግን ያካትታል፡፡ 

በሁለተኛነት የተቀመጠውን አሜሪካን የማጠናከር አላማን ከግብ ለማድረስ ደግሞ የሁለትዮሽ ስምምነቶቹ የኢፒዲሚዮሎጂ መረጃን፣ የአገልግሎት አቅርቦት መረጃን እና የአቅርቦት ሰንሰለት መረጃን ለመከታተል የሚያስችሉ ስርአቶች መዘርጋታቸውን የማረጋገጥ ስራን እንደሚያካትቱ ያመለክታል፡፡  ኢትዮጲያን ጨምሮ ሌሎችም ከአሜሪካ ጋር ይህንኑ ስምምነት የፈረሙ ሃገራት፤ የአሜሪካን የቴክኒክ ድጋፍ ከግለሰብ ክሊኒካዊ ቦታዎች ድጋፍ፤ መንግስታት ቁልፍ ተግባራትን እንዲረከቡ ወደ መደገፍ በፍጥነት ለማሸጋገር እንደሚሰሩ ጠቅሶ፤ ይህም የበለጠ ቀጥተኛ የመንግስት-ወደ-መንግስት ድጋፍ እንዲሁም የግል ዘርፉን እና መንግስታዊ ያልሆኑ ከሃይማኖት ጋር የተቆራኙ ድርጅቶችን ጭምር መጠቀምን ያካትታል።

ከዚህ በተጨማሪም፤ ስምምነቱን የፈረሙት ሃገራት መንግስታት በእነዚህ ጥረቶች ላይ በጋራ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እና በቀጣይም ለጤናው ዘርፍ የሚደረጉ ድጋፎችን በሚመለከት ገንዘብ ለመልቀቅ መሟላት ያለባቸውን የአፈፃፀም መለኪያዎችን ያካትታል።

አሜሪካን ብልጽግና የሚያጎናጽፍበትን መንገድ ሲያብራራም፤ ‹‹በዓለም ዙሪያ የአሜሪካን የጤና ፈጠራ በማስተዋወቅ እና ኢኮኖሚያችንን ከተላላፊ በሽታዎች ወረርሽኝ በመጠበቅ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ የአሜሪካን የጤና ዘርፍ ምርቶች በማስተዋወቅ አሜሪካን የበለጠ እንድትበለጽግ እናደርጋለን›› ይላል፡፡ 

የሁለትዮሽ ስምምነቶቹን በመጠቀም በውጭ የእርዳታ ፕሮግራሞች አማካኝነት ከአሜሪካ ኩባንያዎች እቃዎችን በመግዛት እና በማሰራጨት እንዲሁም የአሜሪካን የጤና ፈጠራና ምርቶችን  ማስፋፋትንም ያካተተ ነው፡፡ ሀገራት ከአሜሪካ ጥቅም ጋር የማይስማማ ፕሮግራም የሚያካሂዱ ከሆነ በማንኛውም ጊዜ ስምምነቱ እንዲቋረጥ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

ከኢትዮጲያ ጋር የተደረገው ስምምነት የስትራቴጂውን ዋነኛ መርሆች ያካተተ ሲሆን በዋነኝነት ግን የጤና ባለሞያዎችን ማጠናከር፣ ወረርሽኞችን መቆጣጠር፣ የላብራቶሪ ማእከላት ክትትል እና የመረጃ ልውውጥ፣ የላብራቶሪ ቁሳቁሶችን ማዘመን እንዲሁም ስልጠና መስጠትን፤ ክትትል የሚደረግባቸውን የላብራቶሪ ማእከላትን አሃዝም አካቷል፡፡

ስጋትና ተቃውሞ  

ይህንን ስምምነት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በመፈራረም ቀዳሚ የሆነችው ጎረቤት አገር ኬንያ ናት። ኬንያ የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ስምምነትን በፕሬዝዳንቷ ዊልያም ሩቶ እና በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ አማካኝነት በኅዳር ወር መጨረሻ ላይ ተፈራርማለች። አንዳንድ ኬንያውያን ግን ይህ ስምምነት አሜሪካ እንደ ኤችአይቪ፣ የቲቢ ሕክምና ታሪክ እና የኬንያውያንን የክትባት መረጃዎችን የመሳሰሉ የግል መረጃዎችን እንድታገኝ በር ይከፍትላታል በሚል ስጋት ሙሉ የስምምነቱ ይዘት እንዲገለጽ ወትውተዋል፡፡ 

ለአሜሪካ እንዲጋሩ የሚደረጉት ምን ዓይነት ልዩ የመረጃ ምድቦች እንደሆኑ መንግስታቸው እንዲያብራራ እና ሰነዱ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ በተደጋጋሚ ጠይቀው፤ የስምምነቱ ሰነድ ይፋ ከመደረጉ ባለፈ ጉዳዩ በመጨረሻም ወደ ፍርድ ቤት አምርቷል፡፡   

ስምምነቱ ከተፈረመ ከ 1 ሳምንት በኋላ የኬንያ ፍርድ ቤት የግላዊ መረጃ ደኅንነት ጥበቃን በተመለከተ ለዜጎች መብት የሚከራከሩ ቡድኖች ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት፤ ጥበቃን የሚሹ የጤና መረጃዎች ተላልፈው እንዳይሰጡ ጊዜያዊ ዕግድ ጥሏል።

ሌላኛዋ ስምምነቱን የፈረመችው ሴራሊዮንም ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ማስተናገድ ጀምራለች፡፡ ግለሰቦችና አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የስምምነት ሰነዱ ግልጽ አለመደረጉ አግባብነት እንደሌለው በመጥቀስ፤ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ እየወተወቱ ነው፡፡ 


‹‹ሴራሊዮናውያን  የተመለከቱት  መግለጫዎች እና ማህደር ይዘው በፈገግታ የተሞሉ ባለስልጣናትን ፎቶዎች ብቻ ነው።  ይህ ሚስጥራዊነት ተቀባይነት የለውም። ዜጎች ሰነዱን የመፈተሸ መብት አላቸው›› የሚሉ ጥያቄዎች እየተሰሙ ነው፡፡

የኢትዮጲያ መንግስት የስምምነቱን ዝርዝር ይዘት ይፋ ባያደርግም፤ በአሜሪካ መንግስት መረጃ መሰረት ግን  ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ከተፈረመው ስምምነት የተለየ እንደማይሆን ይታመናል። 

በዚህ ረገድም የጤና መረጃ አስተዳደር ሥርዓትን ለመዘርጋትና ለመተግበር ባለፈው አመት የወጣው መመሪያ ቁጥር 1362/2017 የተካተተው፤የጤና መረጃ ጥበቃ ጉዳይ ስጋት አለን የሚሉ ባለሙያዎችና ተቋማት አሉ።፡፡

 ባለሞያዎቹ ምን ይላሉ?

ስጋቶቹን አስመልክቶ ኸልዝ ፖሊሲ ዋች ባወጣው ዘለግ ያለ ሃተታ ፤ ፍትሐዊ የጥቅም ክፍፍልን የሚያረጋግጥ ሁኔታ በሌለበት ሁኔታ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ብሔራዊ የጤና መረጃ እና ናሙናዎችን የማጋራት ስምምነት ላይ መድረስ ሀገራት ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ሊያሳጣ እንደሚችል እንዲሁም ብሔራዊ እና ቀጠናዊ የጤና መረጃ ሉዓላዊነትን የሚሸረሽር ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል፡፡

በአንድ ጤና ላይ የሚሰራ አለማቀፍ ተቋም ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙት ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የህክምና ባለሞያ፤ ስምምነቱ ለሀገራቱ ይደረግ የነበረውን ሙሉ የድጋፍ ጥቅል የሚያስቀርና ሃገራቱም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ መሆኑን በበጎ እንደሚመለከቱት ገልጸዋል፡፡ ሃገራቱን ከጥገኝነት ከማላቀቅ ባለፈ ፤ በስምምነቱ የተካተተውን የድጋፍ መጠን በየጊዜው ለመልቀቅ አፈጻጸምን መሰረት ያደረገ ሂደት መኖሩ ጠቃሚ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ሆኖም፤ እንደ ኢትዮጲያ ያሉ ፈራሚ አገራት የእያንዳንዱ ዜጋቸው የጤና መረጃ (የዘረመል፣ የደም ፣ የህክምና ታሪክ እና ሌሎችም መረጃዎች) ተላልፎ የሚሰጥበት ሁኔታ ከመኖሩም በላይ፤ ከጤና መሠረተ ልማቶቻቸው አኳያ በውጭ አገራት ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋል በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ወረርሽኞች በሚከሰቱበት ወቅትም፤ ስምምነቱ ናሙናዎችን የመስጠት ግዴታ እንደሚጥል በመጥቀስ፤ ይህም የአለም ጤና ድርጅትን ከጨዋታ ውጪ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ይህም የአለምን የጤና ዘርፍ በአሜሪካ እይታ እና ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ እንደሚያደርገው አስረድተዋል፡፡ በተለይም ኢትዮጲያ ባለችበት አጠቃላይ ሁኔታ የጤና ዘርፏን መቆጣጠር ወደ ማትችልበት ደረጃ ሊያደርሳት እንደሚችልም ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ‹‹ለዚህም ነው ከኬንያ በስተቀር ሁሉም ፈራሚ ሀገራት ስምምነቱን ግልጽ ያላደረጉት›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ ፈርስት አለማቀፍ የጤና ስትራቴጂ ስምምነትን ኢትዮጲያና ኬንያን ጨምሮ ከ27 የአለም ሃገራት ጋር የተፈራረመ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ህንድ፣ ታይላንድ፣ ፖላንድ እና የላቲን አሜሪካ ሃገራት ይገኙበታል፡፡ [ዋዜማ]

የዋዜማን ዘገባዎች በምንጭነት የምትጠቀሙ ሌሎች የሚዲያ አገልግሎቶች፣ አባካችሁ ዘገባውን ሳይዛባ በማቅረብ እና ምንጩን በአግባቡ በመጥቀስ የሙያ ስነምግባርን ያክብሩ።