ዋዜማ- በአማራና በትግራይ ክልል የይገባኛል ውዝግብ ባለበት የራያ አካባቢ እገታ፣ ዝርፊያና ግድያ እየተስፋፋ መሆኑንና ወጣቶችን አስገድዶ ለውትድርና መመልመልም እየተበራከተ መምጣቱን ዋዜማ ካሰባሰበችው መረጃ ማረጋገጥ ችላለች።
ዋዜማ ከአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው ባሰባሰበችው መረጃ ፣ በተለይ በራያ አምስት ወረዳዎች ሰዎችን አግቶ ማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቅ፣ ታዳጊዎችን ጨምሮ ዜጎችን አስገድዶ በማገት የታጣቂ ቡድን አባላት እንዲሆኑ መመልመል እየተስፋፋ መጥቷል።
ይህ እገታ ፣ዘረፋና ግድያ ማንነትንና የፖለቲካ አመለካከትን መሰረት አድርጎ ጭምር የሚካሄድ በመሆኑ ፖለቲካው ለወንጀል ድርጊት ሽፋን ለመሆኑ ምስክር ነው ይላሉ ወንድማቸውን ስድስት መቶ ሺሕ ብር ከፍለው ከእገታ ያስለቀቁና በውጪ ሀገር የሚኖሩ እማኝ።
እንደየአካባቢው ቢለያይም በዚህ ድርጊት በዋናነት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፀጥታ አባላት ነን በሚሉ ታጣቂዎች የሚፈፀም ሲሆን የአማራ ፋኖ ታጣቂ ናቸው የተባሉ ቡድኖችም በድርጊቱ ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸውን እንደሚያውቁ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
እየተስፋፋ የመጣው ህገወጥነት ለተራ ዘራፊና ቀማኛ ምቹ በመሆኑ የወንጀሉ ተሳታፊዎችን በእርግጠኝነት ለመለየት አደናጋሪ መሆኑን አንድ የአላማጣ ከተማ መምህር ስለጉዳዩ ለዋዜማ በሰጠው ምስክርነት ላይ ተናግሯል።
ግድያና እገታ በተደጋጋሚ በሚፈጸምባት ራያ አላማጣ ከተማ ባለፈው ሳምንት ኹለት ወጣቶች በተከታታይ ተገድለዋል። አንድ ማንነቱ ያልታወቀ ወጣት ህዳር 13፣ 2018 ዓ.ም በአላማጣ ከተማ ገበያ አካባቢ ተገድሎ የተገኘ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ህዳር 15፣ 2018 ዓ.ም አብዲ መኮንን የተባለ ወጣት ተገድሏል።
በአማራ ክልል በኩል የተቋቋመው አስተዳደር ከመፍረሱ በፊት የአማራ ፖሊስ አባል ነበረው አብዲ የተገደለው፣ በዕለቱ ምሽት 2፡00 ገደማ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ታጣቂዎች ናቸው በተባሉ ግለሰቦች በጩቤ ተወግቶ መሆኑን ባልደረቦቹ ለዋዜማ ተናግረዋል።
ከግድያው በተጨማሪ አንድ የሃይማኖት አባትን ጨምሮ በርካቶች በታጣቂዎች መታገታቸውን ነዋሪዎች ገልጠዋል።
ቀሲስ ናየው ደርበው የተባሉ የአቦ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፣ ህዳር 18፣ 2018 ዓ. ም ከኮረም ከተማ በምሽት በታጣቂዎች ታፍነው መወሰዳቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናግረዋል።
ታጣቂዎች ያፈኗቸውን የሃይማት አባትና ወጣቶችን ለመልቀቅ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚጠይቁ ምንጮች ገልጠዋል። በፖለቲካ አመለካከትና ለገንዘብ የሚታፈኑ ሰዎች አካላዊ ደብድባ እንደሚፈጸምባቸው ም ከዚህ ቀደም ታግተው የነበሩ ግለሰቦች ለዋዜማ ተናግረዋል።
ባለፈው አንድ ወር ገደማ ውስጥ በትግራይ ጊዜያዊ መንግስት ታጣቂዎች ከታፈኑ የሃይማኖት አባቶች መካከል፣ ከአንድ ዓመት በፊት እንደ አዲስ የተቋቋመው የራያ ሀገረ ሰብከት ሂሳብ ሹም መምህር ሀረገወይን አያሌው፣ የቅልሻ ደብረ ሰላም መድኃኔአለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ካህሳይ መረሳ፣ የራያ አላማጠ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ኃላፊ መሪጌታ የማነ ብርሃን ታፈሰና ሌሎች ወጣቶች ይገኙበታል፡፡
ከፖለቲካ አመለካከት ልዩነት በተጨማሪ ከገጠር እስከ ከተማ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች በየጊዜው በታጣቂዎች እንደሚታገቱ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። አንድ የዋዜማ ምንጭ ደግሞ በአካባቢው ያለውን ኹኔታ “አቅሙ ደህና የሆነ ሰውን ከተገኘ ይታፈናል” ሲሉ ገልጠውታል።
አንድ የራያ አካባቢ ነጋዴ ልጆቹንና ሚስቱን የህወሓት ታጣቂዎች ናቸው ያላቸው ኃይሎች ለማገት ሙከራ ካደረጉበት በኋላ ቤተሰቡን ይዞ አዲስ አበባ ለመግባት መገደዱ ለዋዜማ ተናግሯል።
አንድ የአላማጣ ከተማ ነዋሪ እናት የታገተ ልጃቸውን ለማስለቀቅ፣ የአንገትና የግንባር ወርቃቸውን ሸጠው ለታጣቂዎች 400 ሺህ ብር ከፍለው ማስለቀቃቸውን ይናገራሉ፡፡
እጃቸው ላይ ገንዘብ የሌላቸው ቤተሰቦቻቸው የታገቱባቸውን ሰዎች ለማስለቀቅ መሬት ከመሸጥ እሰከ “እርጥባን” እሰከተባለ የአደባባይ ልመና ደርሰዋል፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ መንግስት ታጣቂዎች ከዚህ ቀደምም በፖለቲካ አመለካከት ላይ የተመሰረተ እስር ሲፈጽሙ የነበረ ቢሆንም፣ የማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቅ የጀመሩት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ነው።
የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ግድያና እገታ በተደጋጋሚ የሚፈጸመው አላማጣ፣ ኮረም፣ ዛታ፣ ኦፍላና አዘቦ ባሉ የራያ ወረዳዎች ውስጥ ነው።
ከእገታ፣ ደብደባና ንብረት ዘረፋ በተጨማሪ በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች፣ ወጣቶችን በግዳጅ ለወታደራዊ ስልጠና የመመልመል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ነዋሪዎች ጠቁመዋል። የአሁኑ ወቅት በአወዛጋቢ የራያ አካባቢዎች በስፋት የሚንቀሳቀሱት የትግራይ ጊዜያዊ መንግስት ታጣቂዎች፣ በገጠር መንደሮች ወጣቶችን ለወታደራዊ ስልጠና ለመመልመል እንደሚንቀሳቀሱ ምንጮች ገልጠዋል።
አንድ የአካባቢው ነዋሪ “በገጠር አካባቢዎች ወዛደሮች ለሥራ ይፈለጋሉ ብለው ከወሰዷቸው በኋላ ወደ ሥልጠና ያስገቧቸዋል” ብለዋል።
የፋኖ ተጣቂዎች አልፎ አልፎ በሚንቀሳቀሱባቸው ውስን የገጠር አካባቢዎች ላይ ወጣቶች እንዲቀላቀሏቸው፣ ‘እኛ እየታገል እናንተ ምን ትሰራላችሁ’ በሚል ጫና እንደሚፈጥሩ ምንጮች ገልጠዋል። ምንም እንኳን በሚንቀሳቀሱባቸው ውስን ቦታዎች ላይ ማኅበረሰቡን እየሰበሰቡ ድጋፍ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም፣ እስከአሁን የግዳጅ ምልመላ እንዳልገጠማቸው ነዋሪዎች ጠቁመዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ መንግስት ታጣቂዎች በአማራ ክልል በኩል በተሰየመው አስተዳደርና በአካባቢው ኮማንድ ፖስት ሥር የሚመሩ መንግሥታዊ ተቋማትን በኃይል እየተቆጣጠሩ ነው ተብሏል። ባለፉት ኹለት ሳምንታት ውስጥ የሥራ ኃላፊዎችም በዛቻና መስፈራሪያ እንዲለቁ በማድረግ የጤና፣ የውሃና ትራንስፖርት ተቋማትን መቆጣጠራቸውን ዋዜማ ተረድታለች።
የትግራይ ጊዜያዊ መንግስት ታጣቂዎች ግድያ፣ እገታ፣ ዘረፋና የተቋማት ኃላፊዎችን በጫና ሥራ የሚያስለቅቁባቸው አካባቢዎች የፌደራል መንግሥት ያሰማራው ኮማንድ ፖስት መኖሩ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ ኮማንድ ፖስቱ ‘ግጭት እንዳይፈጠር’ በሚል የትግራይ ኃይሎችን እንቅስቃሴ ማስቆም አለመቻሉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ የአካባቢው ባለሥልጣን የዋዜማ ተናግረዋል።
በአወዛጋቢ የራያ አካባቢዎች በተለይ በአላማጣ ከተማ በተደጋጋሚ ግድያዎች መፈጸማቸው ዋዜማ መዘገቧ ይታወሳል።
በአወዛጋቢ የራያ አካባቢዎች የፌደራል መንግሥት ያሰማራው ኮማድ ፖስት፣ ለቆ እንዲወጣ ሕወሓት ህዳር 17፣ 2018 ዓ፣ም በሰጠው መግለጫ ጠይቋል። ሕወሓት ኮማንድ ፖስቱ አወዛጋቢ የራያ አካባቢዎችን ለቆ እንዲወጣ የጠየቀው፣ ለስድስት ወር ጊዜ ገደብ ተሰማቶ ከሦስት ዓመት በላይ መቆየቱ አግባብነት የለውም በሚል ነው። [ዋዜማ]
