ዋዜማ-የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ተቃዋሚው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) ራሱን አክስሞ ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጋር ለመዋሀድ ውሳኔ ማሳለፉን ዋዜማ ከፓርቲው አመራሮች ሰምታለች፡፡

ቦዴፓ ህዳር 15/2018 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የመክሰም ውሳኔ ማሳለፉን የፓርቲው ፕሬዝዳንት አመንቴ ገሺ አረጋግጠውልናል፡፡ በአስቸኳይ ጉባኤው “የውህደት ውሳኔ ነው ያሳለፍነው” በማለት የአስቸኳይ ጉባኤው ዓላማ ፓርቲውን ማክሰም እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አመንቴ እንደገለጹት ከሆነ ቦዴፓ ህልውናውን አክስሞ “ ያለውን ኃይል፣ አጀንዳና ንብረት ይዞ፣ ብልጽግናን ይቀላቀላል” ብለዋል፡፡ ውልናውን ለማክሰም ውሳኔ ያሳለፈው ፓርቲው የሚቀላቀለው ከክልሉ ብልጽግና ቅንጫፍ ሳይሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የሚመራውን እናት ፓርቲ ብልጽግናን መሆኑን አመንቴ ገልጸዋል፡፡

በስምምነት ሂደቱ የክልሉ መንግሥት ፓርቲ ከብልጽግና ጽ/ቤት የተሰጠውን መምሪያ የማስፈፀም ሚና መወጣቱን አመንቴ ገልጠዋል፡፡ አመንቴ ወደ ብልጽግና ለመግባት በምን እንደተስማሙ ከዋዜማ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች “ተግባብተናል” ከማለት የዘለለ ዝርዝር የስምምነት ይዘቶችን ከመግለጥ ተቆጥበዋል፡፡

የውህደቱ ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ ዝርዝር የስምምነቱን ይዘቶች ይፋ እንደሚያደርጉ አመንቴ ተናግረዋል፡፡

የሥራ አስፈጻሚ አባላትን ጨምሮ አንዳንድ የፓርቲው አመራርና አባላት ቦዴፓ ውልውናውን ያጣበትን ውሳኔ እንደማይቀበሉ ገልጠዋል፡፡ ቦዴፓ ህልውናውን ባጣበት አስቸኳይ ጉባኤ “ሆን ተብሎ” ከሂደቱ መገለላቸውን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካዩና የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ መብራቱ አለሙ (ዶ/ር) ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

ቦዴፓ ህልውና የከሰመበት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ከመካሄዱ ከቀናት በፊት የፓርቲው ፕሬዝዳንት አመንቴ ገሺ በጻፉት ደብዳቤ የፓርላማ አባሉ መብራቱ አለሙ ከሥራ አስፈጻሚ አባልነታቸው መታገዳቸውን አሳውቀዋቸዋል፡፡ በፕሬዝዳንቱ ተፈርሞ የእግድ ደብዳቤ የደረሳቸው መብራቱ፣ የፓርቲውን መክሰም ሂደት በመቃወም ለምርጫ ቦርድ ቅሬታ ማቅረባቸውን  ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው ህልውናውን አክስሞ ወደ ብልጽግና ለመግባት ባሳለፈው ውሳኔ፣ ካሉት 13 የሥራ አስፈጻሚ አባላት አምስቱ ስምምነታቸውን አልገለጡም ተብሏል፡፡ እንዲሁም በፓርቲው መክሰም ያልተስማሙ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ፣ በጉባኤው ላይ ያልተገኙ አባላት መኖራቸውን መብራቱ ይናገራሉ፡፡

ዋዜማ ያነጋገራቸው የፓርቲው ፕሬዝዳንት “የእኛ አባል ሆኖ መጠራት የሚገባው ሳይጠራ የቀረ የለም” በማለት የቀረበውን ክስ አስተባብለዋል፡፡

ወደ ብልጽግና ለመግባት ውሳኔ ያሳለፈው ቦዴፓ፣ በስድተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተወዳድሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት ወንበር ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ ፕሬዝዳንቱን አመንቴ ገሺና በእስር ላይ የሚገኙትን ዮሐንስ ተሰማን ጨምሮ በክልሉ ምክር ቤት ሦስት ተመራጮች አሉት፡፡

የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ኃላፊ መብራቱ አለሙ አሸንፈው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ሕጋዊ አግባብነት የለውም ያሉትን የፓርቲያቸውን መክሰም ምርጫ ቦርድ እውቅና እንዳይሰጥ ጥያቄ ማቅረባቸው ጠቁመዋል፡፡

ብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅሕፈት ቤት በጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ያቀረብነውን ጥያቄ እስከ ማክሰኞ ምሽት አልመለሰልንም።

ቦዴፓ ህልውናውን አክስሞ ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጋር ለመዋሀድ ያሰለፈው ውሳኔ የምርጫ ቦርድን ይሁንታ ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡ [ዋዜማ]