ዋዜማ- የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ 7ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የሕገመንግሥት ማሻሻያ በማድረግ የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓትን የሚከተለው የአገሪቱ የምርጫ ስርዓት እንዲቀየር ጥያቄ ማቅረቡን ዋዜማ ሰምታለች።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ከቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫ በፊት በምርጫ ሥርዓት ሕጉ፣ ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረቡንም ስምተናል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ይህንኑ ጥያቄ በጽሁፍ ያቀረበው፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ለጠቅላይ ሚንስቴር ጽሕፈት ቤት ነው። ጥያቄው ለተጠቀሱት የመንግሥት አካላት የቀረበው፣ ጥቅምት 25፣ 2018 ዓ፣ም መሆኑን ዋዜማ ከፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ደብዳቤ ላይ ተመልክታለች።

የፖለቲካ ፓርቲዎች አንስተዋቸዋል ተብለው በጋራ ምክር ቤቱ በኩል ለመንግሥት የቀረቡት ጥያቄዎች፣ የምርጫ ስርዓት ለውጥ፣ የእጩ ተመራጮች የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ሂደት፣ ፓርቲዎች ከመንግሥት የሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ እና የምርጫ ጊዜ ሰሌዳው “በቂ እና አመቺ የጊዜ ቀመር” ያለው እንዲሆን የሚሉት መሆናቸውን የጋራ ምክር ቤቱ ደብዳቤ ያስረዳል።

የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እነዚህን ጥያቄዎች ያቀረበው፣ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን አገር ዓቀፍ ምርጫ ግንቦት 24፣ 2018 ዓ፣ም ለማካሄድ ጊዜያዊ ሰሌዳ ካወጣ ከቀናት በኋላ ነው።

ሕገመንግሥቱ ከጸደቀበት 1987 ዓ፣ም ጀምሮ አገሪቱ ስትጠቀምበት የቆየችው የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት በርካታ ውስንነቶች እንዳሉበት የጠቆመው የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ከእነዚህ ውስንነቶች መካከል የመራጮች ድምጽ መባክን እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ የማሸነፍ እድል እንዳይኖራቸው ማድረጉ ተጠቃሽ ናቸው ብሏል፡፡

ቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ እና ቅቡልነት ያለው እንዲሆን፣ የሕገመንግስት ማሻሻያ በማድረግ የአብላጫ ደምጽ ምርጫ ስርዓቱ እንዲቀየር አባል ፓርቲዎች መጠየቃቸውን ምክር ቤቱ በደብዳቤው ላይ አስረድቷል።

የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የፖለቲካ፣ የቋንቋ፣ የኃይማኖትና ባህል ብዝሃነት ባለባቸው ሀገራት፣ የተለያየ የፖለቲካ ፕሮግራም እና ማህበራዊ መሰረት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በፌደራል እና ክልል ምክር ቤቶች ውክልና እንዲያገኙ እድል እንደማይፈጥር ምክር ቤቱ ገልጧል።

ባለፉት ስድስት ጠቅላላ ምርጫዎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በክልል ምክር ቤቶች ወንበር እንዳያገኙ ካደረጉ በርካታ ምክንያቶች መካከል አንዱ የአብላጫ ድምጽ ምርጫ ስርዓቱ መሆኑንም ምክር ቤቱ በዚሁ ደብዳቤው ላይ ጠቅሷል።

የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት ወደ ተመጣጣኝ የምርጫ ስርዓት እንዲለወጥ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ ሲያነሱ እንደቆዩ በደብዳቤ ላይ ተገልጧል።

ከ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ እና የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች በተገኙበት አንድ መድረክ ላይ የምርጫ ስርዓቱን አስመልክቶ በተደረገ ውይይት፣ የአገሪቱ የምርጫ ስርዓት ከአብላጫ ወደ ተመጣጣኝ የምርጫ ስርዓት መለወጥ እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበርም ምክር ቤቱ አስታውሷል።

ምክር ቤቱ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይለወጥ ቀርቷል የተባለው የምርጫ ስርዓት ለ7ኛው አገር አቀፍ ምርጫ በሕግ መንግሥት ማሻሻያ እንዲለወጥ አቋም መያዙን ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓት እንደምትከተል በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 54 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ተደንግጓል። በዚህም ሳቢያ፣ ኢትዮጵያ የምርጫ ስርዓቷን በሕገመንግስቷ መደንገግ አልነበረባትም የሚል ትችት ሲቀርብ እንደቆየ የሚታወቅ ነው። ይህ ትችት የሚቀርበው፣ ለሕገመንግሥት ማሻሻያ በራሱ በሕገመንግስቱ ላይ የተደነገጉት መስፈርቶች ጠበቅ ያሉ በመሆናቸው ነው።

ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤቱ በኩል ያቀረቡት ኹለተኛው ጥያቄ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገውን ረቂቅ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ የተመለከተ ነው። የጊዜ ሰሌዳ የምርጫ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የጠቆመው ምክር ቤቱ፣ የጊዜ ሰሌዳ ለመራጮች እና እጩዎች ምዝገባ፣ ጥምረት መፍጠር ለሚሹ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለምርጫ ቅስቀሳ ‘በቂ እና አመቺ የጊዜ ቀመር ሊኖረው’ እንደሚገባ ገልጧል፡፡

ይህንኑ መሰረት በማድረግም፣ የቀጣዩን ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቅድመ-ምርጫ ስራዎችን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ይችሉ ዘንድ በቂ ጊዜ መስጠት በሚያስችል መልኩ እንዲዘጋጅ ምክር ቤቱ በዚሁ ደብዳቤው ጠይቋል።

በተለይም የጊዜ ሰሌዳውን ማሻሻል፣ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረቶችን እንዲፈጥሩ ሰፊ እድል ይሰጣቸዋል በማለት የጊዜ ሰሌዳ ለውጡን አስፈላጊነት ምክር ቤቱ አስረድቷል። ምርጫ ቦርድ ይህንን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ፣ የጥምረት መመስረቻ የጊዜ ሰሌዳ የሚሻሻልበትን ሁኔታ እንዲፈጥር የጋራ ምክር ቤቱ ጠይቋል። ምርጫ ቦርድ ከሳምንት በፊት ለፓርቲዎች ያቀረበው የምርጫ ሰሌዳ ገና በረቂቅ ደረጃ ያለ እና የመጨረሻ ውሳኔ ያላገኘ ነው።

ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤቱ በኩል ለመንግሥት ያቀረቡት ሌላኛው የሕግ ማሻሻያ ጥያቄ፣ የተመራጭ እጩዎች የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብን የሚመለከት ነው። ምክር ቤቱ፣ የአገሪቱ ተጨባጭ የሰላም፣ የደህንነት እና የፀጥታ ሁኔታ የድጋፍ ፊርማ ለመሰብሰብ የሚያስችል እንዳልሆነ በመጥቀስ፣ በተለይም ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ለመወዳደር አስቻይ ሁኔታ አይደለም ብሏል።

በቀጣይ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ እና የአካባቢ ምርጫዎች ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆኑ፣ በፓርቲ የታቀፉ እጩዎች የድጋፍ ፊርማ እንዲያሰባስቡ የሚያስገድደው ሕግ እንዲሻሻል ምክር ቤቱ ጠይቋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ስነምግባር አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ቁጥር 139/2017፣ አንቀፅ 10፣ ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ በተቀመጠው ዝርዝር የእጩነት መስፈርቶች መሰረት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ለመወዳደር እያንዳንዱ እጩ 2 ሺህ፣ ሴት እጩዎች 1 ሺህ 500 እንዲሁም አካል ጉዳተኛ እጩዎች 1 ሺህ 500 ፊርማ ማሰባሰብ አለባቸው።

ለክልል ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ እጩዎች ባንጻሩ፣ 1 ሺህ፣ ሴት እጩዎች 750፤ ወንድ አካል ጉዳተኛ እጩ 750 እና ሴት አካል ጉዳተኛ እጩ 500 የድጋፍ ፊርማ ማቅረብ እንዳለባቸው አዋጁ መደንገጉን ምክር ቤቱ ጠቅሷል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ እንዲሻሻል ያቀረበው አራተኛው ጥያቄ፣ መንግሥት ለፓርቲዎች የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ የሚመለከት ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች በመተዳደሪያ ደንባቸው ላይ የጠቀሱትን የአባላት መዋጮ 20 በመቶ መሰብሰባቸው ካልተረጋገጠ፣ ከመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ አያገኙም የሚለው አስገዳጅ ድንጋጌ እንዲሻር ምክር ቤቱ ጠይቋል። ምክር ቤቱ፣ ፓርቲዎች 20 በመቶ ከሆኑ አባላት መዋጮ የመሰብሰብ ግዴታቸው እንዲሻር የጠየቀው፣ ድንጋጌው ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ስለማይቻል መሆኑን ገልጧል።

በቅርቡ በተሻሻለው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የስነምግባር አዋጅ መሠረት ፓርቲዎች ከመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ከ20 በመቶ አባሎቻቸው መዋጮ የመሰብሰብ ግዴታ አለባቸው። [ዋዜማ]