ሟች ለማ ወንድአፈረው

ዋዜማ- በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለማ ወንድአፈረው ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት መገደላቸውን ዋዜማ ከአካባቢው ምንጮች ስምታለች።

የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ኃላፊዎች በታጣቂዎች ሲገደሉ፣ ይህ ሦስተኛው ነው። ሃላፊው በታጣቂዎች ጥቃት መገደላቸውን የከተማ አስተዳደሩ ዓርብ፣ ጥቅምት 14፣ 2018 ዓ፣ም አመሻሽ ላይ ባወጣው የሐዘን መግለጫ አረጋግጧል። የከተማ አስተደደሩ በሃላፊው ላይ ግድያው የተፈጸመው፣ “የጥፋት ቡድኖች” ሲል በጠራቸው ተጣቂ ኃይሎች መሆኑን አስታውቋል።

የከተማ አስተዳደሩ በዚሁ መግለጫው፣ “ሀሳብን በሀሳብ እንጂ በጉልበት ማሸነፍ የማይችሉ” በማለት ያወገዛቸው የግድያው ፈጻሚዎች፣ በሸዋሮቢት ከተማ ላይ ‘የጨለማ ጥላቸውን’ አጥልተዋል ብሏል። የሰላምና ጸጥታ ኃላፊውን የገደሉት ኃይሎች፣ “የጥፋት ተላላኪዎች፣ ሀሳብን የሚፈሩ እና በውይይት የማያምኑ” ናቸው ሲል የከተማ አስተዳደሩ ወንጅሏል።

የከተማ አስተዳደሩ በኃላፊው ላይ ግድያ የፈጸሙትንና ከጀርባቸው ያሉትን ኃይሎች በማስረጃ ላይ ተመስርቶ በማደን ለህግ ለማቅረብ እንደሚሰራም በዚሁ መግለጫው ላይ ጠቁሟል።

በአማራ ክልል በመንግሥት ሃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የትጥቅ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ፣ በሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ዩተለያዩ መዋቅሮች ላይ በሚገኙ ሃላፊዎች ላይ በታጣቂዎች ጥቃት ግድያ ሲፈጸም ቆይቷል።

ባለፉት ዓመታት በታጣቂዎች ከተገደሉ የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናት መካከል፣ ነሐሴ 26፣ 2014 ዓ፣ም የተገደሉት የከተማዋ ከንቲባ ውብሸት አያሌው ይገኙበታል። ከንቲባ ውብሸት ማንነታቸው ያልታወቁ የታጠቁ ኃይሎች በመኖሪያ ቤታቸው ላይ በፈጸሙት ጥቃት መገደላቸውን የከተማዋ አስተዳደር በወቅቱ ገልጦ ነበር።

ዓርብ’ለት ከተገደሉት ለማ ወንድአፈረው ቀደም ብለው የከተማዋ የሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አብዱ ሁሴን በ2015 ዓ፣ም በታጣቂዎች ጥቃት የተገደሉ ሲሆን፣ ከእሳቸው በኋላ የተሾሙት የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ ፍጹም ጌታቸው ደሞ በ2016 ዓ፣ም በተመሳሳይ የታጣቂዎች ጥቃት እንደተገደሉ የሚታወስ ነው። [ዋዜማ]