የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ስባተኛውን ሀገራዊ የምርጫ ሰሌዳ በሚመለከት ከፖለቲካ ፓርቲዎችጋር ማክሰኞ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ያደረኩት ውይይት ገንቢና በቀጣይ ለሚደረጉ የምርጫ ዝግጅቶች ግብዐት የተገኘበት ነበር ሲል አስታውቋል።


የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በዕለቱ ውይይት ላይ እንደተናገሩት ቦርዱ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ የማስፈጸም ሕገ፡መንግሥታዊ ግዴታው እንደሆነ፤ ይኽም ሲሆን፤ በየተግባራቱ ሁሉ ቅደም ተከተሉን ጠብቆ ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚወያይና ተጨባጭነት ያላቸውን ሁነቶች ያገናዘበ ውሣኔዎችን እያሳለፈ ግልጸኝነቱን፣ ነፃና ገለልተኛነት እያረጋገጠ ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል።

የፀጥታ ሁኔታም ሆነ ተያያዥ ጉዳዮችን ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ፓርቲዎቹን ያሣተፈ ቀጣይ ውይይት እንደሚኖርና ምርጫውን የተመለከቱ ማንኛውም ተግባራት ላይ በቅርበትና በጋራ በመሥራት ይከናወናል ብሏል ቦርዱ ።

ይኽም ሲሆን፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በበኩላቸው የመራጮችን ትምህርት ጨምሮ የምርጫውን ሰላማዊነትና ዲሞክራሲያዊነት ለማረጋገጥ የሚረዱ ሕጋዊ ተግባራትን ከወዲሁ ዝግጅት በማድረግ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ምርጫ ቦርድ አሳስቧል።

[አስቀድሞ የቀረበውና የታረመውን የዋዜማ ዘገባ እዚህ ይመልከቱ]

የዋዜማ ማረሚያ

ማክሰኞ ተደርጎ በነበረው ውይይት ዙሪያ በዋዜማ ራዲዮ በኩል የቀረበውን ዘገባ በተመለከተ ቦርዱ ቅሬታ እንዳለው ገልጾልን በጉዳዩ ላይ የቦርዱ ሃላፊዎችን አስተያያት ተቀብለናል። ከቅሬታዎቹ አንዱ ውይይቱ ለጋዜጠኞች ዝግ ነበር ተብሎ መዘገቡ አስቀድሞ ስለክንውኑ አሉታዊ ምስል የሚሰጥ ነው የሚል ነው። ቦርዱ ጋዜጠኞች አለመጋበዛቸውን ግን ደግሞ ቢመጡ ለመዘገብ አይከለከሉም ነበር ብሏል።

ሌላውን የቅሬታ ነጥብ ረቂቅ የምርጫ ሰሌዳውን ከብልፅግና ፓርቲ በቀር ሌሎች ተቃውመውታል መባሉ ከእውነታው የተለየ ነው የሚል ሲሆን ዋዜማ ያቀረበችውን ዘገባ በድጋሚ በመመርመር በውይይቱ ከተሳተፉ ፓርቲዎች የቀረበውን የጊዜ ሰሌዳ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚደግፉት የሚያሳይ መረጃ አግኝተናል። ዋዜማም ይህንን መረጃ አርማለች። ለዚህም ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን።


የዋዜማ ዘገባ በፖለቲካ ፓርቲዎች የተነሳውን በሀገሪቱ በተለይም የሰላምና ፀጥታ ችግር ባለባቸው የአማራ፣ ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች “ነፃና ገለልተኛ” ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ መኖር አለመኖሩ ሳይገመገም የምርጫ ስሌዳ ላይ ውይይት ማካሄድ ተገቢ አይደለም የሚለውን ነጥብ የተንተራሰ ነበር። ለዚህም በውይይቱ የተሳተፉ ስድስት ያህል የፓርቲ ተወካዮችን አነጋግረናል። የምርጫ ቦርድ ቅሬታ በአመዛኙ ከዘገባው አንድምታና ትርጓሜ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን በጎ ያልሆነ ምስል ለማስቀረት ያለመ እንደሚሆን እንረዳለን።

ዋና አዘጋጁ

[አስቀድሞ የቀረበውና የታረመውን የዋዜማ ዘገባ እዚህ ይመልከቱ]