ዋዜማ- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ስባተኛውን ሀገራዊ የምርጫ ሰሌዳ በሚመለከት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማወያየት ለጋዜጠኞች ዝግ የሆነ ስብሰባ ትናንት አድርጎ ነበር፤ ይሁንና ፓርቲዎቹ በጊዜ ሰሌዳው ላይ ከመወያየታችን በፊት የሀገሪቱ  ሰላምና ፀጥታ “ነፃ” ምርጫ ለማድረግ “አስቻይ” አይደለም የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል። ምርጫውን ማራዘም የሚል ሀሳብም ቀርቧል። ውይይቱም የተያዘለትን አጀንዳ ትቶ በአመዛኙ በሰላምና ፀጥታ ላይ ተወያይቷል። ዋዜማ ያሰባሰበችውን መረጃ አንብቡት

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛው አገር ዓቀፍ ምርጫ የሚካሄድበትን ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ለውይይት ባቀረበበት ወቅት ተቃውሞ እንደገጠመው ዋዜማ ሰምታለች። 

ቦርዱ ቀጣዩ አገር ዓቀፍ ምርጫ በሚካሄድበት የጊዜ ሰሌዳ ዙሪያ ጥቅምት 10፣ 2018 ዓ፣ም በአዲስ አበባ ከተማ ስካይላይት ሆቴል ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በዝግ መክሯል። 

ለጋዜጠኞች ዝግ የነበረው የቦርዱ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ወይይት ዋና አጀንዳ የምርጫው ማካሄጃ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ቢሆንም፣ የውይይቱ ተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ግን በአገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ ከሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ከፖለቲካ ምኅዳር ጋር የተያያዙ አስቻይ ሁኔታዎች በመኖር አለመኖራቸው ላይ ቦርዱ እና ፓርቲዎች ከስምምነት ላይ ባልደረሱበት ሁኔታ በምርጫ ማካሄጃ የጊዜ ሰሌዳ ላይ መነጋገር አንችልም በሚል ተቃውሞ ማሰማታቸውን ዋዜማ ከውይይቱ ታዳሚዎች ሰምታለች። 

ምንም እንኳን ምርጫ ቦርድ በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ከፓርቲዎች ግብዓት ለማሰባሰብ ይህንኑ ወይይት ቢያዘጋጅም፣ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚቻል ደረጃ የስብሰባው ተሳታፊ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳታቸውን ያነጋገርናቸው የፓርቲ አመራሮች ነገረውናል። 

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተወካዮች፣ ኢትዮጵያ ከሰላምና ጸጥታ አንጻር አሁን ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ ነጻ እና ፍትሃዊ አገር ዓቀፍ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችላት ቁመና ላይ አይደለችም በማለት የምርጫ ቦርድ አመራሮችን እንደሞገቱ ከምንጮች ተረድተናል። 

አብዛኞቹ ፓርቲዎች በተለይ በአማራ፣ ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች ያሉት የጸጥታ ሁኔታዎች ነጻ እና አሳታፊ ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ አይደሉም የሚል አቋም መያዛቸውን ተገንዝበናል። 

የፖለቲካ ምሕዳር

የምርጫ አስቻይ ከሆኑ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታዎች በተጨማሪ፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር መጥበቡ ፈተና እንደሆነባቸው በመግለጽ በቀጣዩ ምርጫ ላይ ጥያቄ ያነሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ነበሩ። 

የአባላት እስር እና ወከባን ጨምሮ የመንግሥት ጫና በርትቶብናል ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ፣ ከአባሎቻቸው ጋር እንኳ መገናኘት ባልቻሉበት ሁኔታ በቀጣዩ ምርጫ መሳተፍ በመቻላቸው ላይ ጥያቄ አንስተዋል። 

በውይይት መድረኩ ከተሳተፉት የፓርቲዎች አመራሮች መካከል ዋዜማ ያነጋገረቻቸው አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር፤ “ከቀጣዩ ምርጫ የምንሸሸው በምርጫው መሳተፍ ስለማንፈልግ ሳይሆን፣ በነባራዊ ሁኔታዎች ሳቢያ መሳተፍ ስለማንችል ነው” በማለት ገልጸዋል። 

የአገሪቱ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ ነጻ እና አካታች ምርጫ ለማካሄድ አይፈቅድም በሚል ቦርዱን ከሞገቱት ፓርቲዎች መካከል፣ በቀጣዩ ምርጫ አንሳተፍም በሚል ተፈራርመው የጋራ አቋም ለመያዝ ንግግር የጀመሩ ፓርቲዎች መኖራቸውን ምንጮች ጠቁመዋል። 

አብዛኞቹ የውይይቱ ተሳታፊ ፓርቲዎች ያለ ልዩነት በጋራ ያንጸባረቁት አቋም፣ በተለይ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ አለመኖሩን በመግለጽ በቅድሚያ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱትን የሰላምና ጸጥታ ችግሮች መፍታት ያስፈልጋል የሚል እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። 

ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎቹ ከሰላም እና ጸጥታ ጋር በተያያዘ ያነሷቸውን ስጋቶች እንደሚጋራ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወረቅ ኃይሉ መግለጻቸውን የመድረኩ ታዳሚ ምንጮች ገልጠውልናል። 

ይሁን እንጂ፣ ቦርዱ ሁኔታዎች እስከፈቀዱለት ድረስ በሕገመንግሥቱ መሰረት የተሰጠው በየአምስት ዓመቱ አገር ዓቀፍ ምርጫ የማካሄድ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚቀጥል ሰብሳቢዋ ለፓርቲዎቹ ተወካዮች ማስረዳታቸውን ምንጮች ነግረውናል። 

ቦርዱ በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ በሰጠው ማብራረያ፣ እስካሁን ባለው የምርጫ ቅድመ ዝግጅት በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ አለመቻሉን እና በአንጻሩ በሌሎች ክልሎች አንዳንድ ለቅድመ ምርጫ ዝግጅት የሚረዱ የዳሰሳ ጥናቶችን ማድረጉን ገልጿል። 

ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ ውጪ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው በዚሁ የምርጫ ማካሄጃ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ስምምነቱን የገለጠ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ አለመኖሩን ተገንዝበናል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ተወካይ በበኩላቸው፣ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው የጊዜ ሰሌዳ ወደ ቀጣዩ ክረምት የተጠጋ ነው በማለት ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው እንዲሻሻል መጠየቃቸውን ሠምተናል። 

ቦርዱ ባቀረበው ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ግንቦት 24፣ 2018 ዓ፣ም እንዲካሄድ መታቀዱን ምንጮች ጠቁመዋል። 

ምርጫው በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንደሚሆን ያስረዱት የምርጫ ቦርድ አመራሮች፣ በሰላምና ጸጥታ እጦት ዙሪያ የተነሱትን የአስቻይነት ጥያቄዎች በቴክኖሎጂ በተደገፈ አሠራር ለማቃለል ቦርዱ ጥረት እንደሚያደርግ ገልፀዋል። 

ይሄው ወይይት በቦርዱ እቅድ መሠረት ዋነኛ ትኩረቱን በምርጫ ማካሄጃው ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ማድረጉ ቀርቶ፣ በምርጫ ማካሄጃ አሳቻይ ሁኔታዎች መኖር አለመኖር ላይ በማተኮሩ፣ ቦርዱ በጊዜ ሰሌዳው ላይ ያተኮረ ሌላ የውይይት መድረክ እንደሚያዘጋጅ ለፓርቲዎች ተናግሯል። 

ፓርቲዎቹ በመድረኩ ላይ ካቀረቧቸው ሌሎች ጉዳዮች መካከል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩ ተመራጮች የድጋፍ ፊርማ ማስባሰብ ጉዳይ አንዱ እንደሆነ ተነግሯል። በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ቀርቶ የነበረው የፓርቲ እጩዎች የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ፣ በሰባተኛው ምርጫ እንደገና ተግባራዊ መሆን ይጀምራል መባሉን ፓርቲዎች እንደተቃወሙት ተገልጧል። 

በስድስተኛው ዙር ምርጫ ወቅት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተግባራዊ ያልተደረገው የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ የማሰባሰብ ድንጋጌ፣ አገር ዓቀፍ እጩዎች 10 ሺህ እንዲሁም የክልል ዓቀፍ እጩዎች 4 ሺሕ የድጋፍ ፊርማዎችን በቅድሚያ ማሰባሰብ እንዳለባቸው ያስገድዳል። 

አገራዊ ምክክር

ሌላኛው በመድረኩ የተነሳው ጉዳይ፣ ብዙ ነገሮችን ይቀይራሉ ተብለው የታሰቡ አጀንዳዎች የቀረቡለት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አገራዊ ምክክሩን ከቀጣዩ አገር ዓቀፍ ምርጫ በፊት ማጠናቀቅ መቻል አለመቻሉን የሚመለከት እንደሆነ ታውቋል። 

አንዳንድ የውይይቱ ተሳታፊ ፓርቲዎች፣ አገራዊ ምክክሩ በስኬት ከተጠናቀቅ ብዙ የሚቀይራቸው ነገሮች ስለሚኖሩ፣ ቀጣዩን ምርጫ አራዝሞ ምክክሩ የሚያመጣቸውን ለውጦች መጠበቅ ይበጃል የሚል አቋም ማንጸባረቃቸው ተገልጧል። 

ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፣ ምርጫውን አራዝሞ አገራዊ ምክክሩ የሚቀይራቸውን ለውጦች መጠበቅ ይሻላል በሚል ፓርቲዎች ያቀረቡትን ሀሳብ እንደማይቀበል በመድረኩ ላይ አቋሙን መግለጡን ከምንጮች መረዳት ችለናል። 

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ መንግሥት ቀጣዩን አገር ዓቀፍ ምርጫ በሕገ-መንግስቱ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ለማካሄድ ቁርጠኛ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በፌደሬሽን ምክር ቤት የዓመቱ የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ላይ ገልጠው ነበር። 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ የአብላጫ ድምጽ ሥርዓትን የሚከተለው የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት እንዲተካ በአጀንዳነት ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቅረቡን መረዳቱን በመግለጽ፣ ቀጣዩ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የምርጫ ሥርዓቱ ጉዳይ መፍትሄ በሚያገኝበት ሁኔታ ላይ ባለ ድርሻ አካላት ውይይት እንዲያደርጉበት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ መጠየቁ ይታወሳል። [ዋዜማ]