ዋዜማ- በበይነ መረብ የተንቀሳቃሽ ምስል ይዘቶች ማሠራጫ የሆነው ዩቲዩብ ኩባንያ፣ በዩትዩብ ላይ ይዘቶችን በማሰራጨት ገቢ ለሚያገኙ የይዘት ፈጣሪዎች አዲስና ጥብቅ መመሪያ ማውጣቱ ተሰምቷል።
መመሪያው ከፊታችን ሐምሌ 8፣ 2017 ዓ፣ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንና በውስጡም ዩትዩብ ከእንግዲህ ክፍያ የሚፈጽምባቸው ይዘቶች በሌሎች የይዘት ፈጣሪዎች በብዛት ጥቅም ላይ ያልዋሉ፣ አዲስና እውነተኛነታቸው የተረጋገጡ መሆን እንዳለባቸው የሚያስገድድ ሕግ የያዘ ነው ተብሏል።
ይህ የፖሊሲ ማሻሻያ፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የሚሠራጩ ይዘቶችን ከዩቲዩብ የክፍያ ስርዓት የሚያስወጣ እንደሆነ ታውቋል።
ማሻሻያው፤ ኩባንያው በዩትዩብ ቪዲዮዎች ላይ ከሚተላለፉ ማስታወቂያዎች የሚያገኘውን ገቢ ከይዘት ፈጣሪዎች ጋር ለሚጋራበት “ዩቲዩብ ፓርትነር ፕሮግራም” ለተሰኘው ስርዓት ብቁ በሚሆኑ ቪድዮዎች ላይ ያስቀመጠውን መስፈርት በእጅጉ ያጠበቀ ነው።
ዩትዩብ ኩባንያ፣ የይዘት ፈጣሪዎች ለዚህ ፕሮግራም ብቁ ሆነው ክፍያ እንዲፈጸምላቸው የራሳቸው ቪድዮዎችን እንዲለቅቁ እንደሚያስገድድ ከዚህ ቀደም አስታውቆ ነበር። ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ደሞ፣ ለዚህ መስፈርት ቁጥጥር የሚያደርግበትን አሰራር እንደሚያሻሽል የገለጸ ሲሆን፣ አዲሱ ማሻሻያ የሚደረገው በብዛት አየር ላይ የዋሉ እና ተደጋጋሚ ይዘቶችን በተሻለ ሁኔታ ለመለየት እንደሆነ ኩባንያው አብራርቷል።
አንድ በዩትዩብ የበይነ መረብ ይዘቶችን የሚያሠራጭ የይዘት ፈጣሪ ለዩትዩብ የገንዘብ ክፍያ ብቁ ለመሆን፣ በቅድሚያ 1 ሺህ ሰብስክራይበሮች ወይም ተከታይ እንዲሁም በ12 ወራት ውስጥ 4 ሺሕ የዕይታ ሰዓቶች ማግኘት አለበት የሚለው መስፈርት ግን ባለበት እንደሚቀጥል ዩትዩብ አስታውቋል።
አዲሱ የዩትዩብ ፖሊሲ ከክፍያ ስርዓቱ ከሚያስወጣቸው ቪድዮዎች ውስጥ፤ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተፈጠሩ ይዘቶች፣ በተለይም በድምጾች ላይ የሚመረኮዙ ወይም በአነስተኛ የቪዲዮ የአርትዖት ሥራ በድጋሚ የሚጫኑ የሌሎች ሰዎች ይዘቶች እንደሚገኙበት ተነግሯል።
የፖሊሲ ለውጡ በዋናነት ዒላማ ያደረገው፣ ብዙ ጥረት ሳይደረግባቸው የሚሠራጩና የይዘት ፈጣሪው ትክክለኛ የሥራ ውጤት መሆናቸው ያልተረጋገጡ የቪዲዮ ይዘቶችን ነው።
ከክፍያ ሥርዓቱ ከሚወጡት መካከል፣ መልሰው መላልሰው ጥቅም ላይ የዋሉ ይዘቶችና በሌሎች የይዘት ፈጣሪዎች ይዘቶች ላይ በቪዲዮ የሚሰጡ አስተያየቶች ወይም በእንግሊዝኛው ‘ሪያክት” የሚያደርጉ ይገኙበታል። ቀደም ሲል በቪዲዮ የተሠራጩ ይዘቶችን በሰው ሠራሽ አስተውሎት በተቀነባበረ ድምጽ መልሶ ማቅረብ፣ ገቢ ማስገኘቱ ይቀራል ።
የፖሊሲ ለውጡ ዋና ዓላማ፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ክህሎታቸውን ሰውተውና ባንድ የቪዲዮ ይዘት ላይ የራሳቸውን ሃሳቦችና ትንተናዎች ጨምረው የሚሠሩ የይዘት ፈጣሪዎችን ማብረታታት እንደሆነ ተነግሯል። ቀደም ሲል በዩትዩብ ላይ በተጫነ ቪዲዮ ላይ በዋናነት የተመረኮዙ ይዘቶች ሲያጋጥሙ፣ ምንም እንኳ ከዩትዩብ ክፍያ ለማግኘት ዋስትና የሚሰጥ ባይሆንም ዩትዩብ ግን የይዘት ፈጣሪው የራሱን ሃሳብ እንዲጨምርበት፣ የራሱን ድምጽ እንዲጠቀም ወይም የራሱን የፈጠራ ክህሎት እንዲያክልበት ሊጠይቅ ይችላል ተብሏል።
እነዚህን መስፈርቶች የማያሟሉ የቪዲዮ ማሠራጫዎች፣ ከዩትዩብ ምንም ማስጠንቀቂያ ሳይደርሳቸው ሊታገዱ እንደሚችሉም ታውቋል። [ዋዜማ]