ዋዜማ- የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አንድ ኮሚሽነር በራሳቸው ፍቃድ ከኃላፊነት መልቀቃቸውን ዋዜማ ከኮሚሽኑ ምንጮች ሰምታለች።

ከ11ዱ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች መካከል ሥራቸውን በፍቃዳቸው የለቀቁት ተገኘወርቅ ጌቱ መሆናቸውን ምንጮች ጠቁመዋል። ተገኘወርቅ ኃላፊነታቸው በገዛ ፍቃዳቸው የለቀቁት፣ የኮሚሽኑ አጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ከተጀመረ በኋላ ነው።

ኮሚሽነሩ የምክክር ኮሚሽኑ ሥራውን ሳያጠናቅቅ ኃላፊነታቸውን የለቀቁት “ይበቃኛል” በሚል ምክንያት መሆኑን ዋዜማ ተረድታለች። ተገኝወርቅ ኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ባቀረቡት በዚሁ ምክንያት ላይ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኮሚሽኑ በሰጠው የሥራ ጊዜ ልክ ማገልገላቸው በቂ መሆኑን መጥቀሳቸውን ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የኮሚሽኑ ምንጮች ጠቁመዋል።

ተገኘወርቅ ኃላፊነታቸውን የለቀቁት፣ የኮሚሽኑ የሦስት ዓመት የሥራ ዘመን በተጠናቀቀበት ወቅት መሆኑን የዋዜማ ምንጮች ተናግረዋል። ኮሚሽኑ በመቋቋሚያ አዋጁ የተሰጠውን የሦስት ዓመት ጊዜ አጠናቆ ተጨማሪ የአንድ ዓመት ጊዜ የተጨመረለት ባለፈው የካቲት 2017 ዓ፣ም ነው።

ተገኘወርቅ ከኮሚሽኑ አባልነታቸው ከመልቀቃቸው ቀደም ብሎ፣ የመሰላቸት ስሜት ይንጸባረቅባቸው እንደነበር በቅርበት የሚያውቋቸው ምንጮች ነግረውናል። ተገኝወርቅ ቀድሞውኑም ኃላፊነቱን የተቀበሉት “አገሬን ከችግር አረንቋ ለማውጣት የበኩሌን ድርሻ እወጣለሁ” በሚል እምነት መሆኑን ከመልቀቃቸው በፊትም ሲገልጡ እንደነበር ምንጮች አመልክተዋል።

በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1265/2014 ኮሚሽነሮች በገዛ ፈቃዳቸው ከሃላፊነት መልቀቅ እንደሚችሉ ተደንግጓል። በአዋጁ ላይ፣ “ማንኛውም ኃላፊነቱን በገዛ ፍቃዱ መልቀቅ የሚፈልግ ኮሚሽነር፣ የሁለት ወር የጽሁፍ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለኮሚሽነሮች ምክር ቤት እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በማስገባት ሊለቅ ይችላል” ተብሎ ሠፍሯል።

በዚሁ አዋጅ መሠረት፣ አንድ ኮሚሽነር ከኃላፊነት ሲነሳ ወይም ሲለቅ ወይም በሞት ምክንያት ሲለይ አዲስ ተሿሚ ይተካል። የተተኪ ኮሚሽነር ሹመትም የሚሰጠው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን፣ ተተኪው ከዚህ ቀደም ተጠቁመው በኮሚሽነርነት ካልተሾሙ ዕጩዎች መካከል ተመርጦ እንደሚሾም ተደንግጓል። ምንም እንኳ ተገኘወርቅ ኃላፊነታቸው አስረክበው ከተሰናበቱ ጥቂት ወራት ቢቆጠሩም፣ ይህ ዘገባ እሰከተጠናቀረበት ዕለት ድረስ በአዲስ ኮሚሽነር አልተተኩም።

አዋጁ በሚፈቅደው አሠራር መሠረት ለምን ተተኪ ኮሚሽነር እንዳልተሾመ የጠቅናቸው የኮሚሽኑ ምንጮች፣ እስከአሁን ባለው ሂደት አስፈላጊ ነው ተብሎ ትኩረት ስላልተሰጠው እንደሆነ ጠቁመዋል። በሥራ ላይ ያሉት ኮሚሽነሮች፣ በተገኘወርቅ ቦታ አዲስ ኮሚሽነር እንዲተካ እምብዛም ፍላጎት አላሳዩም ተብሏል።

የኮሚሽኑ የበላይ ተቆጠጣሪና የኮሚሽነሮች ሹመት ሰጪ በሆነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል ያለው አቋምም ተመሳሳይ መኾኑን ምንጮች ጠቁመዋል። የምክክር ኮሚሽኑ በዚሁ አጀንዳ በማሰባሰብ ምዕራፍ ላይ እያለ ከተሰጠው የአንድ ዓመት ማራዘሚያ ጊዜ ውስጥ አንድ አራተኛውን አገባዷል። [ዋዜማ]