Alemu Sime, Minster of Transport and Logistics

ዋዜማ- ከዚህ ቀደም የክልልሎችን እና የከተማዎችን ስም ይዞ ይታተም የነበርውን ሰሌዳ የሚያስቀር አዲስ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ተግባራዊ ሊደረግ ነው። አዲሱ ሰሌዳ የተሽከርካሪውን እና የአሽከርካሪውን(የባለንብረቱን) መረጃ የያዘ “ቺብስ” የተገጠመለት እንደሚሆን የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል። 

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አዲሱን ሰሌዳ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችለውን “የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሠሌዳ ዓይነቶችና ምልክቶች መወሰኛ እና የአገልግሎት አሰጣጥ” የተሰኘ መመሪያን አጽድቋል። ቀደም ሲል የነበረው የተሽከርካሪ መለያ ቁጥር ሠሌዳ አመራረት እና አሰረጫጨት የአሠራር ክፍተት የነበረበት መሆኑ በመመሪያው ላይ ተብራርቷል። 

“በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚመጣውን የሠሌዳ ጥሬ ዕቃ በአግባቡ በመጠቀም የመንግሥትን ሀብት ከብክነት ለመታደግ” መመሪያው ተዘጋጅቷል ተብሏል።

በመላው ሀገሪቱ በተመዘገቡና ለምዝገባ በሚቀርቡ ተሽከርካሪዎች ላይ ተፈጻሚ የሚሆነው አዲሱ መመሪያ፤ ካሁን በፊት የነበረውን አሠራር በመለወጥ እስካሁን በሀገሪቱ ውስጥ የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሠሌዳ ለውጥ እንደሚያደርጉ እና እንደ አዲስ እንደሚመዘገቡ ያትታል። 

ወደፊት የሚመዘገቡ ተሽከርካሪዎችም “በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነና ተከታታይነት ያለው የመለያ ቁጥር ሠሌዳ እንዲኖራቸው” እንደሚደረግ ተብራርቷል።  አዲሱ የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሠሌዳ ዓይነቶችና ምልክቶች መወሰኛ እና የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ፤ ሁሉም ተሸከርካሪዎች የሚለጥፉት የመለያ ቁጥር ሠሌዳ ላይ “የኢትዮጵያ ካርታ” እንደሚኖረው ያብራራል። 

“ሀገሪቱ ባጸደቀችው ዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት የተሰጣትን ሀገራዊ ልዩ ምልክት “ETH” እንዲሁም “ኢት” የሚል የግእዝ ፊደላት እና የላቲን ፊደላት ይዘት እንዲኖረው” ይደረጋል ተብሏል። የሁሉም ሠሌዳዎች መደባቸው ነጭ ሆኖ ፊደላቱ እና ቁጥሮቹ በጥቁር ቀለም” እንደሚጻፉ በመመሪያው ላይ ተመልክቷል። በኤሌክትሪክ ወይም በሌሎች ታዳሽ ኃይሎች የሚሠራ የተሽከርካሪ የመለያ ቁጥር ሠሌዳ ግን መደቡ ነጭ ሁኖ ጽሑፉ አረንጓዴ ቀለም እንደሚሆን ተገልጿል።

በአዲሱ መመሪያ የአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ራሱን የቻለ መለያ እንዲኖረው እንደሚደረግ ተጠቁሟል። በዚህ መሰረት “ የአካል ጉዳተኛ ተሽከርካሪ የመለያ ቁጥር ሠሌዳ ነጭ መደብ ከጥቁር ፊደላትና ቁጥሮች ጋር የያዘ ሆኖ፤ ከተሸከርካሪው አካል ላይ ከፊት እና ከኋላ የዊልቸር ምልክት፣ PD የሚል የላቲን እና አ.ጉ የሚል የግዕዝ ምሕፃረ ቃላትን” እንደሚይዝ ዋዜማ ከሰነዱ ላይ ተመልክታለች።

በዚህ መልኩ ተዘጋጅቶ ለአገልግሎት እንደሚበቃ የተነገረለት አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ከዚህ ቀደም በክልል እና በከተማ ስያሜ የሚታተመውን የሚያስቀር መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ዶ/ር አለሙ ስሜ ተናግረዋል። ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ሚያዚያ 24/2017 ዓ.ም የተቋሙ  የ 9 ወር የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ ላይ ነው። “ሰሌዳ አንድን መኪና ከሌላ መኪና መለያ እንጂ የክልል ባሕል መግለጫ አይደለም” ሲሉ ዶ/ር አለሙ ስሜ በአፅንኦት ተናግረዋል። 

ሚኒስሩ አክለውም “[ሰሌዳው ላይ] ክልል የሚለይ[ጽሁፍ] አንጽፍም” በማለት ተናግረዋል።አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ላይ የሚታተመው የክልል ስያሜ ቀረ ማለት ክልሎች ከተሽከርካሪዎቹ ያገኙት የነበረው የአገልግሎት ገቢ ይቀራል ማለት እንዳልሆነ ዓለሙ ስሜ አስረድተዋል። እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ከሆነ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው ሰሌዳ ከተሽከርካሪው ላይ መፈታት እንዳችል ሆኖ የሚመረት ነው። ይህ የአንዱን መኪና ታርጋ አንዱ መኪና ላይ መለጠፍ  እንዳይቻል  ያደርጋል ተብሏል። 

አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ላይ “የሞተር ቁጥር” ፣ “የአሽከርካሪው አድራሻ” እና ሌሎች መረጃዎችን የያዘ ችብስ እንደሚኖረው ዋዜማ መረዳት ችላለች። ይህን መረጃ ከተፈቀደለት አካል ውጭ መመልከት ማንም ሊመለከተው የማይችል መሆኑንም ዶ/ር ዓለሙ አብራርተዋል። 

“ሰሌዳው ሲመረት ለቁጥጥር እና ለምዝገባ ዓላማ የሚያገለግሉ መረጃዎችን የሚሰጡ ምሥጢራዊ ምልክቶችን እያንዳንዱ የሠሌዳ ዓይነት የያዘ” እንደሚሆን በተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሠሌዳ ዓይነቶችና ምልክቶች መወሰኛ እና የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ይገልጻል። ልዩ መግለጫ ያለው የተለየ የመለያ ቁጥር ሠሌዳ የሚጠይቅ  ሰው ሚኒስቴሩ እንደሁኔታው በልዩ ሁኔታ ሊሰጥ እንደሚችልም ተመላክቷል። [ዋዜማ]