ክልሉ ከሚያስፈልገው ዕርዳታ 71 ቢሊየን ብር ያህሉ ለምግብ አቅርቦት የሚያስፈልግ ነው
ዋዜማ- በአማራ ክልል በተፈጥሮ እና ሰውሰራሽ አደጋዎች ለደረሰው ጉዳት “የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ” እና “ምላሽ” ለመስጠት ክልሉ 102 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው የክልሉ የአደጋ ሥጋት መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ለዋዜማ ተናግሯል።
በአማራ ክልል ወደ ሁለት ዓመት እየተጠጋ ባለው ግጭት ሳቢያ ከ 140 ሺህ በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንና ከ 36 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን፤ በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ብርሃኑ ዘውዱ ገልጸዋል።
እንደ አቶ አብርሃኑ ገለጻ ከሆነ፤ በግጭቱ ሳቢያ ከ 170 ሺህ በላይ የክልሉ ነዋሪ ተፈናቅሎ እንደነበር አስረድተዋል። ከነዚህ ተፈናቃዮች ውስጥ “የተወሰኑት ወደ ቀያቸው በመመለሳቸው” አሁን ላይ ያለው የተፈናቃይ ቁጥር 140 ሺህ እንደሚጠጋ ለዋዜማ ነግረዋታል። ሆኖም በምዝገባ ያልተካተቱ ተፈናቃዮች ስለሚኖሩ የተፈናቃይ ቁጥሩ ከፍ ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን እንደሚችል አብራርተዋል።
“ያልተመዘገቡ እና ከገጠር አካባቢዎች ለቅቀው ከተማ እየኖሩ ያሉ ብዙ [ተፈናቃዮች] አሉ። ልትመዘግባቸው በማትችላቸው ሁኔታ ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮች ብዙ አሉ። 140 ሺህ ሲባል ትንሽ ሊመስል ይችላል። ግን ብዙ የተፈናቀሉ አሉ። ክልሉን ለቀው አዲስ አበባ የመጡ አሉ” በማለት አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።
ከተፈናቃዮቹ ውስጥ ቤት እና ንብረታቸው የተቃጠለባቸው እንዳሉ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። በክልሉ ባለው ግጭት ከ 36 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን ዋዜማ መረዳት ችላለች። እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ በዚህ ውድመት ምክንያት ከ 90 ሺህ በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅውለዋል። ይህ ውደመት በተለይ በአዊ ዞን የተከሰተ መሆኑንም አብራርተዋል።
“በተፋላሚ ቡድኖች መካከል የማህበረሰብ ተሳትፎ አለ። ይሄኛን እና ያኛውን ቡድን በሚደግፋ አካላት መካከል interest አለ። በዚህ መካከል ብዙ ቤቶች ተቃጥለዋል ከ 36 ሺህ በላይ ቤቶች ነው የተቃጠሉት። መኖሪያ ቤቶች። ለምሳሌ አዊ ዞንን ብትወስድ ከ 90 ሺህ የሚሆን ሰው ተፈናቅሏል። የዚያ አካባቢ ቤቶች እንዳለ ነው የነደዱት” በማለት በግጭቱ ስለወደሙት መኖሪያ ቤቶች አብራርተዋል።
በፋኖ እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ውጊያ፤ በነዋሪዎች ላይ እያሳደረ ካለው ዳፋ በተጨማሪ እንደ ትምህርት ቤት፣ የጤና ተቋማት፣ በውኃ እና በሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
በዚህ ረገድ በአማራ ክልል በተፈጥሮ እና ሰውሰራሽ አደጋዎች ለደረሰው ጉዳት “የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ” እና “ምላሽ” ለመስጠት ክልሉ 102 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው አቶ ብርሃኑ ለዋዜማ ገልጸዋል። ይህ የገንዘብ መጠን ከተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር በጋራ የተጠና መሆኑንም አክለዋል።
ክልሉ ያስፈልገዋል ከተባለው ገንዘብ ውስጥ ከ 71 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ለምግብ ድጋፍ የሚውል ነው። በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና እና የትምህርት ተቋማት ለመገንባት ደግሞ ከ 20 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚጠይቅ ዋዜማ ከኮሚሽኑ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
በአማራ ክልል በፋኖ ኃይሎች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል ውጊያ የተጀመረው፤ በ2015 መጨረሻ ነበር። በወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ሐምሌ 27/2015 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጻፉት ደብዳቤ፤ ያጋጠመውን የጸጥታ መደፍረስ ክልሉ መቆጣጠር እንዳዳገተው መግለጻቸው ይታወሳል። ዶ/ር ይልቃል በደብዳቤያቸው የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ እና ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድም ጥያቄ አቅርበው ነበር።
የቀድሞ ርዕሰ መስተዳደር ለፌድራል መንግስት ጥሪ ካቀረቡ ከ 1 ቀን በኋላ፤ የሚንስትሮች ምክር ቤት የሕዝብን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ውሳኔ ማስተላለፉ አይዘነጋም። በዚህ ሒደት የመከላከያ ሰራዊት ወደ ክልሉ በመግባት ከፋኖ ኃይሎች ጋር እየተዋጋ ይገኛል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስካሁን የቀጠለው ውጊያ ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ማድረሱን አቶ ብርሃኑ ለዋዜማ ገልጸዋል።
ከግጭቱ በተጨማሪ እንደ ድርቅ፣ ወረርሽኝ እና የመሬት መንሸራተት ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት መሆናቸውን አስረድተዋል። በባለፈው የክረምት ወር በክልሉ 6 ዞኖች ባጋጠመ የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋ የተፈናቀሉ 3,445 ሰዎች መኖራቸውን ዋዜማ የክልሉ የአደጋ ሥጋት መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ሆኖም ለዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል ከተፈጥሮ አደጋ በላይ ሁለት ዓመት የተጠጋው ግጭት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። [ዋዜማ]