Map of Gurage Zone

ዋዜማ- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን  ከባለፈው ዓመት መጨረሻ  ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙ “የአማራ ብሔር ተወላጆች በፍርድ ቤት ውሳኔ ሳያገኙ” ሰባት ወራት እንደሞላቸው ለዋዜማ ተናግረዋል። 

እነዚሁ ግልፅ ባልሆነ ውንጀላ በእስር ላይ የሚገኙት ዜጎች “በጸጥታ ኃይሎች በሚደርስባቸው ድብደባ ለአካል ጉዳት” መጋለጣቸውም ለዋዜማ ነግረዋታል።

በጉራጌ ዞን “የአማራ ብሔር ተወላጅ” በሆኑ ነዋሪዎች ላይ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት እስር የተጀመረው ከባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ እንደሆነ ዋዜማ ታስረው ከተፈቱና ከሌሎች ታሳሪዎች ቤተሰቦች ስምታለች።

የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በቀበሌዎቹ የሚኖሩ “የአማራ ብሔር ተወላጆችን ‘ፋኖን ታሰለጥናላችሁ’፣‘ትደግፋላችሁ’፣ ‘የፋኖ ክንፍ ናችሁ’ ”  በሚል ምክንያት ከመኖሪያ ቤት እና ከስራ ቦታ ወስደው እንዳሰሯቸው ነዋሪዎች ነግረውናል።

በዞኑ በወልቂጤ ከተማ ሁለገብ አዳራሽ ውስጥ በባለፈው የክረምት ወር ከ 100 በላይ የአማራ ክልል ተወላጆች  ታስረው የነበረ ቢሆንም፤ “ገንዘብ የመክፈል አቅሙ ያላቸው እስረኞች ለመርማሪዎች እና ለፖሊስ አባላት እስከ 50 ሺህ ብር ጉቦ በመክፈል” ከእስር እንደተለቀቁ ዋዜማ የደረሳት መረጃ ያመላክታል።

 አሁን ላይ  በአዳራሹ 80 የሚጠጉ ሰዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል። በእነዚህ እስረኞቹ ላይ የጸጥታ ኃይሎች በሚወስዱት እርምጃ ለአካል ጉዳት የተጋለጡ መኖራቸውን ዋዜማ ከታሳሪዎች ሰምታለች።

በጉራጌ ዞን በአበሽጌ  ወረዳ ስር በሚገኙ ዋልጋ እና  ዳርጌ ቀበሌዎች  አሁን ድረስ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች መኖራቸውንም አክለዋል።

“[ታሳሪዎችን] መያዝ የተጀመረው ከሐምሌ ወር ጀምሮ ነው። በጣም ቆይቷል። በከፍተኛ ሁኔታ ስቃይ ውስጥ ነን” ሲል ከሐምሌ ወር ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኝ ምንጭ በጸጥታ ኃይሎች ይደርስብናል ያለውን የመብት ጥሰት አስረድቷል። 

“የታሰሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ወንጀል ሰርተው ሳይሆን አማራ ብቻ ስለሆኑ ነው” በማለት ለእስር የተዳረጉበትን ምክንያት አክሏል በእስር ላይ ያለው ምንጭ።

አሁን ላይ በእስር ከሚገኙት በተጨማሪ በስጋት ምክንያት የመኖሪያ አካባቢያቸውን ጥለው የወጡ በርካታ የአማራ ብሔር ተወላጆች መኖራቸውን የገለጸው፤  በጉራጌ ዞን ሲካሔድ የቆየውን እስር ፍራቻ  ቤት እና ንብረቱን ጥሎ የሸሸ አንድ ሌላ ነዋሪ ነው ። በባለው ሳምንት ወደ ቀድሞ መኖሪያው እንዲመለስ ከአካባቢው ሽማግሌዎች በስልክ ጥሪ እንደደረሰው ይኽው ምንጭ ለዋዜማ ተናግሯል። 

“እስሩን ሽሽት እንደኔ አምልጦ የወጣ በጣም ብዙ ሕዝብ አለ። እና ያም ሰው እንዲገባ ወደከተማ የሔደ፣ ወደጫካ የሔደ እንዲመለስ ተብሎ ነው[የተጠራነው]። ለምን እንደተጠራን አናውቅም፤ እርግጠኛ አይደለንም። ምን ዋስትና ኖሮኝ ነው የምመለሰው?” ሲል የደረሰውን ጥሪ በጥርጣሬ እንደሚመለከተው አብራርቷል።

ለበርካታ ዓመታት የቆየበት መኖሪያ ቤቱ  በጸጥታ ኃይሎች ታሽጎ እንደሚገኝ በመግልጽ እምነት አድሮበት ወደ አካባቢው እንደማይመለስ አስረድቷል።

በእስር ላይ የሚገኙ “የአማራ ብሔር ተወላጆች” ለመጨረሻ ጊዜ ጉራጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት ከአንድ ወር በፊት ታህሳስ 10 ላይ መሆኑን የታሰረበት ስፍራ እንዳይገለጽ የጠየቀ አንድ እስረኛ አስታውቋል። ከታሰሩበት የሐምሌ ወር ጀምሮ 12 ጊዜ ፍርድ ቤት ቢቀርቡም “ፍትህ አልተሰጠንም” ሲል ገልጿል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን “አማራ በመሆናችን ብቻ ለእስር ተዳርገናል” ያሉ ዜጎችን በተመለከተ የክልሉን እና የዞኑን አመራሮች ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። [ዋዜማ]