ዋዜማ- በፍትሕ ሚንስቴር ከደምወዝ ጭማሪ፣ ከቤት፣ ከትራንስፖርትና ከተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች አለመሟላት ጋር ተያይዞ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ 3 መቶ በላይ ነባርና ልምድ ያላቸው ዓቃቤ ሕጎች ከመስሪያ ቤቱ በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ዋዜማ ከታማኝ ምንጮቿ ሰምታለች።

ዋዜማ ያነጋገረቻቸው በተቋሙ ከስምንት ዓመታት በላይ ያገለገሉ ከፍተኛ ዓቃቤ ሕጎች እንደገለጹት፣ በነዚህ ስምንት ዓመታት ውስጥ የደምወዝ ማስተካከያ የተደረገው አንድ ግዜ በ 2012 ዓ.ም ነው ብለዋል።

እየተከፈላቸው ያለው ክፍያ ከተሰጣቸው ተልዕኮ፣ ኃላፊነትና ከወቅታዊው የኑሮ ውድነት አንጻር እጅቅ ዝቅተኛ ነው ሲሉ ለዋዜማ የገለጹት ባለሙያዎቹ፣ በዚህም ምክንያት ሙያውን ወደው እና አክብረው እንዳይሰሩ “እንቅፋት ሆኖብናል” ሲሉ ገልጸዋል።

ከደምወዝ በተጨማሪ የቤት እና የትራንስፖርት ክፍያ ማስተካከያ ከተደረገላቸው ዓመታት መቆጠራቸውን ያነሱ ሲሆን፣ ባለሞያዎቹ በተደጋጋሚ አመልክተው መፍትሄ አለማግኘታቸውን አንስተዋል።

ዓቃቤ ሕጎቹ ለረጅም ዓመታት ሲጠይቁ የነበረው ሌላ ጥያቄ የቤት ጥያቄ መሆኑን ለዋዜማ ያስረዱ ሲሆን፣ ተቋሙን በሚንስትርነት ሲመሩ ከነበሩትና በቅርቡ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆነው ከተሾሙት ጌዴዎን ጢሞቴዎስ አንስቶ ከሳቸው በፊት ለነበሩት ሚንስትሮችም ጥያቄው ሲነሳላቸው ነበር ሲሉ አክለዋል።

ሆኖም “ጥረት እያደረግን ነው፣ እየተነጋገርንበት ነው” ከሚሉ ማዘናጊያ ቃላት በዘለለ እስከ አሁን ድረስ ጥያቄያቸው መልስ አለማግኘቱን ተናግረዋል።

ዓቃቤ ሕጎቹ ለዋዜማ እንደገለጹት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በፍትሕ ሚንስቴር ትይዩ ያለ ተቋም መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ሆኖም በስሩ ላሉ ዳኞች በየካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ መገናኛ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የመኖሪያ ቤት ገንብቶ ማስረከቡን ጠቁመዋል።

ሆኖም ፍትሕ ሚንስቴር ከላይ የተገለጹትን ጥያቄዎች ባለመመለሱ የተነሳ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ 3 መቶ በላይ ዓቃቤ ሕጎች በራሳቸው ፈቃድ ከሥራ መልቀቃቸውንና፣ አሁንም መልቀቂያ እያስገቡ ያሉ በርካታ ዓቃቤ ሕጎች መኖራቸውን ይናገራሉ።

ከሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የለቀቁት ዓቃቤ ሕጎች በተቋሙ ውስጥ የረጅም ዓመታት ልምድ ያላቸው፣ ከባድ እና ውስብስብ የሚባሉ መዛግብት ሲሰሩ፣ ክርክር ሲያደርጉና ለውጤት ሲያበቁ የነበሩ ባለሙያዎች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ ሁሉ ሲሆን በመስሪያ ቤቱ በኩል ልምድ ያለው ባለሙያ ለቀቀ ብሎ የመቆጨት፣ የመቆርቆርና የመጸጸት አዝማሚያ አለማየታቸው እንዳሳዘናቸው የሚገልጹት ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ባለሙያዎች፣ ይህም በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን አደጋ ቀላል አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

ባለሙያዎቹ እንደገለጹት በርካታ የሚባሉ የወንጀል፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ይዘት ያላቸውን መዛግብት ላይ  ክርክር በማድረግ ከሥራ ሲወጡ ካለው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት የተነሳ በታክሲ መሳፈር ቅንጦት ስለሚሆን፣ እንደማንኛውን ዜጋ በከተማ አውቶቡሶች ተጋፍተን ነው የምንሄደው ሲሉ ለዋዜማ አስረድተዋል።

የእነሱ ሙያ ከሌላው የመንግሥት ሠራተኛ በብዙ ነገር እንደሚለይ የሚገልጹት ዓቃቤ ሕጎቹ፣ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ የግድያ፣ የስርቆት እና ሌሎችም የወንጀል መዛግብት ላይ እንደሚከራከሩ በመግለጽ፣ እነዚህ መዛግብትም በግል ሕይወታቸው ለጥቃት ሊዳርጓቸው የሚችሉና የደኅንነት አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ መሆናቸውን ያብራራሉ።

በጎረቤት አገራት ለዓቃቤ ሕጎች የሚከፈለው ክፍያና ጥቅማጥቅም እንዲሁም ለሙያው የሚሰጥው ክብር ከእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር፣ ልዩነቱ የሰማይና የምድር ነው የሚሉት ባለሙያዎቹ፣ በዚህም ምክንያት ተቋሙ በርካታ ሠራተኞችን አጥቷል ብለዋል።

ፍትሕ ሚንስቴር በስሩ ከ 650 በላይ ዓቅቤ ሕጎች እንዳሉት የሚገልጹት የዋዜማ ምንጮች አሁን ላይ የለቀቁትን ነባርና ልምድ ያላቸው ዓቃቤ ሕጎች እየተኩ ያሉት ጀማሪ በሙያው ብዙም ያልቆዩና ልምድ የሌላቸው ናቸው ሲሉ አክለዋል።

ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የሚንስቴር መስሪያ ቤቱን ምላሽ ለመጠየቅ በቢሮ ስልክና ጉዳዩ በሚመለከታቸው ሰዎች የእጅ ስልክ በተደጋጋሚ ደውላ የነበር ቢሆንም ስልካቸው ባለመነሳቱ ለጊዜው ሃሳባቸውን ማካተት አልተቻለም። [ዋዜማ]