ዋዜማ- የሕዳሴው ግድብ በሚገኝበት ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን የሚገኙ አምስት ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ካገኙ ሰባት ዐመት አልፏቸዋል።
በዞኑ በአብዛኛዋ ቦታዎች ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ኤሌክትሪክ ኃይል የተቋረጠ ሲሆን፣ በምዥጋ ወረዳ ብቻ እስካለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ድረስ ኤሌክትሪክ ኃይል ነበር። ሠዳል ወረዳም እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ እየተቆራረጠም ቢሆን ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኝ ነበር።
ዞኑ ኤሌክትሪክ እንዲያገኝ ጥገና ተደርጎ በ2015 ዓ.ም ላይ ለአንድ ሳምንት ብቻ ከቆየ በኋላ ተመልሶ ጠፍቷል። በዚህም የተነሳ በተለይ ዳምቤ፣ ምዥጋ እና ዛይ የሚባሉ ወረዳዎች ለረዥም ጊዜ የኔትወርክ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ አያገኙም። ስለሆነም ስልክ መደወል የሚፈልጉ የዛይ ወረዳ ነዋሪዎች ኔትወርክ ለማግኘት 72 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠበቅባቸዋል።
የመንግሥት ተቋማት አገልግሎቶችን ለመስጠት የጄኔሬተር ነዳጅ ወጪ ስላማረራቸው አብዛኛው አገልግሎቶች በእጅ ጽሑፍ ነው የሚደረጉት።
አምስቱም ወረዳዎች ቀድሞ መብራት ያገኙ የነበረው በአጎራባች የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በኩል ነበር ።
ከካማሽ ወረዳ በስተቀር ያሉት አራቱ ወረዳዎች ከፍተኛ የሆነ የውሃ እጥረት ችግርም እንዳለባቸው ዋዜማ ተረድታለች።
ካማሽ ዞን በክልሉም ሆነ በፌደራል መንግስታት ተረስቷል የሚሉት ነዋሪዎች፣ የመንገድም ሌላኛው ትልቅ ችግር መሆኑን አስተዋል።
የክረምት ወቅት መሆኑን ተከትሎ ከጥቅምት በፊት በነበሩት አራት ወራት ዞኑ እና ክልሉ አልተገናኙም። አሁንም ቢሆን ወደ አሶሳ የሚሄዱ የዞኑ ነዋሪዎች ወንዝ ሲደርሱ በእግራቸው የሚሻገሩ ሲሆን፣ ባለተሽከርካሪዎችም መኪናቸውን ተሸክመው በማሻገር ነው ከዞኑ ወደ ክልሉ ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ያለው። የዞኑ ነዋሪዎች ከካማሽ ወደ አሶሳ ለመሄድ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ምክንያት ቀድሞ የነበረውን መንገድ መጠቀም ካቆሙ ረዥም ጊዜ ሆኗቸዋል።
በወረዳዎች መካከል ያሉ የትራንስፖርት አገልግሎቶችም ውስን በመሆናቸው በተለይ ነፍሰ ጡር እናቶች ጤና ተቋም ሳይደርሱ ለሞት እንደሚዳረጉ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በዚህ ጉዳይ ያናገርናቸው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክር ቤት አባል ለሜሳ ኔኖ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም ይላሉ። የዞኑ ነዋሪዎች ከቴክኖሎጂ ጋር ጨርሶ እንደማይተዋወቁ እና ከተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ጋር ሲነጻጸር ካማሽ ጨለማ ውስጥ ያለ ዞን ነው ብለዋል።
በመተከል ዞን በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች እንዲሁ የኤሌክትሪክ መብራት ከጠፋ ኹለት ዓመት ገደማ ሆኖታል።
በመተከል ዞን ውስጥ ያሉት ድባጤ፣ ቡለን እና ወንበራ ወረዳዎች ኤሌክትሪክ ኃይል ካገኙ ኹለት ዓመት ገደማ ሆኗቸዋል።
በወረዳዎች ለሚገኙ የከተማ ነዋሪዎች ውሃ የሚቀርበው በፀሐይ (ሶላር) ኃይል ሲሆን፣ ጤና ተቋማት፣ የመንግሥት ቢሮዎችና ሌሎች ኃይል የሚፈልጉ ተቋማት ሶላር ወይም ጄኔሬተር መጠቀም ግድ ይላቸዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የድባጤ ወረዳ አመራር በወረዳዎቹ መብራት የጠፋው የተበላሹ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችን ለመጠገን መንገዱ አመች ባለመሆኑን ነው ብለዋል። ሆኖም ጥቂት ኪሎሜትሮች ብቻ በመቅረታቸው በቅርቡ ሶስቱም ወረዳዎች መብራት ያገኛሉ የሚል ተስፋ መኖሩን ነግረዋናል።
በኹለቱም ዞኖች ከዓመታት በፊት በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ጉዳት ደርሶ ነበር።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ጥገና አሁንም በብዙ ቦታዎች እየተሰራ ሲሆን፣ አስተማማኝ የጸጥታ ሁኔታ በሌለባቸው አካባቢዎች ግን ጥገናዎች እየተደረጉ አይደለም።
የዞኑን ዋና ከተማ ግልገልን ጨምሮ ሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎችም ተደጋጋሚ የመብራት መቆራረጥ መኖሩን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። [ዋዜማ]