ዋዜማ- ባንኮች ለሰራተኞቻቸው ለመኪናና ለቤት መግዣ በዝቅተኛ ወለድ ሰባት በመቶ ብድር ሲያገኙ ቆይተዋል። ይህ ማትጊያ በርካቶች የባንክ ዘርፉን እንዲቀላቀሉና በስራቸውም ላይ ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ ረድቷል። ዋዜማ ባለፉት ቀናት ባሰባሰበችው መረጃ ይህ ለአመታት የዘለቀ ማበረታቻ በገበያ ወለድ ተመን ተሰልቶ ልዩነቱ ግብር ይጣልበታል። የባንክ ስራተኞችም ለተበደሩት ገንዘብ የወለድ ልዩነቱ ደሞዛቸው ላይ ተሰልቶ ግብር እንዲከፍሉ ይገደዳሉ። ይህን ህግ ይዞ ብቅ ያለውና ባንኮችን እንዲያስፈፅሙ ያዘዘው የገቢዎች ሚኒስቴር ነው። ዋዜማ ያሰናዳችውን አስረጅ ዝርዝር ያንብቡት

የባንክ ሰራተኞች የባንክ ሰራተኛ ስለሆኑ ከሚሰሩባቸው ባንኮች ለቤት እና መኪና በአነስተኛ ወለድ የሚወስዱት ብድር ፣ ለወሰዱት ብድር የሚከፍሉት አነስተኛ ወለድ ከገበያው ወለድ ጋር ያለው ልዩነት ተሰልቶ የሚመጣው ልዩነት እንደ ገቢ ተቆጥሮ ግብር እንዲከፍሉ ሊደረግ መሆኑን ዋዜማ ሰምታለች። ይህም ከዚህ ወር ማለትም ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ሊሆን ዝግጅት እየተደረገ ነው ።

በገቢዎች ሚኒስቴር “የቅናሽ ወለድ የአይነት ጥቅም ላይ የሚከፈል ግብር” በሚል ሊተገበር የቀረበው ህግ በበርካታ የባንክ ሰራተኞች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል። ለዋዜማ አስተያየታቸውን የሰጡ የባንክ ሰራተኞችም “ህጉ የባንክ ሰራተኛ በመሆናችን የምናገኘውን ብቸኛ ጥቅም የሚነጥቀን ነው” ሲሉ ገልጸዋል።ዋዜማ “የቅናሽ ወለድ የአይነት ጥቅም ላይ የሚከፈል ግብር ” ስለተባለው ህግ ማብራሪያ ጠይቃ ተከታዩን መልስ አግኝታለች።

ንግድ ባንኮች በተለምዶ ለደንበኞቻቸው ብድርን ሲሰጡ ከ12 በመቶ በላይ ወለድ ያስከፍላሉ። ሆኖም ሰራተኞቻቸው ቤትና መኪናን መግዛት ሲፈልጉ የሚያበድሯቸው በሰባት በመቶ ወለድ ነው። ይህ ማለት ብሔራዊ ባንክ ለንግድ ባንኮች ቆጣቢዎች ያስቀመጠው ትንሹ የወለድ ምጣኔ ነው። ንግድ ባንኮችም ለሰራተኞቻቸው የሚሰጡት ዋነኛ ማትጊያ ሰራተኞቻው ቤትና መኪና መግዛት ሲፈልጉ በትንሹ መቆጠቢያ ወለድ ማለትም በሰባት በመቶ ማበደርን ነው።

የገቢዎች ሚኒስቴር በ2016 አ.ም በአነስተኛ ወለድ ብድር የሚያገኙ ሰዎች ፣ የቅናሽ ወለድ የአይነት ጥቅም ላይ የሚከፈል ግብርን መክፈል አለባቸው በሚል በዋነኝነት የባንክ ሰራተኞችን ኢላማ ያደረገ ህግ አወጣ። ይህ ማለት ፣ በሰባት በመቶ ወለድ ብድርን ያገኘ አንድ የባንክ ሰራተኛ በየወሩ የሚከፍለው ወለድ ፣ በገበያ ወለድ ቢበደር ኖሮ ሊከፍል ከነበረው ወርሀዊ ወለድ ላይ ተቀንሶ የሚመጣው ልዩነት ፣ የሰራተኛው ደሞዝ ላይ ተደምሮ ግብር እንዲከፍል ይገደዳል።

አንድ ሰራተኛ በሰባት በመቶው ወለድ ዋናውን ብድር ሳይጨምር በወር ስምንት ሺህ ብር ወለድ ይከፍል ከነበረና የገበያው ወለድ ደግሞ 14 በመቶ ከሆነ ፣ የባንክ ሰራተኛ ሊከፍል  የነበረው ወለድ 16 ሺህ ብር ነው ተብሎ ይታሰባል። ታዲያ ተበዳሪው የባንክ ሰራተኛ ስለሆነ ያልከፈለው ስምንት ሺህ ብር እንደገቢ ተቆጥሮበት ፣ እንደ ገቢ ደሞዙ ላይ ተደምሮ ግብር ይከፍላል ።

ሆኖም የገቢዎች ሚኒስቴር ይህን ህግ ሲያወጣ የገበያ ወለድ የሚባለው ላይ በባንኮች እና በሚኒስቴሩ መካከል ከመግባባት ላይ ባለመደረሱ ህጉ ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል።ሀምሌ ወር ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገበያ መር የወለድ አሰራርን እከተላለሁ ማለቱን ተከትሎ ፣ የፖሊሲ ወለዴም 15 በመቶ ነው በማለቱ ፣ባንኮችም ከሰራተኞቻቸው የቅናሽ ወለድ ጥቅም ግብርን ካበደሯቸው ሰራተኞች ልዩነቱን ለመሰብሰብ የብሔራዊ ባንኩን የ15 በመቶ አዲስ ዝቅተኛ የወለድ ተመንን እንደ ልኬት እንዲጠቀሙት ታዘዋል።

በዚህም መሰረት ንግድ ባንኮች በሰባት በመቶ ካበደሯቸው ሰራተኞች ላይ ፣ ከሚሰበስቡት ወለድ በተጨማሪ ሰራተኞቻው ቀሪ ስምንት በመቶ ወለዱን ቢከፍሉ ኖሮ የሚመጣባቸውን ገንዘብ እንደሰራተኞቻቸው ገቢ ቆጥረው ፣ይህንንም ያበደሯቸው ሰራተኞቻቸው ደሞዝ ላይ በመደመር ግብር ሰብስበው ለገቢዎች ያስተላለፋሉ ።

ይህ አሰራር ከዚህ ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን የተወሰኑ ባንኮች ከተለዋወጧቸው ደብዳቤዎች መረዳት ችለናል።ሆኖም በወለድ ልዩነቱ የባንክ ሰራተኞች የሚከፍሉት ወለድ ከአጠቃላይ ደሞዛቸው ከ10 በመቶ መብለጥ እንደሌለበትም ህጉ ያዛል።

ያነጋገርናቸው የተወሰኑ የባንክ ሰራተኞች እንዳሉንም የምንሰራበት ባንክ ያዋጣኛል ብሎ ለኛ ለሰራተኞቹ ብድር የሰጠበት አነስተኛ ወለድ በምንም መልክ እኛ ላይ እንደ ገቢ ሊቆጠር አይገባም ብለውናል።

የብሔራዊ ባንክ የወለድ ተመንም የዋጋ ንረትንና መሰል የማክሮ ኢኮኖሚ አላማዎችን ማስፈጸሚያ እንጂ በኛ ላይ ተግባራዊ ለሚሆን ህግ መነሻ መሆኑ ተገቢ አይደለም ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ፣ብሔራዊ ባንክ ነገ ከነገ ወዲያ የዋጋ ንረት ከፍተኛ ሆኖ የፖሊሲ ወለዴን ከ15 በመቶ ከፍ አድርጌ 18 በመቶ አድርጌያለሁ ቢል እኛ ምን ልንሆን ነው? ሲሉም ጠይቀዋል።

የግብር አሰራሩም አንድ ሰው ባንክ በመስራቱ የሚያገኘውን ጥቅም በእጅጉ የሚጎዳ እና ሰራተኛው በየወሩ እጁ ላይ የሚገባውን ደሞዝ የሚቀንስ ነው ብለውናል። [ዋዜማ]