ዋዜማ- የእናት ፓርቲ አመራሮች በድርጅቱ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ምርጫ ቦርድ ጣልቃ እንዲገባና ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቃቸውን ዋዜማ ተገንዝባለች።


ዋዜማ የተመለከተችውን በእናት ፓርቲ የላዕላይ ምክር ቤትና የስራ አስፈፃሚ አባላት ተፈርሞ ለምርጫ ቦርድ የገባ ደብዳቤ እንደሚያትተው የፓርቲው የተወሰኑ የስራ አስፈፃሚ አባላት ድርጅቱን “ለህዝባችን ስንል ከብልፅግና ፓርቲጋር እንሰራለን” ከሚል የስልጣን ፍላጎት ጀምሮ በተለያዩ የአሰራር ጥሰቶች ይከሳል።


የፓርቲውን መደበኛና ህጋዊ መዋቅር ወደ ጎን በመተው አዲስ አወቃቀር በመዘርጋት በፓርቲ ውስጥ “ጥያቄ የሚያነሱ” አባላትንና በማባረርና በማገድ አሁን ያለው አመራር የራሱን አዲስ አወቃቀር እየዘረጋ መሆኑንም የላዕላይ ምክር ቤት አባላት ያሉበት ቅሬታ አቅራቢ ቡድን ይናገራል።


በፋይናንስ አሰራርና በሰራተኛ ቅጥር ዙሪያ ብልሹ አሰራር ሰፍኗል የሚለው ቅሬታ አቅራቢ ቡድን ምርጫ ቦርድ ጣልቃ ገብቶ የኦዲት ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቋል።


አባላትም ፓርቲያቸውን ከመፍረስ እንዲታደጉና የተቋቋመበትን “የወግ አጥባቂነት” የፖለቲካ ርዕዮተ አለም ከግብ እንዲደርስ እንዲታገሉ ተማፅኗል።


የድርጅቱ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ አካሂዶ በችግሩ ላይ እንዳይመክርና እርምጃ እንዳይወስድ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ መንገድ በመዝጋት ጉባዔው እንዳይሳካ ማድረጉንም ደብዳቤው ያሰምርበታል።


ችግሩን በተመለከተ የድርጅቱ ምክር ቤት ለአባላት በፅሁፍ ማሳወቅ እንደጀመረና በቀጣይም መወስድ ባለበት እርምጃ ላይ እየተመካከረ መሆኑን አመልክቷል።


የእናት ፓርቲ የሰራ አስፈፃሚ አመራሮች በጉዳዩ ላይ መልስ እንዲሰጡ ከዋዜማ ለቀረበላቸው ጥያቄ ተመካክረን ለሁሉም መገናኛ ብዙሀን ምላሽ እንሰጣለን በሚል ምክንያት ማብራሪያ ሳናገኝ ቀርተናል።

እናት ፓርቲ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በርካታ ዕጩዎችን ያቀረበ፣ “በወግ አጥባቂነት” የፖለቲካ መስመር አምናለሁ የሚል ወጣት ምሁራንን ያሰባሰበ ፓርቲ ነው። [ዋዜማ]