ዋዜማ- የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በትግራይ ክልል ባሉ አብዛኛው የክልሉ መንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በፍርድ ቤቶች፣ በባንኮች እና ሆቴሎች መሰቀል ካቆመ አራት አመት ሊሆነው ነው። 

ለኹለት ዓመት የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረበት ጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ የፌደራሉ ሰንደቅ ዓላማ በክልሉ ባሉ አብዛኛው የመንግሥት ተቋማት እና በባለስልጣናት ቢሮ እንደወትሮው አይታይም።  

ዋዜማ በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ባደረገችው ማጣራት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሚውለበለበው እንደ አየር ማረፊያ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ቴሌኮም በመሳሰሉ የፌደራል ተቋማት እንዲሁም በጥቂት የክልል ቢሮዎች እና ትምህርት ቤቶች ብቻ ነው። 

ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ ማስተማር በጀመሩ በርካታ ትምህርት ቤቶች የሚውለበለበው የክልሉ ሰንደቅ ዓላማ ብቻ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር የማይዘመርባቸው ትምህርት ቤቶችም በርከት ያሉ ናቸው። 

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኮሚንኬሽን ቢሮ የኮሚኒኬሽን ባለሙያው ሰለሞን ገብረእግዚአብሔር፣ ይህ የሆነው አንድም ጦርነቱ በማህበረሰቡ ላይ በፈጠረው የስነልቦና ጫና መሆኑን ጠቅሰው፣ የሰንደቅ ዓላማ እጥረትም የችግሩ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ነግረውናል። 

በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች እና መስሪያ ቤቶች የፌደራሉ ሰንደቅ ዓላማ አሁንም ጥቅም ላይ እንደሚውል ጠቅሰው፣ ሆኖም እንደድሮው ሁሉም ጋር አለ ለማለት እንደማያስደፍር ገልጸዋል። 

ከጦርነቱ በፊት ክልሎች የሚፈልጉትን ባንዲራ መጠን ለፌደራል መንግስቱ በማሳወቅ እና ገንዘብም በመክፈል ከቻይና እንዲመጣላቸው ይደረግ ነበር። አንዳንድ የግል ተቋማትም ባንዲራዎችን ከቻይና አስመጥተው ይሸጡ ነበር። ይህ አሰራር በሌሎች ክልሎች ቀጥሎ ሊሆን ቢችልም በትግራይ ክልል ግን ከጦርነቱ በኋላ አልቀጠለም። 

ባለሙያው የትም ይሁን የፌደራሉ እና የክልሉ ሰንደቅ ዓላማ አብረው መሰቀል አለባቸው (የየራሳቸውን መጠን እና ከፍታ ጠብቀው) የሚል አስገዳጅ ህግ መኖሩን አንስተው፣ እዚህ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ሥራዎች የተቀዛቀዙ መሆናቸውን ገልጸዋል። የፌደራል መንግሥቱም ህጉ ተግባራዊ እንዲደረግ እስካሁን የተለየ እንቅስቃሴ አለማድረጉን ጠቅሰዋል። 

ከጥቅምት 2013 እስከ ኅዳር 2015 ዓ.ም የተካሄደው የሰሜኑ ጦርነት የፈጠረው ጠባሳ በማህበረሰቡ ዘንድ “ኢትዮጵያዊ አይደለንም” የሚል ስሜት እስከመፍጠር ደርሷል ያሉት ባለሙያው፣ ይህ ስሜት ቶሎ አይጠፋም ሆኖም ግን ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በማህበረሰቡ ዘንድ የነበረው ስሜት ተሻሽሏል ብለዋል።

አክለውም፣ የፌደራል መንግሥቱም ክልሎችን በእኩል ዓይን ማየት ሲችል እንዲሁም የትግራይ ክልል ህዝብ በፌዴሬሽን እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውክልና አግኝቶ ጥያቄዎች እየተመለሱ ሲሄዱ የሰንደቅ ዓላማው ጉዳይም አብሮ ይስተካከላል ። 

ዘንድሮም በዚህ ሳምንት የተከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎች ክልሎች ከሰሜኑ ጦርነት በፊት በነበረው ስነ ስርዓት ተከብሯል።

ከሰሜኑ ጦርነት በፊት በየዓመቱ ለሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ቻይና ታትሞ የሚመጣ የፌደራል እና የክልል ሰንደቅ ዓላማ ወደ ክልሎች ይሰራጭ ነበር። የትግራይ ክልል ምክር ቤትም ኅላፊነቱን ወስዶ ለበዓሉ የሚያስፈልገውን የፌደራል እና የክልል ሰንደቅ ዓላማ ተረክቦ ወደ ዞን እና ወረዳዎች ሲልክ ቆይቷል። ባለሙያው እንደሚሉት ከጦርነቱ በኋላ ይህ አካሄድ በትግራይ ክልል ተቋርጧል። 

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አዋጅ፣ “የሪፐብሊኩን ሰንደቅ ዓላማ መውለብለብ የሚያግድ ከአቅም ላይ የሆነ ምክንያት ካላጋጠመ በስተቀር ከላይ እስከታች ባሉ የክልል የስልጣን አካላት በጽህፈት ቤቶች፣ በፍርድ ቤቶች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በፖሊስ እና በጤና ጥበቃ ተቋማት እንዲሁም በሌሎች የፌደራል ተቋማት በየቀኑ ሰንደቅ ዓላማ ይሰቀላል” ይላል። [ዋዜማ]