“ጊዜያዊ አስተዳሩን የሾመው ጠቅላይ ሚንስትሩ ነው፣ ሕወሐት ማውረድ አይችልም “

ዋዜማ- የደብረፂዩን አንጃ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሊቀመንበርና ሌሎች ሹማምንትን ከሀላፊነታቸው የማንሳት ስልጣን እንደሌለውና በጉዳዩም ላይ እስከ ሰኞ ማምሻውን ድረስ ከፌደራሉ መንግስት ጋር የተደረገ ውይይት አለመኖሩን የፌደራሉ መንግስት ባለስልጣን ለዋዜማ ነግረዋል።

ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመሩት የሕወሓት ክንፍ፣ ጌታቸው ረዳን ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሥልጣን ማንሳቱን ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ቡድኑ፣ ጌታቸውን ማን ሊተካቸው እንደሚገባ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡

የደብረጺዮን የሕወሓት ቡድን፣ 13 የካቢኔ አባላትን፣ የቢሮ ሃላፊዎችንና የዞኖች አስተዳዳሪዎችን ከሃላፊነት ማውረዱን ጠቅሶ፣ በምትካቸው ሌሎች አመራሮችን መመደቡንና ከሃላፊነታቸው የተነሱት ሰዎች ከትናንት ጀምሮ የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር መምራት እንደማይችሉ አመልክቷል።

ቡድኑ፣  ከሃላፊነታቸው አንስቻቸዋለኹ ባላቸው አመራሮች ምትክ የመደባቸውን ሃላፊዎች ዝርዝር ይፋ አድርጓል። በካቢኔ ሹመት ላይ ተመድበዋል ከተባሉት መካከል፣ ምርጫ ቦርድ እውቅና የነፈገው የፓርቲው ጉባኤ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ የመረጣቸው አማኑኤል አሠፋ እንዲኹም አብርሃም ተከስተ ይገኙበታል።

በሌላ በኩል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመሩት የሕወሓት. ክንፍ “መፈንቅለ መንግስት አውጆብኛል” በማለት ባወጣው መግለጫ ከሷል። ቡድኑ ሥርዓት አልበኝነትን ለማስፋፋትና ትርምስ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ያለው አስተዳደሩ፣ በዚህ ቡድን አመራር ላይ “ሕጋዊ ርምጃ” መውሰድ እንደሚጀምርና በሂደቱ ለሚደርስ ማናቸውም ጉዳት ይኼው ቡድን እና አመራሮቹ ብቻ ተጠያቂ እንደኾኑ ሕዝቡ እንዲረዳ አሳስቧል።

“ገለልተኛ ነኝ” የሚለው የትግራይ ጸጥታ ኃይሎች አመራር በኹለቱ አካላት ተጻራሪ መግለጫዎች የተነሳ በክልሉ ውስጥ የሚፈጠር ማንኛውንም ዓይነት ሥርዓት አልበኝነትና የጸጥታ ችግር አልታገስም በማለት አስጠንቅቋል።

ደብረፂዮን የሚመሩት አንጃ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳንና ሌሎች አመራሮችን አንስቶ በቦታቸው የሚተካ መሪ ለመፈለግ ከፌደራሉ መንግስት ጋር እየተነጋገረ ስለመሆኑ ቢያሳውቅም ዋዜማ ከፌደራሉ መንግስት ባገኘችው መረጃ በደብረፂዮንና በፌደራሉ መንግስት መካከል በጉዳዩ ላይ ንግግር አልተደረገም።

ዋዜማ ያነጋገረቻቸውና ስማቸውን መግለፅ ያልወደዱ የፌደራሉ መንግስት ባለስልጣን “ሕወሐት እገሌ ይነሣ እገሌ ይተካ ማለት አይችልም። ከሕወሐት መካከል ፌዴራል መንግሥት ይመርጣል እንጂ ሕወሐት የመምረጥ ሥልጣን የለውም” ሲሉ ያብራራሉ።

“ጊዜያዊ አስተዳሩን የሾመው ጠቅላይ ሚንስትሩ ነው። ሕወሐት ማውረድ አይችልም”

“በዚህ ጉዳይ የተደረገም የሚደረግም ንግግር የለም” ይላሉ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑት ባለስልጣን።

በትግራይ የፖለቲካ ውዝግቡ ወደ ለየለት የፀጥታ ስጋት በተሸጋገረበት በዚህ ወቅት ደብረፂዮን ገብረሚካዔል ወደ አዲስ አበባ አቅንተዋል። የደብረፂዮን የአዲስ አበባ ቆይታ በዋናነት ጠቅላይ ሚንስትሩን አግኝቶ ለማነጋገር ያለመ መሆኑን ስምተናል።

ደብረፂዮን የሚመሩት አንጃ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ካለው በሚል በስልክ ለማነጋገር ያደርግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።[ዋዜማ]