ዋዜማ- በደቡብ ጎንደር ዞን በሚገኙ ከአምስት ወረዳዎች ከ2016 ዓ.ም ማብቂያ ጀምሮ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ለቀው መውጣታቸውን ዋዜማ ተረድታለች።
የፌደራል እና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች እስቴ መካነ ኢየሱስ፣ አንዳቤት፣ ሙጃ፣ ስማዳ እና ታች ጋይንት ከሚባሉ ወረዳዎች ከነሐሴ ዕኩሌታ ጀምሮ እስከ ጳጉሜ መጨረሻ ባሉት ጊዜያት ሙሉ በሙሉ ለቀው መውጣታቸውን ዋዜማ ተገንዝባለች። የመንግስት ኀይሎች ለምን ከአካባቢው እንደወጡ በይፋ አልተናገሩም።
በወረዳዎቹ የነበሩ የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮች እንዲሁም የፖሊስ እና የሚሊሻ አባላት ሙሉ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ከፌደራል የጸጥታ አካላት ጋር ወደ ዞኑ መቀመጫ ደብረታቦር ገብተዋል።
ይህን ተከትሎም በወረዳዎች ኹሉም ዓይነት የመንግሥት አገልግሎቶች የተቋረጡ ሲሆን፣ በፖሊስ እና በሚሊሻ የሚሰጡ አገልግሎቶችም በተመሳሳይ ቆመዋል።
በአንጻሩ በእነዚህ ወረዳዎች ባንኮች እና የጤና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ ነው ተብሏል። ትምህርት ቤቶች እስካሁን ምዝገባ አላከናወኑም።
የአማራ ክልል መንግስት የኮምኒኬሽን ቢሮ ስለጉዳዩ ላቀረብንለት ጥያቄ ጉዳዩን መመለስ የሚችለው የኮማንድ ፖስቱ ነው ከማለት ውጪ ምላሽ ለመስጠት አልፈቀደም።
የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከወረዳዎቹ ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ በቦታው የተተኩት የፋኖ ታጣቂዎች የራሳቸውን የአስተዳደር መዋቅር ለመዘርጋት ጥረት እያደረጉ ነው።
በአንጻሩ የዞኑ ዋና መቀመጫ ደብረታቦር እንዲሁም ንፋስ መውጫ፣ ፎገራ እና ደራ ወረዳዎች ዋና ከተሞቻቸው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ስር ይገኛሉ። ሆኖም በዞኑ ዋና ከተማ ደብረታቦር ዙሪያ ታጣቂዎች በብዛት እንደሚገኙ ሰምተናል።
በሰሜን ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደር እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖችም ሰሞኑን በኹለቱ ኃይሎም መካከል ከፍተኛ ውጊያ ሲካሄድ ቆቷል።
ሰሞኑን በመንግስት ወታደሮች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የዞን አስተዳደር መቀመጫ በሆኑት በጎንደር እና በደባርቅ ከተሞች በከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ ሲካሄድ ሰንብቷል። ይህን ተከትሎም በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ለሞት እና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ተገንዝበናል።
በክልሉ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረው ግጭት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ለሞትና ለአካል ጉድት መዳረጋቸውን ብሎም ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱን የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተቋማት የሚያወጧቸው ሪፖርቶች ያሳያሉ። [ዋዜማ]