ዋዜማ- ከአዲስ አበባ 700 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኘው የምስራቅ ቦረና ዞን በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረ አዲስ የዞን አደረጃጀት ነው።
በተለይም ቀደም ሲል በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ጉጂ ዞን ስር ካሉ ወረዳዎች አንዷ በነበረችው ጎሮ ዶላ ወረዳ በየጊዜው በሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች እረፍት አልነበራትም፡፡ አስር ወራት ያስቆጠረው ተቃውሞና አለመረጋጋት ወትሮም እንደነገሩ የነበረውን የትምህርትና የጤና አገልግሎት አስተጓጉሎታል።
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ)መጋቢት 20 ቀን 2015 ዓ.ም ሃያ አንደኛ የክልሉን ዞን በማድረግ አዲስ ያዋቀረውን የምስራቅ ቦረና ዞን አደረጃጀት ይፋ ካደረገበት ቀን ጀምሮ በዞኑ ስር ካሉ 18 ወረዳዎች አንዷ የሆነችው የጎሮ ዶላ ወረዳ “በምስራቅ ቦረና ዞን ስር መካከል አንፈልግም” ያሉ የወረዳዋ ነዋሪዎች ያለማቋረጥ የተቃውሞ ስልፍ እያደረጉ ነው፡፡
ነጌሳ ጎዳና የዕድሜ ባለጸጋ ሲሆኑ በወረዳው ሐረ ቀላ ከተማ ለረዥም ዘመናት የኖሩ አባት ናቸው የጎሮ ዶላ ወረዳ እንደ ወረዳ ከተዋቀረችበት 1994 ዓ.ም ጀምሮ በምስራቅ ጉጂ ዞን ስር ስትተዳደር እንደነበር እና ነጌሌ ቦረና ደግሞ የዞኑ ዋና ከተማ እንደሆነች ይናገራሉ፡፡
የነዋሪዎች ተቃውሞ ዋነኛው ምክንያት የክልሉ መንግሥት ወረዳዋን በአዲሱ የምስራቅ ቦረና ዞን ስር ለማካለል ሲወስን ሕዝቡን አላወያየም የሚል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
እንዲሁም አደረጃጀቱ ወረዳዋ ከጉጂ ዞን እንዲሁም ከዋና ከተማዋ ከነጌሌ ቦረና ስታገኝ የነበረውን ተቋማዊ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ የሚያቋርጥ በመሆኑ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ተቃውሞውን ሲያሰማ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ሌላ የወረዳው ነዋሪ ጃርሶ ጉዬ በበኩላቸው በየጊዜው በሚደረጉ ተቃውሞዎችም በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ የሚደርሰው ውድመት ከፍተኛ ነው። ለአብነትም ባለፈው ነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ላይ ድምጻቸውን በሰላማዊ መንገድ ሊያሰሙ በወረዳው ሀረ ቀላ ከተማ የወጡ ከ 2 ሺሕ በላይ ሰዎችን ለመበተን የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በሰዎች ላይ ሞት እንዲሁም ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰ መሆኑን እንዲሁም ከ 2መቶ በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ተናግረዋል፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በወረዳው አስተዳደር ውስጥ የሚሰሩ አመራር እንደነገሩን ደግሞ በዚሁ ተደጋጋሚ ተቃውሞ ምክንያት የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ሥራ ካቆሙ ሦስት ወራት አልፏቸዋል ያሉ ሲሆን የንግድ እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴም እንዲሁ ከቀን ወደ ቀን እየተቀዛቀዘ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡
አሁን እንደ ትምሕርት ቤት፣ጤና ጣብያ እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራ እየሰሩ አየደለም በማለት ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በወረዳው ስር ካሉ 80 አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት እስካሁን የተማሪ ምዝገባ እንኳን አለማድረጋቸው፣ በዚህም ምክንያት 60 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸውን ሰምተናል፡፡
የተማሪዎቹ ምዝገባ የዘገየውም በወረዳዋ ያለማቋረጥ በሚደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ምክንያት ሲሆን ሰልፉም ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጋር ወደ ግጭት ስለሚያመራ የደህንነት ስጋት ማስከተሉን ነዋሪዎች ይናገራሉ።፡፡
አብዛኛዎቹ መምህራን ከደመወዝ ክፍያ መዘግየት ጋር ተያይዞ ስራ ካቆሙ ወራት መቆጠራቸውን እና ችግሩ እንዲፈታና ተማሪዎች ወደትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ከክልል እስከ ዞን በየደረጃው ላሉ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት አቤቱታችንን ብናቀርብም ችግሩ እልባት ሊያገኝ አልቻለም ሲሉ የትምህርት ዘርፍ ሀላፊዎች ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ከጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለዋዜማ ያስረዱት የሀረቀላ ጤና ጣቢያ የጤና ባለሙያ ተመስገን ደደቻ በወረዳው ካሉ 5 የጤና ጣቢያውች መካከል አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው በከተማዋ የሚገኘው ሀረቀላ ጤና ጣቢያ ብቻ ነው ያሉ ሲሆን እሱም ቢሆን ከፍተኛ የሆነ የመድኃኒት እና የህክምና ቁሳቁስ እጥረት እንዳለበት አውስተዋል፡፡
ዋዜማ ስለጉዳዩ የጎሮ ዶላ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑትን ጌቱ ጩሉቄን ያነጋገረች ሲሆን ካለው የጸጥታ ስጋት አንጻር አካባቢው ላለፉት አምስት ዓመታት በኮማንድፖስት ወይም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር እንደምትተዳደር ገልፀዋል፡፡
ምንም እንኳን ወረዳዋ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ብትተዳደርም በየጊዜው “ማን እንደጠራው የማይታወቅ” ሰልፍ ይደረጋል ለዚህም ሲባል የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ሰልፉን ለመበተን በሚወስዱት እርምጃ በሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡
በወረዳዋ በተለይም “የተለየ ተልዕኮ ያላቸው” ወጣቶች በተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፉን ሲያያደርጉ መንገድ ከመዝጋት ጀምሮ ተሽከርካሪዎችን ማቃጠል፣ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ላይ ጥቃት ማድረግ እና ሌሎችንም ተግባራትን ሲፈጽሙ ተስተውሏል ብለዋል፡፡
አካባቢው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ለዓመታት ሲንቀሳቀስበት የነበረና አሁንም የሚንቀሳቀስበት እንደሆነ የገለጹት ጌቱ ለዚህም ሲባል በኮማንድ ፖስት ስር እንድትተዳደር መደረጓን አብራርተዋል፡፡
አስተዳዳሪው አክለው እንደተናገሩት በወረዳው ችግሮች ከዕለት ወደዕለት እየተባባሱ መጥተዋል በማለት ለዚህም መፍትሄ የሚሆነው ተቀራርቦ መነጋገር ብቻ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
የምስራቅ ቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጃርሶ ቡሌ በበኩላቸው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ከስምንት ወራት በፊት ይፋ ባደረገው አወቃቀር መሰረት በጉጂ ዞን ሥር የነበሩ ጎሮ ዶላን ጨምሮ ዱብሉቅ፣ ኦቦርሶ፣ አሬር፣ ዋጪሌ እንዲሁም ቦርኖርን የመሳሰሉ ወረዳዎች በአዲሱ አደረጃጀት ወደ ምስራቅ ቦረና ዞን መካለላቸውን አስረድተዋል፡፡
ይህም “የጉጂ ሕዝብ ከሃያ ዓመታት በላይ ሲጠይቀው የነበረ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነው።” በማለት ወረዳዎቹ ወደ ምስራቅ ቦረና ዞን መካለላቸው ምንም አይነት ጉዳት እንደሌለው በክልሉ መንግሥት ስለታመነበት ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
አሁንም አልፎ አልፎ የሚታዩ አመጾች ከዚህ በላይ ዋጋ እንዳያስከፍሉ ከአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም በየደረጃው ካሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ጋር ተከታታይ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም የአከባቢው ማኅበረሰብ ለዘመናት ሲጠቀምቀት የነበረውን “ጃርሱማ” የተሰኘ በአገር ሽማግሌዎች የሚመራ ባሕላዊ የግጭት አፈታትን ዘዴን በመጠቀም የመንግሥት አካላት ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀራርበው ለመነጋገር እና ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ [ዋዜማ]
ዋዜማ ይህን ዘገባ ያቀረበችው በኢንተርኒውስ የገንዘብ ድጋፍ ታግዛ ነው