ዋዜማ- በጌዴኦ ዞን 320 ትምሕርት ቤትዎች የሚገኙ ሲሆን የትምህርት ሚንስቴርን መመዘኛ አሟልተው ‘’ትምሕርት ቤት ‘’ለመባል የሚበቁት 13 ብቻ መሆናቸውን ዋዜማ ከዙኑ ትምሕርት መምሪያ ኃላፊ ሰምታለች፡፡
ከ80 በላይ የትምህርት ቤት የደረጃ መለኪያዎች ቢኖሩም በጌድኦ ዞን የሚገኙት ትምህርት ቤቶች ግን መሰረታዊ የሚባሉትን የደረጃ መለኪያዎች እንኳን የሚያሟሉ አይደሉም።
ከእነዚህ መካከል ከፍተኛውን ስፍራ የሚይዙት የግንባታ ሁኔታ፣ ለተማሪዎች እና ለመማር ማስተማር ምቹ መሆን፣የሚያስፈልግ የሰው ሐይል፣ቤተ መፅሐፍት፣ቤተ ሙከራ፣ውሃ ፣መብራት ፣መፀዳጃ ቤት፣የትምህት አመራር እና አስተዳደር ናቸው፡፡
በመመዘኛዎቹ መሰረት በጌዲኦ ዞን የሚገኙ 98 በመቶ ትምሕርት ቤቶች የጥራት ደረጃን የሚያሟሉ አይደሉም፡፡
በዞኑ በርከት ያሉ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ፡፡ በ2015 ዓ.ም ትምህርት በመከታተል ላይ ከሚገኙ 266 ሺህ 700 ተማሪዎች ውስጥ ከ18ሺህ በላይ የሚሆኑት ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፡፡
ዋዜማ ከዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች ክፍሌ እንደሰማችው ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከሚያቋርጡባቸው ምክንያቶች መካከል የማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ቀውሶች፣ በጌዲዮ ዙሪያ ያለው የጸጥታ ስጋት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡
በጸጥታ ስጋት የተነሳ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ ይህን ተከትሎ 2014 ዓ.ም አምስት ትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው ተዘግተዋል፡፡ ዘንድሮም በጌዲኦ ዙሪያ በሚገኙ አራት ወረዳዎች ‘’የኦነግ ሸኔ’’ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ነዋሪዎች ተረጋግተው መኖር ስላልቻሉ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት በዞኑ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች ምጣኔ በመቶኛ ሲሰላ 14 በመቶ የነበር ሲሆን ዘንድሮ ወደ 6 በመቶ ዝቅ ብሏል ። ምንም እንኳን ቁጥሩ የመቀነስ አዝማሚያ ቢኖረውም ችግሩ ቀላል የሚባል አይደለም ሲሉ የትምሕርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች ክፍሌ ገልጸዋል፡፡
የቡና አብቃይ በሆነችው ጌዲኦ ተማሪዎች በትምሕርታቸው እንዲቀጥሉ ከማድረግ ይልቅ ወደ ቡና ንግድ እና ስራ እንዲገቡ በማሕበረሰቡ ይበረታታሉ፡፡ [ዋዜማ]