ዋዜማ- በቅርቡ መንግስት የስንዴ ምርትን ለውጪ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በሀገር ውስጥ የስንዴ ዋጋ በከፍተኛ መጠን የናረ ሲሆን ህገ ወጥ የኮንትሮባንድ የስንዴ ግብይት መጀመሩን ዋዜማ ከአርሶአደሮችና ከሸማቾች ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል።
የሀገሪቱን ገፅታ በበጎ የገነባና በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን መነጋገሪያ የነበረው ስንዴን ለውጪ ገበያ የማቅረብ መርሀግብር ይፋ ከተደረገ በኋላ በኮንትሮባንድ ህገ ወጥ ገበያ አንድ ኩንታል ስንዴ ከ5,500 ብር ጀምሮ እስከ 7,000 ብር እየተሸጠ ነው።
የስንዴ ዋጋ መወደድ በርከት ያሉ የዳቦ መጋገሪያዎች ስራቸው እንዲስተጓጎል ማድረጉንና የተለያዩ የምግብ ሸቀጦች ላይ አሉታዊ ተፅኖ ማሳደሩንም ባደረግነው የገበያ ምልከታ ታዝበናል።
መንግስት የኦሮምያ ክልልን ጨምሮ ስንዴ አብቃይ በሆኑ ክልሎች ያሉ አርሶ አደሮች ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ስንዴን በአነስተኛ ዋጋ ለመንግስት እንዲያቀርቡ የሚያስገድድ አሰራር መተግበሩን ዋዜማ ከዚህ ቀደም መዘገቧ የሚታወስ ነው።
በመንግስት መመሪያ መሰረት ስንዴ አምራች አርሶ አደሮች አንድ ኩንታል ስንዴን በ3,200 ብር እንዲያቀርቡ ይህም በኢትዮጵያ ምርት ገበያን ጨምሮ በተለያዩ የንግድ ሰንሰለቶች ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ ተወስኖ ነበር።
የዚህ እቅድ አካል የሆነ 2.5 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ለኬንያ እና ሱዳን እንዲሁም ለዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች እንዲሸጥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተገኙበት በስንዴ አብቃይነቱ በሚታወቀው ኦሮሚያ ክልል ባሌ ይፋ መደረጉ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት በጥቅሉ በዚህ አመት ለውጭ ገበያ ከሚቀርብ ስንዴ 150 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ማቀዱን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። ሆኖም የዚህ ስንዴን ለውጭ የማቅረቡ ነገር ገና ከመጀመሩ የሀገር ውስጡን ገበያ ማናጋት ጀምሯል።
ምርቱን በኩንታል መንግስት ባስቀመጠው ዋጋ መሸጥ አያዋጣንም ያሉት አርሶ አደሮች ምርቱን መሸሸግ መርጠዋል። መንግስት ባስቀመጠው አሰራር ስንዴን የማያስረክብ ካለና መንገድ ላይ የሚያንቀሳቅስ ተሽከርካሪም ከተገኘ ይወረሳል።
ይህም የህገ ወጥ የስንዴ ኮንትሮባንድ ንግድ እንዲስፋፋ ማድረጉን ተገንዝበናል።
ቅኝት ባደረግንበት በአዳማ ከተማ አንድ ኩንታል ስንዴ እስከ 5,500 ብር እየተሸጠ እንደሆነ ስማቸው እንዳይጠቀስ ከፈለጉ አንድ ነጋዴ ጋር ባደረግነው ቆይታ ነግረውናል። በዚህ ዋጋም ቢሆን ዱቄት አምራቾች ይገዙ ይሆናል እንጂ እቤቱ ወስዶ ለመጠቀም ለፈለገ ሰው ስንዴ እንደ ልብ የሚገኝ አይደለም።
በአንጻሩ ለስንዴ አምራቿ አርሲ ቅርብ ወደ ሆነችው አዳማ ስንዴ ለመድረስ ሶስት ፍተሻዎችን ማለፍ ይጠበቅበታል።ነጋዴዎች ስንዴውን መንግስት ባስቀመጠው መመሪያ እየሸጡ ባለመሆኑም ሶስቱንም ፍተሻ ለማለፍ ህገወጥ ክፍያን ይከፍላሉ። ስለዚህም አርሲ ውስጥ መንግስት ካስቀመጠው ለኩንታል ከ3, 200 ብር በላይ ለአርሶ አደሮች ከፍለው የገዙ ነጋዴዎች በየኬላው ለማሳለፍ የከፈሉትን እና ትርፋቸውን አስልተው አዳማ ውስጥ በኩንታል እስከ 5,500 ብር ይሸጡታል።
የስንዴው ዋጋ ወደ አዲስ አበባ ቀረብ ወዳሉ ከተሞች ደግሞ ከዚህ በላይ ይወደዳል።አዲስ አበባ ዙርያ ባሉ ሰበታ ፣ ሰንዳፋ የመሳሰሉት አካባቢዎች ስንዴ በኩንታል እንደየደረጃቸው እስከ 7, 000 ብር እንደሚሸጥም ሰምተናል። ይህም የሆነው ገበያው ከስንዴ አምራች አካባቢዎች እየራቀ በመጣ ቁጥር ህገ ወጥ ክፍያ የሚፈጸምባቸው ኬላዎች ቁጥርም ስለሚጨምርም ጭምር ነው። በጭነት ከሶስት ኩንታል በላይ ስንዴን ማጓጓዝ የተከለከለባቸው ከተሞችም እንዳሉም ሰምተናል። በመዲናይቱ የዳቦ ዱቄት በኪሎ 80 ብርን እየተሻገረ ነው።
የያዝነው ወር ወትሮ ምርት የሚገባበትና የጥራጥሬ ዋጋ ቅናሽ የሚያሳይበት ነበር። ይሁንና አሁን ያለው የየጥራጥሬ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ሲነፃፀር ሀያ ዘጠኝ በመቶ ደርሷል።
የስንዴ ዋጋ ላይ የታየው ጭማሬው ካለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ አንጻር የላቀ ልዩነት አለው። በ2014 አ.ም ምርት ተሰብስቦ ባለቀበት ጥር ወር አካባቢ አንዱ ኩንታል ግፋ ቢል እስከ 4,000 ብር ነበር የሚሸጠው። የስንዴ ዋጋ በአንጻሩ ከፍ ይላል በሚባልበት ሚያዝያ ወር አካባቢ የነበረው ዋጋ እንኳ በኩንታል 4500 ብር ነበር።
መንግስት ስንዴን ለወጪ ንግድ ለማቅረብ መወሰኑን ተከትሎም ከስንዴ አምራቾች ጋር የተፈጠረው አለመግባባትም ለሀገር ውስጥ ገበያው መዛነፍ ምክንያት ሆኗል።በተለይ ባለፈው አመት መንግስት ለማዳበሪያ ሲያደርግ የነበረውን ድጎማ አቁሞ ገበሬዎች በውድ ዋጋ ማዳበሪያ መግዛታቸውም ዛሬ ላይ ለውጭ ገበያ በሚቀርበው ስንዴ ዋጋ ላይ ለተፈጠረው አለመግባባትና እሱን ተከትሎ የስንዴ ምርት ከይፋዊ ገበያ ወጥቶ ወደ ህገወጥ ንግድ ለመግባቱም በምክንያትነት ይነሳል። [ዋዜማ]