ዋዜማ- ባለፉት ሳምንታት በሱማሌላንድ ላስ አኖድ ከተማ የተቀሰቀሰውን ግጭት የሸሹ ከ83ሺ በላይ ስደተኞች የኢትዮጵያን ድንበር በማቋረጥ ሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን እንደሚገኙ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት አስታውቋል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች፣ህፃናት፣ነፍሰ ጡሮች እና አቅመ ደካሞች በመሆናቸው አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲሉ የአገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋሁን ጎበዛይ ገልፀዋል።
ተፈናቃዮቹ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ይህ ነው የሚባል የዕለት ደራሽ ዕርዳታ አላገኙም።
በመሆኑም የተመጣጠነ ምግብ፣ውሃ፣የንፅህና ግብዓት አቅርቦት ብሎም ልዩ ጥበቃና ከለላ አገልግሎት በአስቸኳይ እንዲያገኙ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ጠይቋል።
የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ከተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ ጋር በመሆን ድጋፍ እየደረገ መሆኑን ገልጾ ከችግሩ ስፋት አንፃር አለማቀፉ ማህበረሰብ እና አጋር አካላት እጃቸውን እንዲዘረጉ ጥሪ አቅርቧል።
ተፈናቃዮችን የሚቀበሉት የማህበረሰብ ክፍሎች በአፍሪካ ቀንድ ተባብሶ የቀጠለው ድርቅ በተደጋጋሚ ሰለባ በመሆናቸው ሁኔታውን የበለጠ አስቸጋሪ እንዳደረገው ዳይሬክተሩ ለዋዜማ ገልፀዋል። በመሆኑም አብዛኛውን ጥገኝነት ጠያቂዎች ተቀባይ ማህበረሰቡ መኖሪያ ቤቶች እና ሰዎች በሌሉባቸው ቦታዎች ማረፋቸው ተገልጿል።
የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዳይሬተር ተስፋሁን ጎበዛይ ”ኢትዮጵያ ለተቸገሩት ከለላ የመስጠት የረጅም ታሪክ አላት ያሉ ሲሆን ይሄንንም ለማስቀጠል ሰብዓዊና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገ ነው ብለዋል። እስካሁንም ከሶማሌ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ቢሮ ጋር በመተባበር ከ1ሺ 5መቶ በላይ ለሆኑ ስደተኞች ድጋፍ ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።
የተመድ የስደተኞች ኤጄንሲ የኢትዮጵያ ተጠሪ ማማዱ ዲያን ባልዴ በበኩላቸው ” የኢትዮጵያ መንግስት ከለላና ጥበቃ ለሚሹ የሶማሌ ወንድሞቹና እህቶች በሩን ክፍት አድርጎ ያልተቆጠበ ለጋስነቱን አሳይቷል” ብለዋል። ቁጥራቸዎ መቶ ሺ የሚጠጋ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለመርዳት የምንችለውን እያደረግን ነው፤ መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ለሟሟላት ግን ከአለማቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ ትኩረትና ድጋፍ ያስፈልጋል” ብለዋል ተጠሪው።
በላስ አኖድ ከተማና አካባቢዋ ሦስተኛ ስምንቱን የያዘው ግጭት እየተካሄደ ያለው፣ በሱማሌላንድ ወታደሮችና በዱልባሃንቴ ጎሳ ሚሊሻዎች መካከል ነው። ይህንን ግጭት ሽሽት ወደ ኢትዮጵያ የገቡትን ስደተኞች በተመለከተ ለመጠለያ የሚሆን ቦታ ለመወሰን የሚመለከታቸው አካላት ተከታታይ ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ዋዜማ ሰምታለች። [ዋዜማ]