ዋዜማ- መንግስት የገንዘብ፣ የበጀት እና ሌሎች ዘርፎችን የሚነኩ ፖሊሲዎችን ክለሳ በማድረግ ለመተግበር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ዋዜማ ከመንግስት ምንጮች ስምታለች።
በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን የሚመራው ይህ የክለሳ ውይይት የተለያዩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት ያካተተ መሆኑን ተረድተናል።
በቁጥጥር ስር ሊውል ያልቻለው የዋጋ ንረት ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ፣ እንዲሁም እጥረቱን ተከትሎ በባንክ እና በጥቁር ገበያ መካከል የተፈጠረውን የተጋነነ የዋጋ ልዩነት መንግስትን ለተለያዩ እርምጃዎች አነሳስተውታል ተብሏል።በቅርቡም ይፋ የሚሆኑ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንደሚኖሩም ተነግሯል።
መንግስት የገንዘብ ፖሊሲን አሁን የሚያሻሽል ከሆነ በአንድ ዓመት ለሶስተኛ ጊዜ ይሆናል።ከአንድ ዓመት በፊት የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዋጋ ንረት 26 በመቶ የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የዋጋ መረጋጋት ያመጡልኛል ያላቸውን ሁለት የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎች ተግብሮ ነበር።
ባንኮች ካላቸው የተጣራ ቁጠባ ለመጠባበቂያነት ያስቀምጡ የነበረውን የአምስት በመቶ ምጣኔን ወደ አስር በመቶ እንዲያሳድጉ እንዲሁም ንግድ ባንኮች የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥማቸው ከብሄራዊ ባንክ ሲበደሩ የሚጠየቁት የ13 በመቶ ወለድ ክፍያ ወደ 16 በመቶ እንዲያድግ መወሰኑ ይታወሳል። በወቅቱ ፖሊሲውን በዚህ ደረጃ ማስተካከል ያስፈለገውም ለዋጋ ንረቱ አንዱ ምክንያት በባንኮች በኩል ወደ ገበያ የሚገባው ብር መሆኑ ስለታመነ መጠባበቂያ እና የባንኮች መበደሪያ ወለድን ከፍ በማድረግ ወደ ገበያ የሚገባውን ገንዘብ ለመቀነስ ታስቦ ነው።
ከዚያ በሁዋላም ቢሆን ግን የዋጋ ንረቱ የመቀነስ አዝማሚያን አላሳየም።ባለፈው አመትም በአመዛኙ የሀገሪቱ የዋጋ ንረት ከ30 በመቶ በላይ ሆኖ ነው የተጠናቀቀው። ሁኔታዎች በዚህ ላይ እንዳሉም ነው ብሄራዊ ባንክ መልሶ የገንዘብ ፖሊሲውን ከጥቂት ወራት በሁዋላ መልሶ ያሻሻለው።
በሁለተኛ ማሻሻያውም ባንኮች ከተጣራ ቁጠባቸው ለመጠባበቂያነት የሚያስምጡትን 10 በመቶ ገንዘብ ምጣኔ ወደ ሰባት በመቶ ዝቅ በማድረግ ከተቀማጫቸው ተጨማሪ ሶስት በመቶውን እንዲያበድሩ ፈቅዷል። በጦርነት ምክንያት በርካታ አምራች ፋብሪካዎች ስራ ስላቆሙ ተጨማሪ ብድር ቀርቦላቸው ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ ታስቦ ነበር ማሻሻያው የተደረገው። ሆኖም ውሳኔው አጠቃላይ የዋጋ ንረት 34 በመቶን ባለፈበት ጊዜ የተላለፈ በመሆኑ ተጨማሪ ገንዘብ በማስገባት የዋጋ ንረቱን ያባብሳል የሚል ትችት በኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሲቀርብበት ቆይቷል።
ካለፈው አመት መስከረም ወር ጀምሮ የተወሰዱት የገንዘብ ፖሊሲ እርምጃ የዋጋ ንረቱን በማስተካከል ረገድ ውጤታማ አልሆኑም። በቅርቡም አዳዲስ ገንዘብ ነክ ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ የሚያስችል ምክክር ተጀምሯል።የውጭ ምንዛሬን የተመለከቱ አዳዲስ መመሪያዎች ይፋ እንደሚደረጉ ምንጮቻችን በእርግጠኝነት ነግረውናል።
ባለፈው አመት በጥቁር ገበያው የአንድ አሜሪካ ዶላር ዋጋ 65 ብር ደርሶ ከባንክ ምንዛሬ ጋር የ20 ብር ልዩነትን ማሳየቱን ተከትሎ መንግስት የኢኮኖሚ አሻጥር ውጤት ነው በሚል የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱ ይታወሳል። በተለይ በወቅቱ የሰሜኑ ጦርነት እንደገና ያገረሸ መሆኑን ተከትሎ ግለሰቦች ቤት እየሸጡ ገንዘባቸውን በውጭ ምንዛሬ እየቀየሩ ስለሆነ የጥቁር ገበያው ደርቶ ፣ ዋጋውም ከይፋዊ ገበያ ልዩነቱ ሰፍቶ የዋጋ ንረት የተከሰው በዚህ ምክንያት ነው ተብሎ ታምኖ ነበር። መንግስትም የቤት ሽያጭን እንዲሁም የባንክ ብድርን ወዲያው ነበር ያገደው።
እርምጀውን ተከትሎም የጥቁር ገበያው ዋጋ ወርዶ ከባንክ ጋር ያለው ልዩነት ጠቦ ቆይቷል። በሂደት የተቀመጡ እግዶች ሲነሱ የሰሜኑም ጦርነት ለሶስተኛ ጊዜ ሲያገረሽ የውጭ ምንዛሬ መዛነፎች እንደገና አገርሽተዋል።
በባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት የእርዳታና ብድር በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ፣አገር አቀፍ ሁኔታዎች የፈጠሩት የአሜሪካ ዶላር ዋጋ መወደድ ፣ ጦርነቱ የጠየቀው የውጭ ምንዛሬ እንዲሁም መንግስት ከባንኮች የውጭ ምንዛሬ ግኝት 70 በመቶውን ወስዶም ወደ ገበያው በቂ ምንዛሬ መልቀቅ አለመቻሉ እጅግ የከፋ የምንዛሬ እጥረትና የይፋዊና ጥቁር ገበያ የምንዛሬ ዋጋ ልዩነት ተከስቷል።
በሁለቱ ገበያዎች ያለው የዋጋ ልዩነት ወደ ጥቁር ገበያ አዘንብሎ የ50 ብር ልዩነት አምጥቷል። በዚህም ሳቢያ የመንግስት ምንዛሬን የተመለከተ አዳዲስ መመሪያዎች ተግባራዊ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።መመሪያዎቹ የባንኮችና ብሄራዊ ባንክ የምንዛሬ ክፍፍልን እንዲሁም የአሜሪካ ዶላር መጠንከሩን ተከትሎ መንግስት ከዕለት ዕለት የብር ምንዛሬ ተመንን ከማዳከም ባለፈ አንድ ጊዜ የሚደረግ የብር ምንዛሬ የማዳከም እርምጃን ሊወስድ የሚገደድበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ለጉዳይ ቅርብ የሆኑ ባለሙያዎች ግምት ያስቀምጣሉ። ሆኖም ይህም ተጨማሪ የዋጋ ንረት ፈጣሪ ይሆናል የሚል ስጋቶች አሉ።
መንግስት እያደረገ ያለውን ምክክር ሲያጠቃልል ከፖሊሲ እርምጃዎችና ከገንዘብ ባለፈ የበጀት እና ሌሎች ማእቀፎችን አካቶ ተግባራዊ እንደሚሆን ይጠበቃል ። [ዋዜማ]
የዋዜማ ዋና አዘጋጆችን በኢሜይል አድራሻችን wazemaradio@gmail.com ሊያገኙን ይችላሉ