ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ ከተማ ከሰንጋ ተራ እስከ ተክለሀይማኖት ባለው አካባቢ 39 የመንግስት ተቋማትን በአንድ ላይ ያሰባሰበ ግዙፍ የከተማ ማዕከል ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር ዋዜማ ስምታለች።
የሜጋ ኮንስትራክሽን የፕሮጀክት ኮንትራት አስተዳዳር ዳይሬክተር ዳዊት ጥበቡ (ኢንጂነር) ለዋዜማ ራዲዮ እንደተናገሩት ክፍለ ከተሞችን ሳይጨምር ሰላሳ ዘጠኝ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ከሰንጋተራ አንስቶ እስከ ተክለሀይማኖት በሚዘልቀው 14 ሔክታር መሬት ላይ በሚሰሩ የተለያዩ ዘመናዊ ሕንፃዎች ውስጥ ይገባሉ።
ተቋማት እንደሚሰጡት አገልግሎት አይነት በዘርፍ በዘርፍ ተደራጅተው በመንደሮች የሚደራጁ ይሆናሉ።
የሚሰሩት ህንፃዎች እጅግ ዘመናዊና ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር የተዋደዱ እንደሚሆኑም ኢንጂነር ዳዊት ነግረውናል።
ይህ አይነቱ አደረጃጀት አገልግሎት ፈላጊው ህዝብ በአንድ አካባቢ ሁሉንም አይነት አገልግሎት እንዲያገኝ የሚረዳው እንደሚሆን ኢንጂነር ዳዊት እምነታቸውን ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የጨረታ ሂደቱ የተጀመረ ሲሆን በቢሊየን ብሮች የሚያወጣው ይህ ፕሮጀክት ቁርጥ ዋጋውን የጨረታ ሂደቱ እስኪያበቃ መግለፅ እንደማይችሉ ዳይሬክተሩ ነግረውናል።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በነባሩ የአዲስ አበባ ይዞታና በነዋሪዎች ላይ ስለሚያስከትለው ተፅዕኖ ሀላፊው አላብራሩም።
ከኢንጂነር ዳዊት ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ ከታች ያድምጡት