ዋዜማ ራዲዮ- ቀደም ሲል የደቡብ ክልል በሚል ታቅፈው በነበሩትና አሁን የየራሳቸውን አዳዲስ ክልል በመሰረቱት መካከል የቀድሞ የጋራ ዋና ከተማቸው ሐዋሳ ላይ በጋራ የፈሩትን ሀብት ለመከፋፈል ፈተና ገጥሟቸዋል። ፈተናው ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ህጋው ውስብስቦሽ ያለበት ነው። ዋዜማ የዚህን ውዝግብ አንኳር ነጥቦች ለናንተ አቅርባለች።
ሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከነባሩ ደቡብ ክልል ጋር የሃብት ክፍፍል ውስጥ ይገኛሉ።
በሐዋሳ ከተማ (በሲዳማ ክልል ውስጥ) የሚገኙ መንግስታዊ የሆኑ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን ቆጥሮ፣ መዝግቦ እና ዋጋ አውጥቶ የሚያከፋፍል አካል በጋራ ይሁንታ ያዘጋጁት ክልሎቹ ሲዳማ ከከተማዋ መንግስታዊ ሃብቶች መካከል 23 ከመቶ እንዲወስድም ወስነዋል።
የሲዳማ ክልላዊ መንግስት እንደሚለው ከሃብት ክፍፍሉ ሲዳማ እስካሁን መውሰድ የቻለው መንግስታዊ መኪኖችን እና ከሶስት የማይበልጡ ህንጻዎችን ብቻ ነው ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የሚገኝበት ህንጻ፣ የክልሉ እና የሃዋሳ ከተማ ብልጽግና ቢሮዎች ከሃብት ክፍፍሉ የተገኙ መሆናቸውን ዋዜማ ተረድታለች።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ መንግስታዊ ሃላፊነት ውስጥ የሚገኙት የዋዜማ ምንጭ በበኩላቸው በሃዋሳ ከተማ የሚገኙት ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ሃብቶች በርካታ በመሆናቸው ክፍፍሉን ውስብስብ እና የተራዘመ አድርጎታል ይላሉ።
ሌሎች ከደቡብ ክልል የመገንጠል ጥያቄ ያቀረቡ ክልሎች በመኖራቸው እና ፖለቲካዊ ውሳኔ በቅርቡ ከተሰጠ ክፍፍሉ ቀጣይ መሆኑን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል።
የሀብት ክፍፍል መደረግ ያለበት በሀምሳ ስድስቱም የክልሉ ብሄሮች ባለፉት አመታት መሰብሰብ በቻሉት ገቢ ልክ ተሰልቶ መሆን አለበት የሚል ሀሳብ ያላቸው ወገኖች አሉ።
አሁን ሶስቱ ክልሎች ይገባናል ያሏቸው የልማት ድርጅቶች እና በርካታ ህንጻዎች ላይ የተጀመረው ክፍፍል የተራዘመ ጊዜ እንደሚወስድ ያም ሆኖ ሁሉን ሊያግባባ የሚችል የክፍፍል ቀመር ማዘጋጀት አስቸጋሪ መሆኑን በዚሁ የሀብት ማካፈል ስራ ላይ የተመደቡ የክልል ተወካዮች ይናገራሉ።
የሃዋሳ ስታዲዬም ላይ የተፈጠረው አለመግባባት በክፍፍሉ ዙሪያ ያለውን ብዥታ ያስረዳል።
ስታዲዬሙ ላይ ሁለት የአማራጭ ሃሳብ ቀርቧል።
አንደኛው አማራጭ ስታዲየሙን በአክሲዮን ሶስቱም ክልሎች እንዲያስተዳድሩት በማድረግ ከስታዲዬሙ የሚገኘውን ገቢ በፍትሃዊነት መከፋፈል ሆኗል።
ይሄን ሃሳባቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ተወካዮችም ይደግፋሉ።
ሃሳቡ በሲዳማ ክልል ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም። ሲዳማ ሁለተኛውን አማራጭ አይቷል።
ሃሳባቸውን ለዋዜማ ሬዲዮ የሰጡት የሲዳማ ክልላዊ መንግስት የስራ ሃላፊ “የስታዲዬሙ ዋጋ ተተምኖ በረጅም ጊዜ ለሁለቱ ክልሎች ተገቢውን ክፍያ በመፈጸም ማስተዳደርን እንመርጣለን” ይላሉ።
ሲዳማ ክልል አሁን ላይ ይሄን የማድረግ አቅም እንዳለው የጠየቅናቸው ምንጮች በበኩላቸው “የማይሆን ነው” ሲሉ መልሰዋል።
ክልሉ አዲስ እንደመሆኑ አሁን ላይ በሰራተኛ ደመወዝ እና በቢሮ ኪራይ ወጭዎች ተወጥሯል። የሚሰበስበው ገቢ ክልሉን ለማስተዳደር ከሚያስፈልገው መጠን እጅጉን ያነሰ ነው። ለዚህም ነው ክልሉ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ ፈተና የሆነበት። በቅርቡ አዲስ ፕሮጀክት መጀመርም አይታሰብም።
ሲዳማ ክልል ካለበት የገንዘብ እጥረት አኳያም ለክፍፍል ዝግጁ ከሆኑ መንግስታዊ ሃብቶች መካከል አብዛኛውን ይዞ የመቆየትና የመውሰድ ፍላጎት አሳይቷል።
ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ የሲዳማ ክልል መንግስት ከፍተኛ አመራር ግን ሲዳማ ራሱን ችሎ ክልል ከሆነ በኋላ የኢኮኖሚ ፈተና ገጥሞታል በሚለው አይስማሙም። ዋዜማ ይህን አስተያየት እንድታርም ከጠየቁ በኋላ ሲዳማ በበፊቱ የደቡብ ክልል ውስጥ የነበረውን ከፍ ያለ የኢኮኖሚ ድርሻ ሁሉም ያውቀዋል። አሁንም በተሻለ ደረጃ የሚገኘው ሲዳማ “የብልፅግና መርሀግብር” አውጥቶ በርትቶ እየሰራ ነው ይላሉ ሀላፊው።
የሀብት ክፍፍሉን በተመለከተ ሁሉም ከሲዳማ ለመቀማት የሚያደርገው ሩጫ ተገቢ አለመሆኑንና አጎራባች ክልሎች በጋራ የመልማትን ጉዳይ እንዲያስቡበት ሀላፊው ይመክራሉ።
ክልሉ ካለፉት 27 አመታት የተሻለ ከክልል ምስረታ በኋላ በርካታ መሰረተ ልማቶችን መዘርጋቱን፣ የንጹህ ውሃ ጥያቄ መመለሱን እና በኢንቨስትመንትም ከፍተኛ ገቢ ማስመዝገቡን ይገልጻሉ። የስታዲዬሙ ግንባታ ወጪ ቢተመንም በረጅም ጊዜ መክፈል እንዳማያቅታቸው ነው የሚናገሩት። “አብሮ እንደኖረ ህዝብ ብዙ ሃብት በክፍፍሉ ከመጠየቅ ተቆጥበናል” ብለዋል።
ከፌዴራል የ2015 በጀት አመት የክልሎች ድጋፍ ሲዳማ ክልል 8.4 ቢሊዬን ብር ተይዞለታል። ክልሉ ሰኔ 27 ከተመሰረተ ሁለት አመት ሆኖታል።
ሐዋሳ ከተማን ለአስር አመት በጋራ የመጠቀም ስምምነቱን በመተው ነባሩ ደቡብ ክልል በቅርብ ወራት ሊለቅ ዕቅድ እንዳለው ዋዜማ ከምንጮቿ ተረድታለች።
ሌሎች የክልልነት ጥያቄ አንስተው ራሳቸውን የቻሉ መንግስታት ለመመስረት በዝግጅት ላይ ያሉና በተስፋ የሚጠባበቁ አሉ። የሀብት ክፍፍሉም አዳዲስ ክልሎች በተፈጠሩ መጠን እየተወሳሰበ ይሄዳል። [ዋዜማ ራዲዮ]