ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዓመቱ መጀመሪያ እተገብረዋለሁ ያለውን ተግባራዊ ማድረግ አልቻለም፣ በዚህም ሳቢያ የባንኩ ሰራተኛች ቅሬታ ማሰማት መጀመራቸውን ዋዜማ ሰምታለች።
ባንኩ ተግባራዊ ሊያደርግ ያስጠናው አዲስ መዋቅር ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር በአንድ ላይ ታጭቆ ይመራ የነበረው የተለያየ የኢንቨስትመንትን ዘርፍ በአይነት በመክፈል በዳይሮክቶሬት ደረጃ የሚያዋቅር እና ለደንበኞችም የተቀላጠፈ እና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላልም የተባለለት ነው።
ለአብነት ያህልም በግብርና ኮርፖሬት ፋይናንሲንግ ስር የሰብል ምርት ዳይሮክቶሬት፤ የሆልቲካልቸራል እና የደን ልማት ዳይሮክቶሬት፤ የቁም እንስሳት እርባታ ዳይሮክቶሬት ሌሎች የግብርና ስራዎችንም ያካተተ ዳይሮክቶሬት እንዲቋቋም መዋቅሩ ተጠንቶ ተጠናቋል።
ይኸው አደረጃጀት በኢንደስትሪያል ፋይናንስ ኮርፖሬት ስርም የጨርቃ ጨርቅ እና ሌዘር፤ የምግብ እና ምግብ ነክ ፕሮሰሲንግ፤ የኬሚካል እና ፋርማቲኩላር ዳይሮክቶሬት አና ሌሎችም በዚሁ ስር እንዲዋቀሩ እንደሚደረግ ዋዜማ ያገኘችው የባንኩ የጥናት ሰነድ ያመለክታል።
ይህ አዲስ መዋቅር የሚቋቋሙት ዳይሬክቶሬቶች ለዘርፉ እውቀት ባላቸው ባለሙያዎች እንዲመራ በማስቻል ከዚህ ቀደም ባንኩ ያጋጥመው የነበረው የፕሮጀክቶች መበላሸት እና የብድር አለመመለስ ችግርን የሚፈታ መፍትሄ ይዞ እንደሚመጣም ተስፋ ተጥሎበታል
ይህንን መዋቅርም ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል የባንኩ ሰራተኞች ከ4 ወር በፊት በፈተና እንዲወዳደሩ በማድረግ የስራ ምደባ ለማውጣት ሙከራ ቢደረግምዋ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ሂደቱ መቋረጡን ሰራተኞቹ ያስረዳሉ።
ባንኩ በፍጥነት ያስጠናውን የመዋቅር ጥናት ተግባራዊ እንዲያደርግ ለማስገደድም ሰራተኞቹ የጋራ ፊርማ በማሰባሰብ ለባንኩ የአመራር ቦርድ ማስገባታቸውንም ዋዜማ ከምንጮቿ አረጋግጣለች።
የባንኩ የስራ አመራር በጉዳዩ ላይ አስተያየት ካለው በሚል ከሁለት ሳምንት በፊት ላቀረብነው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘንም። [ዋዜማ ራዲዮ]