ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያከናውኑ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ ዛሬን ጨምሮ ሶስት ቀን ቀርቶታል።
ይሁንና ዋዜማ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደሰማችው እስካሁን ጠቅላላ ጉባኤአቸውን ያካሄዱት አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ናቸው።
እነዚህም ብልጽግና ፓርቲ ፣ ህዳሴ፣ የጋምቤላ ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ እና ከፋ አረንጓዴ ፓርቲ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የካቲት 9 2014 ባወጣው ማስታወቂያ 13 አገራዊ እና 13 ክልላዊ በአጠቃላይ 26 ፓርቲዎች በአንድ ወር ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን አካሂደው አስፈላጊ የሰነድ ማሻሽያዎች ለቦርዱ እንዲያስገቡ ማሳሰቡ ይታወሳል ።ይሁንና በርካታ አገራዊና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔያቸውን አላካሄዱም።
በቀጣይ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ለማካሄድ ለቦርዱ ያሳወቁ ፓርቲዎች መኖራቸውንም ከቦርዱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ከነዚህ መካከል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መጋቢት 11 2014 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባዔያቸውን እንደሚያካሄድ ቀደም ብሎ አስታውቆ ነበር።
ጠቅላላ ጉባኤ የሚያካሂዱበት ጊዜ እንዲራዘምላቸው ጥያቄ ካቀረቡ ዘጠኝ ፓርቲዎች መካከል ለአረና ትግራይ ለዴሞክራሲያዊ ሉዓላዊነት፣ ለአፋር ህዝብ ፓርቲ እንዲሁም ለነጻነትና እኩልነት ፓርቲዎች በቂ ምክንያት በማቅረባቸው እንደተራዘመላቸው ለማወቅ ችለናል።
ከእነዚህ መካከል ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ መጋቢት 18 2014 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ ፕሮግራም መያዙን ዋዜማ ሰምታለች።
የይራዘምልን ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት ያላገኙና ጥያቄ ያላቀረቡ ፓርቲዎችን ጉዳይ ቦርዱ ከቀነ ገደቡ መጠናቀቅ በኋላ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጠቅላላ ምርጫ በፊት ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም በወቅቱ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ከምርጫ በኋላ እንዲያከናውኑ በቦርዱ ተወስኖ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። ከዚያ ውሳኔና ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላ ደግሞ አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መሆኗ ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ የማያስችል ሁኔታ ፈጥሮ ቆይቷል። በቅርቡ ደግሞ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን የድርቅ ሁኔታ በምክንያትነት በመጥቀስ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቦርዱን ቀነ ገደብ በመቃወም የይራዘምልን ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል። [ዋዜማ ራዲዮ]