ዋዜማ ራዲዮ- በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የትግራይ ህዝብ በህወሓት ቡድን አቋም ምክንያት ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት ብልጽግና ፓርቲ በማንኛውም የሰላም አማራጭ ሁኔታውን ለመቋጨት እንደሚሰራ አስታወቀ።
የፓርቲው የህዝብና የአለምአቀፍ ግንኙነት ሃላፊ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ ትናንት በተጀመረው የፓርቲው የመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ ውይይት የተደረገባቸውን ጉዳዮች አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የማዕከላዊ ኮሚቴ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበትና እንደጸደቀ የገለጹ ሲሆን በዚህ ሪፖርት በዋናነት የአገሪቱ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ መካተቱን ገልጸዋል።
የትግራይ ህዝብ አካላችን ነው ህዝባችን ነው ሲሉ የገለጹት ሃላፊው የትግራይ ህዝብ በህወሃት አቋም ምክንያት ያልተገባ ዋጋ እየከፈለ ነው ብለዋል። በዚህም መነሻነት ብልጽግና ፓርቲ በማንኛውም የሰላም አማራጭ ይህን ለማስቀረት ይሰራል ብለዋል። ሃላፊው የሰላም አማራጭ ያሏቸውን ግን በዝርዝር ከመግለፅ ተቆጥበዋል።
ብልጽግና ፓርቲ እያካሄደ በሚገኘው በዚህ የመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲውን ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዝደንት እንዲሁም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የሚመርጥ ሲሆን ማዕከላዊ ኮሚቴው ደግሞ የስራ አስፈፃሚ አባላት ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል። በሌላ በኩል የፓርቲው ፕሮግራም እንዲሁም መተዳደሪያ ደንብ በዚህ ጉባኤ ይጸድቃሉ ። [ዋዜማ ራዲዮ]