ዋዜማ ራዲዮ- በሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የፀጥታ አካላት ግድያ ተከሰው ጥፋተኛ የተባሉ ተከሳሾች ከ15 ዓመት እስከ እድሜ ልክ እስከ ፅኑ እስራት ቅጣት ተወሰነባቸው፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ የካቲት 29/2014 ዓ/ም በዋለው የወንጀል ችሎት በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የፀጥታ አካላት ግድያ ተከሰው በክስ መዝገቡ ከቀረቡትና ጥፋተኛ ከተባሉ ተከሳሾች ፣ ጉዳያቸው በሌሉበት የታዩት ሻንበል መማር ጌትነት፣ በላይሰው ሰፊነው እና ልቅናው ይሁኔ የተባሉ ሦስት ተከሳሾችን በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ሲቀጣ፤ 18 ተከሳሾችን በ16 ዓመት ከ6 ወር፣ 2 ተከሳሾች በ15 ዓመት፣ 2 ተከሳሾች በ16 ዓመት፣ 4 ተከሳሾችን በ18 ዓመት እና 2 ተከሳሾችን በ17 ዓመት ፅኑ እስራት ቀጥቷል።
ፍርድ ቤቱ የጤና ሁኔታ፣ ማህበራዊ አገልግሎት ፣ ለሀገር የተከፈለ ዋጋ፣ የቤተሰብ ኃላፊነት፣ ከዚህ በፊት ያለ ሪከርድ አለመቅረብ የሚሉ 5 ማቅለያዎችን መሰረት በማድረግ ለ4 ተከሳሾች 5 ማቅለያዎችን፤ ለ20 ተከሳሾች 4 ማቅለያዎችን፤ ለ4 ተከሳሾች 3 ማቅለያዎችን ጉዳያቸው በሌሉበት የታየው ለ3 ተከሳሾች 1 ማቅለያ ከግምት አስገብቷል።
ከህዳር 23/2012 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ጉዳዩን ሲያይ የነበረው ችሎቱ
- ሻምበል ውለታው አባተን በ16 ዓመት፣
- ሻለቃ አዱኛ ወርቁን በ17 ዓመት፣
- ሻንበል ታደሰ እሸቴን በ17 ዓመት፣
- ሃምሳ አለቃ በላቸው ዘውዴን በ15 ዓመት፣
- ሃምሳአለቃ አበበ መልኬን በ16 ዓመት፣
- ሃምሳአለቃ አሰፋ ጌታቸውን በ16 ዓመት ከ6 ወር ፣
- ሃምሳ አለቃ አየነው /ምድብ/ ታደሰን 16 ዓመት ከ6 ወር፣
- መልካሙ ባለሟልን በ16 ዓመት ከ6 ወር፣
- ሙሉጌታ ፀጋየን በ18 ዓመት፣
- አያልነህ /ፔፕሲ/ ገዛኸኝን በ16 ዓመት ከ6ወር፣
- ብርሀኑ ይደጉን በ16 ዓመት ከ6 ወር፣
- ፈንታሁን እንድሪስን በ16 ዓመት ከ6 ወር፣
- ሃምሳ አለቃ አሊ ሀሰንን በ18 ዓመት፣
- ሃምሳ አለቃ ሲሳይ ገላናውን በ15 ዓመት፣
- ፈቃዱ ምትኩን በ18 ዓመት፣
- በለጠ ወርቁን በ16 ዓመት ከ6 ወር፣
- አሸናፊ ዳኘን በ16 ዓመት ከ6 ወር፣
- ይመር እሸቱን በ16 ዓመት ከ6 ወር፣
- እሸቴ ስዩምን በ16 ዓመት ከ 6 ወር፣
- ምስጋናው ገነትን በ16 ዓመት ከ6 ወር፣
- አባተ ብዟየሁን በ18 ዓመት፣
- መንግስቱ መኩሪያውን በ16 ዓመት ከ6 ወር፣
- መለሰ መብራቱን በ16 ዓመት ከ6 ወር፣
- ሃምሳአለቃ ጥጋቡ ለገሰን በ16 ዓመት ከ6 ወር፣
- አሊ ኢብራሂምን በ16 ዓመት ከ6 ወር፣
- መንግስቱ እያሱን በ16 ዓመት ከ6 ወር፣
- ሃምሳ አለቃ ልመንህ የኔሰውን በ16 ዓመት ከ6 ወር፣
- ጉልሽ ደምሳሽን በ16 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።