ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ የ40/60 እና 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የፋይናንስ እጥረት ማጋጠሙን ተከትሎ፣ ለቤቶቹ ማጠናቀቂያ ብድር እንዲፈቀድ ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ቀረበ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥር 16/2014 የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የስድስት ወራት ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ የሚገነቡ የጋር መኖሪያ ቤቶች ሳይጠናቀቁ ለተጠቃሚዎች በመተላለፋቸው ውስብስብ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለምክር ቤቱ አቅርቧል፡፡
በቤቶቹ ለመኖር የሚያስችሉ እንደ መብራት፣ ውሃ እና ፍሳሽ ማስወገጃ ያሉ መሰረተ ልማቶች ሳይጠናቀቁ ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸው በርካታ ችግሮች ማስከተሉን የጠቆመው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ችግሩ እንዳይደገም ያልተጠናቀቁ 29 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የብድር ጥያቄ እንደቀረበ ገልጿል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአዲስ አበባ በአሁኑ ጊዜ 29 ሺሕ 40/60 እና 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መኖራቸውን የገለጸ ሲሆን፣ ቤቶቹን አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ እስከ 19 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አስታውቋል፡፡
ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው የብድር ጥያቄ የሚፈቀድ ከሆነ ሳይጠናቀቁ በተላለፉ ቤቶች ላይ የተፈጠረውን ችግር ማስቀረት እና ቤቶቹን በወቅቱ አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ እንደሚቻል በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ቤቶች ልማት አስተዳድር ኃላፊ አቶ ታደሰ ከበበ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
ለመኖሪያነት ለማገልግል የሚያስችል መሰረተ ልማት ሳይሞላላቸው ለተጠቃሚዎች የተላለፉ በተለይ የ13ኛው ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይጠናቀቁ ቁልፍ ቢሰጣቸውም ለመኖሪያነት ዝግጁ አለመሆናቸውን ነዋሪዎች በተጋጋሚ ቅሬታ ያቀርባሉ።፡፡
ያላለቁ ቤቶች የተረከቡ ተጠቃሚዎች ከተማ አስተዳደሩ ቤቶቹን እንዳጠናቅቅላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም አንዳንዶቹ ምንም እንኳን በመንግሥት የተገነቡ 40/60 እና 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መሸጥ በሕግ የተከለከለ ቢሆንም፣ ለሶስተኛ ወገን የሚሸጡ መኖራቸውም በተደጋጋሚ ይሰማል። [ዋዜማ ራዲዮ]