ዋዜማ ራዲዮ- በ2012 ዓም ለዩንቨርስቲ መግቢያ የማትሪክ ይወስዱ የነበሩ ተማሪዎች በኮቪድ 19 ምክንያት የካቲት 29 2013 ዓም መሰጠቱ የሚታወቅ ነው፡፡
ትምሕርት ሚኒስቴር ለዩንቨርስቲ የሚያስፈልገውን የመግቢያ ነጥብ ይፋ አድርጓል። ይሁንና ተማሪዎች ወደየትኛው የትምህርት ተቋማት እንደተመደቡ ገና ይፋ አልተደረገም።
በሀገሪቱ ባለው የፀጥታ ሳቢያ ልጆቻቸው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ነጥብ ቢኖራቸውም የአዲስ አበባና አቅራቢያ ከተሞች ነዋሪዎች (ወላጆች) ልጆቻቸውን አዲስ አበባ በሚገኙ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እያስመዘገቡ ነው።
የዋዜማ ሪፖርተር በተለያዩ የግል ኮሌጆች ተዘዋውራ እንደተመለከተችው የትምህርት ተቋማቱ በተመዝጋቢዎች ተጨናንቀዋል፣ አንዳንዶቹም ተጨማሪ ተመዝጋቢ ለመቀበል ቦታ የላቸውም።
ተመዝጋቢዎች የምዝገባና የአንድ ሴሚስተር ክፍያ እየፈፀሙ ነው ምዝገባውን እያከናወኑ ያሉት።
“ ልጄን ያሰተማርኩት የሰው እጅ አይቼ ነው። የ12 ክፍል የማትሪክ ውጤቱ በጣም ቆንጆ ነው። አዲስ አበባ ይመደባል ብዬ ባስብም የሚሆነው አይታወቅም። አገሪቷ ላይ ባለው ሁኔታ ከኔ ርቆ እንዳይሄድ የግል ኮሌጅ አራት ሺ አምስት መቶ ብር ከፍየ አስመዝግቤወዋለሁ” የምትለው ብርቱካን ስንታየው ልጇን ወደ ክፍለ ሀገር ቢሄድ ያለባን ፍርሀት ለዋዜማ ተናግራለች።
“ያለው ነገር ምንም ደስ አይልም። የምናየውም የምንሰማውም ያስፈራል። ለዚህ ነው ልጄን ምደባ ከመውጣቱ በፊት የግል ዩንቨርሰቲ ያስመዘገብኩት። …. ፡፡ አዲስ አበባ ከደረሰው በጣም ደስ ይለኛል አለበለዚያ ግን የትም ክፍለ አገር አልሰድም። ቅርብም ቢሆን” ትላለች ብርቱካን።
“ የግል ዩንቨርስቲ መክፈሉ በጣም እንደሚከብደኝ አውቃለው። ቢሆንም የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ። መለመን ካለብኝም እለምናለሁ ። እሱም ካቃተኝ ቤት ይቀመጣል እንጂ አገራችን ባለችበት ሁኔታ የትም አይሄድም” ስትል ስር የሰደደ ስጋቷን ታብራራለች።
“ ባለፈው አመት ትልቋ ልጄ የመቀሌ ዩንቨርስቲ ተመራቂ ነበረች ያሉት በዩኒቲ ዩንቨርስቲ ልጃቸውን ሲያሰመዘግቡ ዋዜማ ያገኘቻቸው አባት፣ ያለፈው ዓመት ያየሁትን ስቃይ መቼም መልሼ መየት አልፈልግም ይላሉ።
“በትግራይ ክልል ጦርነቱ ሲነሳ ልጄ በመቀሌ ዩንቨርሰቲ የአካውንቲንግ ተመራቂ ተማሪ ነበረች መንገድ እና ስልክ የተቋረጠበት ግዜ ያሳለፍነው ህይወት በጣም ከባድ ነው። በሽተኛ ነው የሆንኩት። የልጅን ነገር የወለደ ያውቀዋል። ለዚህ ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስኩት። ልጄን የትም አልክም ። ምንም ቢፈጠር ከአዲስ አበባ ውጪ አልክም” ብለዋል።
አስተያየት የጠየቅናቸው የሁለት የግል ዩንቨርሲቲ ሰራተኞች በድንገቴው የምዝገባ መጨናነቅ ግር እንደተሰኙና ብዙዎቹ ተቋማት የመማሪያ ቦታቸውን ከተመዘገበው ተማሪ ጋር ለማመጣጠን እቅድ እያወጡ መሆኑንና የመምህራን ቁጥርን ለመጨመር የቅጥር ስራ ለማከናወን እየተዘጋጁ መሆኑን ነግረውናል። [ዋዜማ ራዲዮ]