ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ዐቃቢያን ሕጎች አርብ ሚያዝያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ከተማው አስተዳደር በማምራት ያቀረቧቸው የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ምላሽ አንዲያገኝ አቤቱታ ያቀርባሉ።
ባለሙያዎቹ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ሲሆን በቁጥር ሶስት መቶ ያህል ናቸው።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ሲመጡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 64/2011 መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ ፍትሕ ቢሮ ፈርሶ የአዲስ አበባ ከተማ ዐቃቢ ህግ ቢሮ መቋቋሙ ይታወሳል።
ከሀገሪቱ የህግ ማሻሻያ ማዕቀፍ ጋር በተያያዘ ለዳኞችና ዐቃቢያን ሕጎች የደሞዝ ማሻሻያና ጥቅማ ጥቅም እንዲስተካከል ቢወሰንም ለዳኞች ብቻ የደሞዝ ጭማሪው ተደርጎ ለአቃቢ ህጎቹ ግን ሳይሰተካከል ቀርቷል።
በፌደራል እና ክልሎች የዳኞች እና ዐቃቢያን ሕጎች ደሞዝ ትይዩ ሆኖ የሚተገበርበት አሰራር በመላዋ አገሪቱ ሲተገበር የከተማዋ ዳኞች በትምሕርትም በክህሎትም ሆነ የስራ ልምድ ከከተማዋ ዐቃቢያን ሕጎች ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ሳለ የዳኞች ጥቅማ ጥቅም ጥያቄ በአፋጣኝ ምላሽ ሲያገኝ የዐቃቢያን ሕጎች ግን ችላ መባሉ አግባብነት የለውም ሲሉም ይገልጻሉ፡፡
ዋዜማ ባገኘችው መረጃ መሰረት የፌድራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና የፌድራል ዳኞች አሁን የሚከፈላቸው ደሞዝ መነሻ 18.000 ሺሕ(አስራ ስምንት ሺሕ ብር) ሲሆን የመኖሪያ ቤት አበል 4.500 (አራት ሺሕ አምስት መቶ ብር) የትራንስፖርት አበል 2.500(ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር) እና የሞባይል ካርድ 250(ሁለት መቶ ሃምሳ ብር) ያገኛሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዳኞችም በተመሳሳይ መነሻ ደሞዛቸው 18.000 ሺሕ(አስራ ስምንት ሺሕ ብር) ነው፡፡
የአዲስ ከተማ አስተደዳር ዐቃቢያን ሕጎች ደሞዝ ግን መነሻው 5.432 (አምስት ሺሕ አራት መቶ ሰላሳ ሁለት ብር) ሲሆን የመኖሪያ ቤት አበል 2.150 (ሁለት ሺሕ አንድ መቶ ሃምሳ) የትራንስፖርት አበል 900(ዘጠኝ መቶ ብር) ነው፡፡
ከክልሎች ፣ የደቡብ ክልል ጠቅላይ ዐቃቢያን ሕጎች እና ዳኞች መነሻ ደሞዛቸው 15.445 (አስራ አምስት ሺሕ አራት መቶ አርባ አምስት ብር) ሲሆን ጥቅማ ጥቅሞችን አያካትትም፡፡
መጋቢት 20 ቀን 2013 ዓ.ም የየክፍለ ከተማዎቹ ዐቃቤ ህግ ፅ/ቤት ዐቃቤያነ ሕጎች ፊርማ ያረፈበትና ጥያቄያቸውን የሚያስረዳ ዝርዝር ማስረጃ ለከተማ አስተዳደሩ አስገብተው የነበረ ሲሆን ጥያቄያቸው ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።
ያቀረብነው ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ በህጋዊ መንገድ አቤቱታችንን እንቀጥላለን ብለዋል አስተባባሪዎቹ።
ዐቃቢያን ሕጎች የህዝብና የመንግስት ጥቅምና ህጋዊ አሰራር መከበሩን ከሚከታተሉ የመንግስት የፍትህ አካላት መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። [ዋዜማ ራዲዮ]