ዋዜማ ራዲዮ- በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ጃርቴ ጃርቴጋ ወረዳ ሐሮ ዳኢ በተባለ ቀበሌ ማክሰኞ አመሻሽ ሰባት ሰዎች ኦነግ ሸኔ መሆናቸው በተነገረ ታጣቂዎች መገደላቸውን እና ሶስት ሰዎች መቁሰላቸውን የዋዜማ ሪፖርተር ዘግቧል።
የሰባቱ አስከሬን ቀብር ዛሬ ረቡዕ በዚያው በቀበሌያቸው መፈጸሙንና ገና ያልተገኘ አስከሬን መኖሩን የሟች ቤተሰቦች ለዋዜማ ገልጸዋል።
ሶስት ሰዎች በሕይወት የተገኙ ሲሆን ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል መግባታቸውን ጨምረው ተናግረዋል።
በተደጋጋሚ በዚሁ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን “የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች” የሚፈጽሙት ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ነዋሪዎቹ ሲገልጹ ቆይተዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት እሁድ የዚሁ የጃርቴ ወረዳ አጎራባች በሆነው አቤ ደንጎሮ ወረዳ 29 ሰዎች ኦነግ ሸኔ መሆናቸው በተነገረ ታጣቂዎች መገደላቸውን ዋዜማ መዘገቧ ይታወቃል።
ዛሬም የዚያው ወረዳ የዴቢስ ቀበሌ ነዋሪዎች ጥቃቱን በመፍራት የወረዳው መቀመጫ ወደ ሆነችው ቱሉ ዋዩ ከተማ እየገቡ ነው።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት የተፈናቀሉት ዜጎች ቁጥራቸው ከ1 ሺህ 800 በላይ እንደሚልቅ ተናግረዋል።
የአቤ ደንጎሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ በበኩላቸው ህዝቡ መፈናቀሉን አምነው የተጠቀሰው ቁጥር ግን የተጋነነ ነው ሲሉ ለዋዜማ ተናግረዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]