ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) በሳምንቱ መጨረሻ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ዋዜማ አረጋግጣለች።
ዳይሬክተሩ ለሁለት ዓመታት ያህል ተቋሙን መርተዋል። አሁን ስልጣን የለቀቁበትን ምክንያት ለጊዜው አላብራሩም። ይሁንና ተቋሙ በተለያዩ ጊዜያት ከፅንፈኛ የፖለቲካ ሀይሎችና ሌሎች አካላት ጫና እንደነበረበት ዋዜማ ከዚህ በፊት ካሰባሰበችው መረጃ ተረድታለች።
ጌታቸው ድንቁ የብሮድካስት ባለስልጣንን እንዲመሩ ከተሾሙ ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ በዘርፉ መንግስት ሊወሰድ ቃል የገባውን የተሀድሶ እርምጃ ሲመሩ ነበር። በተለይ አፋኝ የሚዲያ ህጎች እንዲሻሻሉ፣ የመገናኛ ብዙሀን አቅም እንዲጎለብትና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን በግንባር ቀደምትነት መርተዋል።
የተሻሻለው የሚዲያ ህግ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወሳል። ከዚያ አስቀድሞም የብሮድካስት ባለስልጣን የሚዲያ ፖሊሲ አዘጋጅቶ ይፋ አድርጎ ነበር።
ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) ለረጅም አመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ በመምህርነትና በተመራማሪነት የሰሩ ሲሆን የማስተማርን ሙያ አብልጠው እንደሚወዱት ደጋግመው ሲገልፁ ይደመጣሉ። ወደ መንግስት ሀላፊነት ከመምጣታቸው በፊት ይኖሩበት ከነበረው ዩናይትድ ስቴትስ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ወደ ሀገራቸው ለዚሁ የማስተማር ስራ መመለሳቸውንም ይናገራሉ። [ዋዜማ ራዲዮ]