ዋዜማ ራዲዮ- የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብር እና በህገመንግስት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ችሎት ዛሬ ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም ረፋድ ላይ በኦፌኮ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የከፈተውን የክስ መዝገብ ተመልክቷል፡፡
ችሎቱ ከዚህ ቀደም በነበረው ቀጠሮ ሲሰየም በመዝገቡ የተካተቱት ጃዋር መሀመድ እና በቀለ ገርባ “ወደ ፍርድ ቤት ስንመጣ ጥቃት ሊደርስብን ይችላልና አንመጣም፤ባለንበት ቦታ ጊዜያዊ ችሎት ይቋቋምልን።” በማለት ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ በዛሬው ቀጠሮ በችሎት እንዲገኙ ጥብቅ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።
ትዕዛዙን ተከትሎ ዛሬ በችሎት የቀረቡት ተከሳሾች “ተገደን መቅረባችን አሳዝኖናል” ብለዋል።
ጃዋር መሀመድ በበኩሉ “እኛ ላይ ምንም አይነት ጥቃት ቢደርስ ኦነግ ሸኔ ነው ወይንም ወያኔ ነው ብላችሁ እንዳታሳብቡ። በእኛ ላይ ምንም አይነት ጥቃት ቢፈፀም ሀላፊነቱን የሚወስደው መንግስት እና ችሎቱ ነው።” ብሏል።
“የፍትህ ስርዓት ሂደቱን ለማፋጠን ነው ይህንን ውሳኔ የወሰንነው” ያለው ችሎቱ ዛሬ የተሰየመበትን ዋና ጉዳይ ማለትም የመቃወሚያ ክርክሩ ላይ መርምሮ የደረሰበትን ውሳኔ አሳልፏል።
ተከሳሾቹ ከዚህ ቀደም በቀረበባቸው ክስ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አሰምተው አቃቤ ህግም ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።
የግራ ቅኙን የፅሁፍ ክርክር የመረመረው ችሎቱ አቃቤ ህግ ካቀረበው ክስ ላይ 4 ነጥቦችን እንዲያሻሽል ትዕዛዝ ሰጥቷል።እኚህም በጃዋር ሞሀመድ ላይ ከቀረቡት ክሶች መሃከል 3ኛው ግልፅ ባለመሆኑ እሱ ተብራርቶ ይቅረብ፣3ኛ ተከሳሽ ቅስቅሳ ሲያደርግ ነበር የተባለው በየትኛው ሚዲያ እንደሆነ ይገለፅ፣ ከ5ኛ እስክ 10ኛ ያሉ ተከሳሾች ላይ ከጦር መሳሪያ ጋር ተያይዞ የቀረበው ክስ አዋጁ ተጠቅሶ ይቅመጥ የሚሉት እና በክስ መዝገቡ ላይ ሸኔ ተብሎ በደፈናው የተቀመጠው ይብራራ የሚሉት ናቸው።
የአቃቤ ህግን የተሻሻለ ክስ ለማየት ችሎቱ ለጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ስጥቷል።
አቃቤ ህግ ሰራተኞች በጠቅላላ ክፍለ ሀገር ስለሄዱ 1 ወር ይሰጠኝ የሚል ጥያቄ ቢያቀርብም ችሎቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ትልቅ ትቋም ነው ብዙ ሰራተኞች ሊኖሩት ይገባል በማለት ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል። [ዋዜማ ራዲዮ]