FILE- Previous US citizens evacuation

ዋዜማ ራዲዮ- አሜሪካ በትግራይ ውስጥ ያሉ አንድ ሺህ የሚገመቱ ዜጎቿን በአስቸኳይ ልዩ በረራ ከግጭት ቀጠናው ለማውጣት ከመንግስት ፈቃድ እየተጠባበቀች መሆኑን የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል።


በጉዳዩ ላይ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያቤት የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ሀላፊ ቲቦር ናዥ ትናንት ከውጪ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ጋር በስልክ መወያየታቸውን ስምተናል።
በትግራይ መውጫ አጥተው ያሉት ወገኖች በአብዛኛው የአሜሪካ ዜግነትን በተለያየ ጊዜ የወሰዱ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ቤተሰቦቻቸው ናቸው።


ቲቦር ናዥ ከውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ደመቀ መኮንን ጋር በነበራቸው ውይይት በማዕከላዊ መንግስትና በሕወሓት መካከል ያለው ግጭት ቆሞ ጉዳዩ በሰላማዊ ድርድር እንዲፈታ ሀገራቸው ያላትን ፍላጎት አስረድተዋል። አሜሪካ ችግሩ እንዲፈታ ገንቢ ሚና ለመጫወት ያላትንም ዝግጁነት ተናግረዋል።


አቶ ደመቀ መኮንን መንግስት በትግራይ የጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ያለመ መሆኑንና በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንመለሳለን ሲሉ አብራርተዋል።

በተመሳሳይ ድርድር እንዲጀመር ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ የነበሩት የአውሮፓ ህብረትና የጀርመን ባለስልጣናት ኢትዮጵያን ለማግባባት ያልተቋረጠ ሙከራ እያደረጉ ነው።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የአውሮፓ ህብረትና ጀርመን ያቀረቡላቸውን የድርድር ጥያቄ አልቀበልም ካሉ በኋላ የጀርመኑ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሂኮ ማስ ወደ ተባበሩት አረብ ዔምሬትስ ልዑል መሀመድ ቤን ዛይድ ስልክ ደውለው ዔምሬትስ የበኩሏን ማግባባትና ግፊት እንድታደርግ ጠይቀዋል።

የተባበሩት አረብ ዔምሬትስ ኢትዮጵያና ኤርትራን በማግባባትና ወደ ሰላም ስምምነት በማምጣት ጉልህ ድርሻ ነበራት።

የኢትዮጵያ መንግስት የጀመርኩት ዘመቻ ግቡን ሳይመታ ድርድር አልቀመጥም በሚል አቋሙ እንደፀና ነው። በሕወሓት በኩል ችግሩ በድርድር እንዲፈታ ከፍተኛ ፍላጎት አለ። [ዋዜማ ራዲዮ]