Ethiopian troops in Somalia, Photo The East African- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በትግራይ ክልል ታጣቂ ሀይልና በፌደራሉ መንግስት ወታደሮች መካከል ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ከጎረቤት ሶማሊያ ማስወጣት መጀመሯን በቦታው ከሚገኙ ምንጮች ስምተናል። ወታደሮቹ በትግራይ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ድጋፍ እንዲሰጡ ዕቅድ ስለመኖሩም ተነግሯል።

ከባድ መሳሪያ የታጠቁት የኢትዮጵያ ስላም አስከባሪ ወታደሮች ከነመሳሪያቸው ከሶማሌዋ ጌዶ ግዛት በብዛት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መመለሳቸውን የአፍሪካ ህብረት ስላም አስከባሪ ሀይል ምንጭ ለዋዜማ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ ጌዶ ግዛት በተደጋጋሚ ዘልቀው በመግባት ወታደራዊ ተልዕኳቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ ድንበር ተመልሰው ሲሰፍሩ የሚስተዋልበት አካባቢ ነው።

ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሀይል ስር የተሰማሩ ወታደሮች ቢኖራትም ግማሽ ያህል ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ያሰማራችው በተናጠል ከሶማሊያ መንግስት ጋር ባላት ስምምነት ነው። አሁን መንቀሳቀሳቸው የተነገረው ወታደሮች በተናጠል ስምምነት የተሰማሩት እንደሆኑ ታውቋል።


በተመሳሳይ ጊዜ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል ወታደሮች ወደ ድንበር ተንቀሳቅሰው በንቃት ድንበር እየጠበቁ መሆኑ ተሰምቷል።ረቡዕ ዕለት የፌደራሉ መንግስት ባለስልጣናት ወደ ጅጅጋ ተጉዘው በድንበርና ክፍለ አህጉታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ከክልሉ መንግስት ጋር ምክክር አድርገዋል።


የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ መውጣት መጀመር አመታት ላስቆጠረው የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ሀይል ትልቅ ፈተና ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው። ይሁንና ኢትዮጵያ ምን ያህል ወታደሮችን ለማስወጣት እንዳቀደች አልታወቀም። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ በሶማሊያ ያሉትን ሰባት መቶ ያህል የአሜሪካ ወታደሮች ለማስወጣት ማቀዳቸውን ይፋ አድርገው ነበር።


በተያያዘ ዜና የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፓምፒዮ በትግራይ ክልልና በፌደራል መንግስቱ መካከል የተፈጠረው ግጭት በአስቸኳይ እንዲረግብ ሁሉም ወገኖች ግጭት ከማባባስ እንዲቆጠቡ አሳስበው ” ህዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ በፌደራሉ መንግስት የጦር ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው” ብለዋል።

የእንግሊዝ የኖርዌይና፣ የሲውዲን መንግስታትም በትግራይ ክልልና በማዕከላዊው መንግስት መካከል የተፈጠረውን ግጭት አውግዘው ለችግሩ ሰላማዊ እልባት እንዲበጅለት መክረዋል።


በሌላ በኩል በትግራይ የተከሰተው የፀጥታ ቀውስ ያሳሰባት ሱዳን ወታደሮቿን ወደ ድንበር አስጠግታለች። በተለይ በገዳሪፍ በኩል በርከት ያለ ወታደር ያሰፈረች ሲሆን የሀገሪቱ ስራዊት በድንበር አካባቢ የሚኖረውን እንቅስቃሴ በንቃት እንዲከታተል ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሀምዶክ ረቡዕ ዕለት ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ስልክ ደውለው በተፈጠረው ችግር ዙሪያ ተወያይተዋል። ከሶስት ቀናት በፊት የሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤት ስብሳቢ አብዱል ፈታ አል ቡርሀን ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን በፀጥታ ትብብር ጉዳዮች ላይ ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር ስፊ ውይይት አድርገው ነበር። [ዋዜማ ራዲዮ]

To reach Wazema Editors- —–wazemaradio@gmail.com